ዓይናፋርነት ያጠቃሃልን?
1 አንድ ሕፃን ከእናቱ ወይም ከአባቱ ኋላ ሆኖ አሾልቆ ሲመለከተን ብናይ ብዙም አይገርመንም። በልጅነት ዕድሜ ዓይናፋር መሆን የተለመደ ነው። ሌላው ቀርቶ ብዙ ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎችም እንኳ በተፈጥሮአቸው ዓይናፋር ናቸው። ዓይናፋርነት በአገልግሎት እንቅስቃሴህ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
2 ዓይናፋርነትን መቋቋም:- ‘ለተሰወረው የልብ ሰው’ ትኩረት መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥ. 3:4) ለይሖዋና ለሰዎች ያለህን ፍቅር አጠንክር። እንድትሰብክ የተሰጠህን ትእዛዝ መፈጸምህ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የሚገለጸውን ፍቅር ለማሳየት ከሚያስችሉህ አጋጣሚዎች አንዱ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አምነህ መቀበል ይኖርብሃል። የግል ጥናት የማድረግና በስብሰባዎች ላይ የመገኘት ጥሩ ልማድ አዳብር። ያለብህን ችግር ለይተህ በመጥቀስ አዘውትረህ የይሖዋን እርዳታ በጸሎት ጠይቅ። ጠንካራ እምነት መገንባትና በይሖዋ መታመን በራስ የመተማመን ስሜት እንድታዳብርና ‘የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሃት እንድትነግር ከፊት ይልቅ ድፍረት’ ይሰጥሃል።—ፊልጵ. 1:14
3 ብቁ አይደለሁም የሚለውን ስሜት ተዋጋ። ጢሞቴዎስ እንዲህ ማድረግ አስፈልጎት የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ “ማንም ታናሽነትህን አይናቀው” በማለት ካበረታታው በኋላ ‘እግዚአብሔር የኃይል . . . እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና’ ሲል አሳስቦታል። (1 ጢሞ. 4:12፤ 2 ጢሞ. 1:7) በሙሉ ልብህ በአምላክ በመታመን ለመሻሻል ጥረት ካደረግህ ይሖዋ ጢሞቴዎስን ሙሉ በሙሉ እንደተጠቀመበት ሁሉ በአንተም ሊጠቀም ይችላል።—መዝ. 56:11
4 ዓይናፋርነቷ ተቃዋሚ ባሏን በጣም እንድትፈራው አድርጓት የነበረች አንዲት እህት እንደ ማቴዎስ 10:37 ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰሏ ጠቅሞአታል። ሳትሰለች በመጣሯ አገልግሎቷ ቀላል ሆነላት። ውሎ አድሮም ባሏ፣ እናቷና ወንድሞቿ እውነትን ተቀበሉ!
5 ዝግጅት የግድ አስፈላጊ ነው:- ለአገልግሎቱ የተሟላ ዝግጅት ካደረግክ በራስ የመተማመን ስሜትህ ይበልጥ ይጨምራል። ከማመራመር መጽሐፍ ወይም ቀደም ብለው ከወጡት የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞች ላይ ቀለል ያለ አቀራረብ ምረጥና በደንብ አጥናው። ከዚያም አቀራረቡን ተለማመድ። በራስህ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ጭንቀት ከመፍጠር ይልቅ አዎንታዊ በሆነ መንገድ አስብ። ከሌሎች ጋር አብረህ በመሥራት ድፍረትን አዳብር። በር ላይ የምታገኛቸው አብዛኞቹ ሰዎች ልክ እንደ አንተው ዓይናፋሮች መሆናቸውን አትርሳ። እያንዳንዱ ሰው የመንግሥቱ መልእክት ያስፈልገዋል።
6 ዓይናፋርነት የሚያጠቃህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ራስህን እስካቀረብክ ድረስ ይሖዋ የምሥራቹ ውጤታማ ሰባኪ እንድትሆን ስለሚረዳህ በአገልግሎቱ ደስታ ታገኛለህ።—ምሳሌ 10:22