በማስተዋል ስበኩ
1 ማስተዋል እንዲኖረን ከፈለግን ስለምንሰብክላቸው ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ አለብን። ይህን ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሰዎችን ልብ መንካታችን የተመካው የመንግሥቱን መልእክት እነርሱን በሚስባቸው መንገድ በማቅረባችን ላይ ነው። በጥር ወር እስካሁን በጉባኤው እጅ ሊኖሩ የሚችሉትን የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ መጽሐፎች እናበረክታለን። ጉባኤው እነዚህ መጽሐፎች ከሌሉት አስፋፊዎች ወጣትነትህ እና የቤተሰብ ኑሮ የተባሉትን መጽሐፎች ያበረክታሉ። ከዚህ ቀጥሎ ጠቃሚ ሐሳቦች ቀርበዋል።
2 “የቤተሰብ ኑሮ” በተባለው መጽሐፍ የምትጠቀም ከሆነ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “በጊዜያችን ቤተሰብን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች ባለፉት ትውልዶች አይታወቁም ነበር ቢባል አይስማሙም? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህ የሆነው ለምን ይመስልዎታል? [ሰውዬው የሰጠውን መልስ እንደምትስማማበት አሳይ። ከዚያም 2 ጢሞቴዎስ 3:1-3ን አውጥተህ አንብብ።] ‘ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ’ እና ‘ፍቅር የሌላቸው’ የሚሉት ሐረጎች በጊዜያችን ያሉትን ብዙ ሰዎች ሁኔታ በትክክል ይገልጻል። ሆኖም እነዚህ ችግሮች እንደሚከሰቱ የተናገረው አምላክ ቤተሰብን በይበልጥ ለማቀራረብ የሚያስችል አስተማማኝ ምክር ጭምር ሰጥቶናል።” በገጽ 2 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፉ አዘጋጂዎች” የሚለውን አንቀጽ አንብብ።
3 “የአምላክ ዘላለማዊ ዓላማ ለሰው ልጆች ጥቅም ድል በማድረግ ላይ ነው” የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ የምታበረክት ከሆነ መፍትሔ ያልተገኘለትን ማኅበራዊ ችግር በተመለከተ አንድ ትኩስ ዜና ከጠቀስክ በኋላ እንዲህ ብለህ በመጠየቅ ልትጀምር ትችላለህ:-
◼ “ሰዎች አንድ ቀን ይህንን ችግር የሚፈቱት ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለትና በሰውዬው ሐሳብ እንደምትስማማ ግለጽ።] ሁላችንም እንደዚህ ዓይነት ችግር በሌለበት ዓለም ውስጥ መኖር እንፈልጋለን። ይህም በምንጸልይለት የአምላክ መንግሥት ሥር እውን ይሆናል።” ሰላምና ደህንነት እንዴት ሊገኝ እንደሚችል ለማሳየት ኢሳይያስ 32:17, 18ን አንብብ። በተጨማሪም በገጽ 4 ላይ ከርዕሱ ሥር የተሰጠውን የመግቢያ ሐሳብ አንብብና መጽሐፉ አምላክ ስለ ምድር የሰጠው ተስፋ በቅርቡ እንደሚፈጸም የሚያሳይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ እንደሚያቀርብ ተናገር። ሰውዬው በሐሳቡ ከተደሰተ መጽሐፉን አበርክትለት።
4 ጥሩ ማስተዋል ካለን የምናገኛቸው ሰዎች የሚያስፈልጋቸውንና የሚያስደስታቸውን ነገር ለመገንዘብ እንችላለን። ምሳሌ 16:23 በ1980 ትርጉም “አስተዋይ ሰዎች ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ፤ ስለዚህ የሚናገሩት ሁሉ ተደማጭነት አለው” በማለት ይህንን ያረጋግጥልናል።