“ ዝም ማለት አንችልም”
1 ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከቱን ሥራ በቅርብ ሆኖ እየተከታተለው ነው። (ማቴ. 28:20፤ ማር. 13:10) ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉት ንቁ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በ234 አገሮች ውስጥ ምሥክርነት እየሰጡ ቢሆንም ሥራው ተጠናቋል ብለን ማሰብ አይኖርብንም። አምላክ በቃ ብሎ ሥራውን እስከሚያስቆምበት ጊዜ ድረስ ስለተማርናቸው ነገሮች “ከመናገር ዝም ማለት አንችልም።”—ሥራ 4:20
2 በአምላክ መንፈስ ተማመኑ:- ሰይጣን ከባድ ተጽእኖ በማድረስ እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ይሞክራል። (ራእይ 12:17) ፍጹም ያልሆነው ሥጋችንም ብዙ ችግር ይፈጥርብናል። እንዲህ ያሉት ነገሮች በጣም አስፈላጊ ከሆነው የስብከት ሥራ በቀላሉ ትኩረታችንን ሊወስዱት ቢችሉም በይሖዋ ከታመንን መንፈሱ ማንኛውንም መሰናክል እንድንወጣ ይረዳናል።
3 የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ከባድ ስደት በደረሰበት ጊዜ ወንድሞች ቃሉን በድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ አምላክ እንዲረዳቸው ጸልየዋል። ይሖዋም መንፈሱን በላያቸው በማፍሰስ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ ለመቀጠል የሚያስፈልጋቸውን ቅንዓት እንዲያሳዩና ቁርጥ አቋም እንዲይዙ በመርዳት ለጸሎታቸው መልስ በመስጠቱ ወንድሞች ምሥራቹን ያለማቋረጥ በድፍረት ማወጃቸውን ቀጥለዋል።—ሥራ 4:29, 31፤ 5:42
4 የሰዎችን ትችት አትፍሩ:- ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት ወይም የሚካሄድብን ስም የማጥፋት ዘመቻ እንድንፈራ ያደርገን ይሆናል። ሆኖም ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ለአይሁድ የፍርድ ሸንጎ በድፍረት የተናገሩትን በሥራ 5:29-32 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ታሪክ አስታውሱ። የሕግ መምህር የሆነው ገማልያል እንደተናገረው የአምላክ ሥራ ሊጨናገፍ አይችልም። በእኛ ኃይል የሚሠራ ሥራ አይደለም። ይህ ታላቅ ሥራ የአምላክ ድጋፍ ያለውና እርሱ ብቻ ሊፈጽመው የሚችለው ሥራ ነው!—ዘካ. 4:6
5 ምሥራቹን በቅንዓት እንድናውጅ የሚረዳንን መንፈሱን እንዲሰጠን ይሖዋን ዘወትር እንለምን። እኛም እንደ ኤርምያስ የመንግሥቱ መልእክት በአጥንቶቻችን ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ነው ለማለት እንችል ዘንድ ምኞታችን ነው። (ኤር. 20:9) ዝም ማለት አንችልም!