“ይህን ዘወትር ለመታሰቢያዬ አድርጉት”
1 ሰዎች ትልቅ ግምት የሚሰጣቸውን ጉዳዮች እንኳ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አስፈላጊነታቸውን የመርሳት ዝንባሌ አላቸው። ኢየሱስ ‘የጌታ እራትን’ ባስጀመረበት ጊዜ “ይህን [“ዘወትር፣” NW] ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት ደቀ መዛሙርቱን ያዘዛቸው በዚህ ምክንያት ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክርስትያኖች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በማክበር “ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና” የሚለውን በታዛዥነት ሲጠብቁ ቆይተዋል።—1 ቆሮ. 11:20, 23-26
2 በቅርብ ጊዜ ኢየሱስ ‘ከታናሹ መንጋ’ ቀሪዎች መካከል የመጨረሻዎቹን በሰማያዊው ስፍራ ይቀበላቸዋል። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 14:2, 3) በዚህ ዓመት ቅቡዓን ቀሪዎች ቁጥሩ እየጨመረ ከሚሄደው ታላቅ መንጋ ማለትም ‘ከሌሎች በጎች’ ጋር በመሆን ሚያዝያ 11 ቀን የጌታ እራትን እንደገና የማክበር መብት ያገኛሉ። (ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 7:9, 10) ይህም ይሖዋ አንድያ ልጁን በመላክ ለሰው ልጆች ላሳየው ታላቅ ፍቅር ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። ይህ በዓል የኢየሱስን ምሳሌነት፣ ፍቅሩን፣ ቤዛ ለመሆን ሲል እስከ ሞት ድረስ ያሳየውን ታማኝነት፣ በተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ እንደሚገኝና መንግሥቱ ለሰው ልጆች የሚያመጣውን በረከት ያጎላል። እውነትም ሊከበር የሚገባው በዓል ነው!
3 ከአሁኑ እንዘጋጅ፦ ይህንን የመታሰቢያ በዓል ለእኛም ሆነ ከእኛ ጋር ለሚሰበሰቡት ታላቅ የደስታና አመስጋኝነታችንን የምንገልጽበት ጊዜ እንዲሆን ሁላችንም እንጣር። የኢየሱስን የመጨረሻዎቹን ጥቂት የአገልግሎት ቀናትና ሊሞት አካባቢ የነበሩትን ሁኔታዎች እንደገና ከመጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ለበዓሉ ራሳችንን ልናዘጋጅ እንችላለን። ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ጥቂት ሳምንታት በቤተሰብ ጥናታችን ታላቅ ሰው ከተባለው መጽሐፍ ከምዕራፍ 112-16 ያሉትን ልንከልስ እንችላለን።
4 ለመታሰቢያው በዓል ያላቸውን አድናቆት በማነሳሳትና በዚያ መገኘታቸው አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ በማድረግ ልትጋብዛቸው የምትችል ምን ያህል ሰዎች አሉ? አሁኑኑ የስም ዝርዝራቸውን ጻፍና መምጣት እንዲችሉ በአንተ በኩል የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ከዚያም በሌሎች ስብሰባዎች ላይ ዘወትር እንዲገኙ በማበረታታት በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው።
5 የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሰሞን እያንዳንዱ ሰው የስብከት እንቅስቃሴውን ከፍ እንዲያደርግ ልዩ ዝግጅት ይደረጋል። በሚያዝያ ወይም በግንቦት ወር ጥሩ ፕሮግራም በማውጣት ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትችላለህን? የኢየሱስን መሥዋዕትነት በከፍተኛ አድናቆት እንደምናስታውሰው የምናሳይበት አንዱ ትልቅ መንገድ ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋ እና በልጁ የሚተዳደረው መንግሥት ስለሚያመጣው በረከት በመናገር ነው።—መዝ. 79:13፤ 147:1