የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • km 6/00 ገጽ 7-8
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 9—1 ሳሙኤል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 9—1 ሳሙኤል
  • የመንግሥት አገልግሎታችን—2000
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
የመንግሥት አገልግሎታችን—2000
km 6/00 ገጽ 7-8

የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 9​—1 ሳሙኤል

ጸሐፊዎቹ:- ሳሙኤል፣ ጋድ፣ ናታን

የተጻፈበት ቦታ:- እስራኤል

ተጽፎ ያለቀው:- 1078 ከዘአበ አካባቢ

የሚሸፍነው ጊዜ:- 1180-1078 ከዘአበ ገደማ

በ1117 ከዘአበ በእስራኤል መንግሥታዊ አወቃቀር ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ተካሄደ። ሰብዓዊ ንጉሥ ተሾመ! ይህ የሆነው ሳሙኤል የይሖዋ ነቢይ ሆኖ በእስራኤል ያገለግል በነበረበት ጊዜ ነው። ይሖዋ ይህ ሁኔታ እንደሚከሰት አስቀድሞ አውቆ የተናገረው ነገር ቢሆንም እንኳ የእስራኤል ሕዝብ ንጉሣዊ አገዛዝ ለማግኘት ያቀረቡት ጥያቄ ሳሙኤልን በጣም አስደንግጦታል። ሳሙኤል ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነና የይሖዋን ንጉሣዊ አገዛዝ በጥልቅ ያከብር የነበረ በመሆኑ ባልንጀሮቹ የሆኑት የአምላክ ቅዱስ ብሔር አባላት ከባድ ውድቀት እንደሚገጥማቸው ከወዲሁ ተገንዝቦ ነበር። ሳሙኤል የሕዝቡን ጥያቄ የተቀበለው ይሖዋ ስላዘዘው ብቻ ነው። “ሳሙኤልም የመንግሥቱን ወግ ነገረ፣ በመጽሐፍም ጻፈው በእግዚአብሔርም ፊት አኖረው።” (1 ሳሙ. 10:​25) በዚህ መንገድ የመሳፍንት ዘመን አከተመና በእስራኤል ዓይን ከፍተኛ ኃይልና ክብር ያለው በመጨረሻ ግን የይሖዋን ሞገስ የሚያሳጣቸውና ውርደት ላይ የሚጥላቸው የሰብዓዊ ንጉሥ አገዛዝ ዘመን ተጀመረ።

2 ይህን ከፍተኛ ለውጥ የተካሄደበትን ዘመን ለመመዝገብ ብቁ የሚሆነው ማን ነው? ይሖዋ ታሪኩን መጻፍ እንዲጀምር ታማኙን ሳሙኤል መምረጡ ተስማሚ ነው። ሳሙኤል የሚለው ቃል “የአምላክ ስም” ማለት ሲሆን በዚያን ጊዜ የይሖዋን ስም ከፍ አድርጎ በመያዝ ረገድ በእርግጥም ጎልቶ የሚታይ ሰው ነበር። ሳሙኤል የመጀመሪያዎቹን 24 ምዕራፎች የጻፈ ይመስላል። ከዚያም እርሱ ከሞተ በኋላ እስከ ሳዖል ሞት ድረስ ያለውን የጥቂት ዓመታት ታሪክ የጻፉት ጋድ እና ናታን ናቸው። በ1 ዜና መዋዕል 29:​29 ላይ ይህ ሁኔታ የተገለጸ ሲሆን ጥቅሱም እንዲህ ይላል:- “የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፣ እነሆ፣ በባለ ራእዩ በሳሙኤል ታሪክ፣ በነቢዩም በናታን ታሪክ፣ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፎአል።” የሳሙኤል መጽሐፍ ከነገሥትና ከዜና በተለየ መንገድ ቀድሞ ስለተፈጸሙ ታሪኮች ምንም አይዘግብም። ይህም በዳዊት ዘመን በሕይወት የነበሩት ሳሙኤል፣ ጋድ እና ናታን ጸሐፊዎች እንደነበሩ ያረጋግጣል። እነዚህ ሦስት ሰዎች የታመኑ የይሖዋ ነቢያት የነበሩ ሲሆን የብሔሩን ጥንካሬ ያዳከመውን የጣዖት አምልኮ ተቃውመዋል።

3 ሁለቱ የሳሙኤል መጻሕፍት በመጀመሪያ በአንድ ጥቅል ወይም በአንድ ጥራዝ የተጻፉ ነበሩ። ይህን ክፍል የያዘው የግሪኩ ሴፕቱጀንት በታተመ ጊዜ የሳሙኤል መጽሐፍ ለሁለት ተከፈለ። በሴፕቱጀንት እትም ውስጥ አንደኛ ሳሙኤል አንደኛ መንግሥት ተብሎ ይጠራ ነበር። ይህ አከፋፈልና አንደኛ ነገሥት የሚለው ስያሜ በላቲኑ ቩልጌት ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን በካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሁን ድረስ ይሠራበታል። አንደኛና ሁለተኛ ሳሙኤል መጀመሪያ ላይ አንድ መጽሐፍ የነበሩ መሆናቸውን ማሶራውያን ለ​1 ሳሙኤል 28:24 ጥቅስ ከሰጡት ማስታወሻ ማየት ይቻላል። ይህ ጥቅስ የሳሙኤል መጽሐፍ መሐከል ላይ እንደሚገኝ ማስታወሻቸው ይገልጻል። መጽሐፉ ተጽፎ ያለቀው በ1078 ከዘአበ አካባቢ ይመስላል። ይህ ከሆነ አንደኛ ሳሙኤል ከአንድ መቶ ዓመት ጥቂት በለጥ የሚሉ ዓመታትን ማለትም ከ1180 እስከ 1078 ከዘአበ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል።

4 ዘገባው ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። በውስጡ የሰፈሩት መግለጫዎች ከጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ጋር ይስማማሉ። ዮናታን በማክማስ ሰፍሮ በነበረው የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ላይ በተሳካ ሁኔታ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ የተሟላ ድል የተቀዳጀ ሲሆን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም የእንግሊዙ የጦር አዛዥ፣ በመንፈስ አነሳሽነት በሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸውን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ተከትሎ ቱርኮችን ድል ማድረጉ ትኩረት የሚስብ ነው።​—⁠14:​4-14

5 ይሁን እንጂ መጽሐፉ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና በውስጡ የያዛቸውም ታሪኮች ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ከዚያ የበለጠ ጠንካራ ማስረጃዎች አሉ። እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲሾምላቸው እንደሚጠይቁ ይሖዋ አስቀድሞ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ነው። (ዘዳ. 17:​14፤ 1 ሳሙ. 8:​5) ከዓመታት በኋላ ሆሴዕ “በቁጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፣ በመዓቴም ሻርሁት” በማለት ይሖዋ የተናገረውን ቃል በመጥቀስ ለዘገባው ትክክለኝነት ተጨማሪ ማጠናከሪያ ሰጥቷል። (ሆሴዕ 13:​11) ጴጥሮስ፣ ሳሙኤል ስለ ኢየሱስ ‘ወራት የተናገረ’ ነቢይ እንደሆነ አድርጎ በመጥቀስ ሳሙኤል በመንፈስ አነሳሽነት የተናገረ ነቢይ መሆኑን አመልክቷል። (ሥራ 3:​24) ጳውሎስ የእስራኤልን ታሪክ ባጭሩ በተናገረ ጊዜ ከ1 ሳሙኤል 13:​14 ላይ ጥቂት ሐሳቦችን ቀንጭቦ ወስዷል። (ሥራ 13:​20-22) ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን ፈሪሳውያን “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ እርሱ ያደረገውን . . . አላነበባችሁምን?” ብሎ በመጠየቅ ዘገባው ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል። ከዚያም ዳዊት የመሥዋዕቱን ኅብስት ለመብላት ያቀረበውን ጥያቄ ተናገረ። (ማቴ. 12:​1-4፤ 1 ሳሙ. 21:​1-6) ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ዕዝራም ታሪኩ እውነተኛ እንደሆነ አድርጎ ተቀብሏል።​—⁠1 ዜና 29:​29

6 ይህ መጽሐፍ ዳዊት ያደረጋቸው ነገሮች የመጀመሪያ ዘገባ እንደመሆኑ መጠን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ዳዊት የተጠቀሰበት ቦታ ሁሉ የሳሙኤል መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል መሆኑን ያረጋግጣል። በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈሩት አንዳንድ ክንውኖች በመዝሙር 59 (1 ሳሙ. 19:​11)፣ በመዝሙር 34 (1 ሳሙ. 21:​13, 14)፣ እና በመዝሙር 142 (1 ሳሙ. 22:​1 ወይም 1 ሳሙ. 24:​1, 3) ላይ ባሉት የዳዊት መዝሙር መግቢያዎች ላይ እንኳ ሳይቀር ተጠቅሰው ይገኛሉ። አንደኛ ሳሙኤል ትክክለኛ ዘገባ መሆኑን የአምላክ ቃል ራሱ በማያሻማ መንገድ ያረጋግጣል።

ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት

27 አንደኛ ሳሙኤል እንዴት ድንቅ የሆነ ታሪክ ይዟል! የእስራኤላውያንን ድክመትም ሆነ ጥንካሬ በሐቀኝነት በዝርዝር ይገልጻል። በዚህ ወቅት በእስራኤል ሁለቱ የአምላክን ሕግ የተከተሉ፣ ሁለቱ ደግሞ ያልተከተሉ በድምሩ አራት ነገሥታት ነበሩ። ዔሊ እና ሳኦል ስህተት የፈጸሙት እንዴት እንደሆነ ልብ በል:- ዔሊ ማድረግ የነበረበትን ሳያደርግ የቀረ ሲሆን ሳኦል ደግሞ ማድረግ የሌለበትን በትዕቢት አድርጓል። በሌላው በኩል ደግሞ ሳሙኤልና ዳዊት ከልጅነታቸው ጀምሮ ለይሖዋ መንገድ ፍቅር እንዳላቸው አሳይተዋል፤ ይህም በረከት አስገኝቶላቸዋል። ከዚህ ለሁሉም የበላይ ተመልካቾች የሚሆን እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት እናገኛለን! የበላይ ተመልካቾች ጽኑ፣ የይሖዋን ድርጅት ንጽሕናና ሥርዓታማነት በንቃት የሚከታተሉ፣ ለይሖዋ ዝግጅት አክብሮት ያላቸው፣ ደፋሮች፣ መንፈሳቸውን የሚገዙ፣ ቆራጦችና ለሌሎች ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያሳዩ መሆናቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! (2:​23-25፤ 24:​5, 7፤ 18:​5, 14-16) በተጨማሪም ስኬታማ የሆኑት እነዚህ ሁለት ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ጥሩ የሆነ ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና እንዳገኙና ሁለቱም ገና ለጋ ወጣት በነበሩበት ጊዜ የይሖዋን መልእክት ለመናገርና በአደራ የተቀበሉትን ኃላፊነት በጥንቃቄ ለመጠበቅ ደፋር እንደነበሩ ልብ በል። (3:​19፤ 17:​33-37) ዛሬም በወጣትነት ዕድሜያቸው ይሖዋን የሚያገለግሉ ሁሉ “የሳሙኤል” እና “የዳዊት” ዓይነት አቋም እንዲኖራቸው እንመኛለን!

28 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙት ጠቃሚ ቃላት መካከል ቶሎ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ሳኦል “የአማሌቅን ዝክረ ስሙን ከሰማይ በታች” ሳያጠፋ በመቅረቱ ይሖዋ በሳሙኤል በኩል ያስነገረው ፍርድ እንደሚሆን ግልጽ ነው። (ዘዳ. 25:​19) ‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’ የሚለው ትምህርት በሆሴዕ 6:​6፣ በሚክያስ 6:​6-8 እና በማርቆስ 12:​33 ላይ በተለያየ መንገድ በተደጋጋሚ ተገልጿል። (1 ሳሙ. 15:​22) ዛሬም እኛ የአምላካችንን የይሖዋን ድምፅ ሙሉ በሙሉ በመታዘዝ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከዚህ ዘገባ ጥቅም ማግኘታችን የተገባ ነው! የደምን ቅድስና አውቆ መታዘዝ በ1 ሳሙኤል 14:​32, 33 ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ተገቢ በሆነ መንገድ ደሙ ያልፈሰሰን ስጋ መብላት ‘በይሖዋ ላይ በደል’ መፈጸም እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። በሥራ 15:​28, 29 ላይ በግልጽ ሰፍሮ እንደሚገኘው ይህ በክርስቲያን ጉባኤም ላይ ይሠራል።

29 የአንደኛ ሳሙኤል መጽሐፍ የእስራኤል ብሔር ከሰማይ ሆኖ የሚያስተዳድረው የአምላክ አገዛዝ ተግባራዊ እንዳልሆነ አድርገው በመመልከት የፈጸሙትን አሳዛኝ ስህተት ያሳያል። (1 ሳሙ. 8:​5, 19, 20፤ 10:​18, 19) ሰብዓዊ አገዛዝ ምን ያህል አደገኛና ከንቱ መሆኑ በስዕላዊም ሆነ ትንቢታዊ መንገድ ተገልጿል። (8:​11-18፤ 12:​1-17) መጀመሪያ ላይ ሳኦል የአምላክ መንፈስ ያለው ልኩን ­የሚያውቅ ሰው ­እንደነበር ተገልጿል። (9:​21፤ 11:​6) ይሁን እንጂ ለጽድቅ የነበረው ፍቅርና በአምላክ ላይ የነበረው እምነት እየተመናመነ ሲሄድ ማስተዋሉ ጨለመ እንዲሁም ልቡ ክፉ ሆነ። (14:​24, 29, 44) በኋላ ላይ ያሳየው ትዕቢት፣ የዓመፀኝነት መንፈስና በአምላክ ላይ የፈጸመው ክህደት መጀመሪያ ላይ አስመዝግቦት የነበረውን ቅንዓት ሁሉ መና አድርጎታል። (1 ሳሙ. 13:​9፤ 15:​9፤ 28:​7፤ ሕዝ. 18:​24) እምነት ማጣቱ ወደ ፍርሃት፣ ምቀኝነት፣ ጥላቻና ነፍስ ግድያ መርቶታል። (1 ሳ⁠ሙ. 18:​9, 11፤ 20:​33፤ 22:​18, 19) በአምላኩና በሕዝቡ ፊት ማፈሪያ ሆኖ በዚያው አኗኗሩ ሞቷል። እንደ እርሱ ‘ኩራተኛ’ ለሆነ ሁሉ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆናል።​—⁠2 ጴጥ. 2:​9-12

30 ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒ በጥሩነቱ የሚታወቅ ሰው አለ። ለምሳሌ ያህል ማጭበርበር፣ መድሎ ሳይኖርበት ሕይወቱን በሙሉ እስራኤልን ያገለገለውን ታማኙ ሳሙኤል የተከተለውን አካሄድ ልብ በል። (1 ሳሙ. 12:​3-5) ከልጅነቱ ጀምሮ ታዛዥ ነበር (3:​5)፤ ጨዋና ሰው አክባሪ ነበር (3:​6-8)፤ በታማኝነት ሥራውን ያከናውን ነበር (3:​15)፤ አምላክን ለማገልገል ከገባው ውሳኔ ፈጽሞ ውልፍት አላለም (7:​3-6፤ 12:​2)፤ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነበር (8:​21)፤ የይሖዋን ውሳኔ ለማስፈጸም ፈጣን ነበር (10:​24)፤ ለማንም ፊት ሳያዳላ ይፈርድ ነበር (13:​13)፤ መታዘዝ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አጥብቆ ያምን ነበር (15:​22)፤ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ያልተቆጠበ ጥረት ያደርግ ነበር (16:​6, 11)። እንዲሁም ከሌሎች ጥሩ ስም አትርፏል። (2:​26፤ 9:​6) በወጣትነት ዕድሜው ያሳለፈው አገልግሎት በዛሬ ጊዜ የሚገኙ ወጣቶችን የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ (2:​11, 18) እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ያከናወነው አገልግሎት በእድሜ የገፉትን ሰዎች ይደግፋል።​—⁠7:​15

31 ዮናታንም ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ወራሹ እርሱ ሆኖ ሳለ ዳዊት በእርሱ ምትክ ንጉሥ እንዲሆን መቀባቱ ምንም ዓይነት የጥላቻ ስሜት አላሳደረበትም። ከዚያ ይልቅ በዳዊት ጥሩ ባሕርያት ተማርኮ የእርሱ ወዳጅ ለመሆን ቃል ኪዳን አደረገ። እንዲህ የመሰለው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ወዳጅነት በዛሬው ጊዜ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ያሉትን ሰዎች የሚገነባና የሚያበረታታ ነው።​—⁠23:​16-18

32 ከባሏ ጋር ወደ ይሖዋ የአምልኮ ቦታ ዘወትር ትሄድ የነበረችው ሐናም ለሴቶች ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች። አዘውትራ የምትጸልይና ትሑት ሴት የነበረች ከመሆኑም በላይ የገባችውን ቃል ለመፈጸምና ይሖዋ ላደረገላት ደግነት ያላትን አድናቆት ለማሳየት ስትል ከወንድ ልጅዋ ጋር የነበራትን ትስስር እርግፍ አድርጋ ሠውታለች። ልጅዋ ዕድሜውን ሙሉ በይሖዋ አገልግሎት ፍሬያማ ሲሆን መመልከቷ ለእርሷ በእርግጥ አስደሳች ነበር። (1:​11, 21-23, 27, 28) ከዚህም በተጨማሪ የታዛዥነትንና የአስተዋይነትን ባሕርይ በማንጸባረቅ የዳዊትን ቀልብ የሳበችው አቢጋኤል የተወችው ምሳሌም አለ። ከጊዜ በኋላም ዳዊት ሚስቱ አድርጎ ወስዷታል።​—⁠25:​32-35

33 ‘የይሖዋ ቅቡዕ’ የነበረውና በኋላ ከእሱ መንገድ ያፈገፈገው ሳኦል በምድረ በዳ ያሳድደው በነበረበት ወቅት ባቀነባበረው መዝሙር ውስጥ ዳዊት ለይሖዋ ያለው ፍቅር ልብ በሚነካ ሁኔታ ተገልጿል። (1 ሳሙ. 24:​6፤ መዝ. 34:​7, 8፤ 52:​8፤ 57:​1, 7, 9) እንዲሁም ዳዊት ዕብሪተኛውን ጎልያድን በተጋፈጠ ጊዜ የይሖዋን ስም አስገራሚ በሆነ መንገድ አስቀድሷል! “በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ . . . ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፤ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደለ ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” (1 ሳሙ. 17:​45-47) ደፋርና ታማኝ የይሖዋ ‘ቅቡዕ’ የነበረው ዳዊት ይሖዋ የምድር ሁሉ አምላክና እውነተኛው የመዳን ምንጭ እርሱ ብቻ መሆኑን አጉልቶ አሳይቷል። (2 ሳሙ. 22:​51) ሁላችንም ይህን ደፋር ምሳሌ የምንከተል እንሁን!

34 አንደኛ ሳሙኤል ስለ አምላክ መንግሥት ዓላማ አፈጻጸም ምን የሚናገረው ነገር አለ? ይህ ጥያቄ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ጉልህ ቦታ ወደተሰጠው ነገር ይወስደናል! ምናልባትም ስሙ “የተወደደ” የሚል ትርጉም ያለውን ዳዊትን የምናገኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ዳዊት በይሖዋ ዘንድ የተወደደ ከመሆኑም በላይ ለይሖዋ ‘እንደ ልቡ’ የሆነ በእስራኤል ንጉሥ ለመሆን ብቃት ያለው ሰው ሆኖ ተገኝቷል። (1 ሳሙ. 13:​14) በመሆኑም ዘፍጥረት 49:​9, 10 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ያዕቆብ ከተናገረው በረከት ጋር በሚስማማ መንገድ መንግሥቱ ወደ ይሁዳ ነገድ ተላልፏል። እንዲሁም የሰው ሁሉ መታዘዝ ለእርሱ የሆነለት ገዥ እስኪመጣ ድረስ ንግሥናው በይሁዳ ነገድ ተወስኖ ይቆያል።

35 ከዚህም በተጨማሪ የዳዊት ስም በቤተ ልሔም ከተወለደውና በዳዊት የትውልድ ሐረግ ከተገኘው ከመንግሥቱ ዘር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። (ማቴ. 1:​1, 6፤ 2:​1፤ 21:​9, 15) ይህም ሰው በክብር ከፍ የተደረገው “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር” የሆነውና “የዳዊት ሥርና ዘር . . . የሚያበራም የንጋት ኮከብ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ራእይ 5:​5፤ 22:​16) ይህ “የዳዊት ልጅ” በመንግሥት ሥልጣኑ ላይ ተቀምጦ የአምላክን ጠላቶች ድምጥማጣቸውን በማጥፋትና በመላው ምድር ላይ የይሖዋ ስም እንዲቀደስ በማድረግ እንደ አያቱ ደፋርና ቆራጥ መሆኑን ያሳያል። በዚህ የመንግሥቱ ዘር ላይ ያለን እምነት ምንኛ ጠንካራ ነው!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ