ከይሖዋና ከልጁ ጋር በደስታ ተባበሩ
በዓመቱ ውስጥ የላቀ ግምት የሚሰጠው በዓል መጋቢት 28 ይከበራል
1 መጋቢት 28, 2002 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የጌታ እራትን በዓል በማክበር ከይሖዋና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያስደስት አንድነት እንዳለን እናሳያለን። በዚያ በጣም ልዩ በሆነ በዓል ላይ የቅቡዓን ክርስቲያን ቀሪዎች ከሌሎች የመንግሥቱ ወራሾች፣ ከአብና ከልጁ ጋር ባላቸው ልዩ “ኅብረት” ይደሰታሉ። (1 ዮሐ. 1:3፤ ኤፌ. 1:11, 12) በሚልዮን የሚቆጠሩት “ሌሎች በጎች” ከይሖዋና ከልጁ ጋር አንድ በመሆን በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ የአምላክን ሥራ ለመፈጸም ባገኙት ግሩም መብት ላይ ያሰላስላሉ!—ዮሐ. 10:16
2 የተቀራረበ ዝምድና በመመሥረት አብሮ መሥራት፦ ይሖዋና ኢየሱስ ሁልጊዜ አስደሳች የሆነ አንድነት አላቸው። ሰው ከመፈጠሩ በፊት ሕልቆ መሳፍርት ለሌለው ዘመን ተቀራርበው ኖረዋል። (ሚክ. 5:2) በዚህም የተነሳ በሁለቱ መካከል ጥልቅ የሆነ የመዋደድ ትስስር ዳብሯል። ይህ የበኩር ልጅ ሰው ከመሆኑ በፊት በነበረው ሕይወት በጥበብ ተመስሎ እንዲህ ሊል ችሏል:- “ዕለት ዕለት [ይሖዋን] ደስ አሰኘው ነበርሁ፤ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ።” (ምሳሌ 8:30) ቁጥር ስፍር ለሌላቸው ዓመታት የፍቅር ምንጭ ከሆነው አካል ጋር ተቀራርቦ መኖር በአምላክ ልጅ ላይ ጥልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል!—1 ዮሐ. 4:8
3 ይሖዋ የሰው ልጅ መቤዠት እንደሚያስፈልገው በመገንዘብ ለሰው ልጆች ልዩ ፍቅር የነበረውን አንድያ ልጁን በመላክ ለሰው ልጅ መዳን ብቸኛ አማራጭ የሆነው ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲከፈል አድርጓል። (ምሳሌ 8:31) ይሖዋና ልጁ አንድን ዓላማ ዳር ለማድረስ ተባብረው እንደሚሠሩ ሁሉ እኛም የአምላክን ፈቃድ በደስታ በማድረግ ከእነርሱ ጋርና እርስ በርሳችን ጠንካራ በሆነ የፍቅር ማሰሪያ ተሳስረን መኖራችንን እንቀጥላለን።
4 ከልብ አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየት፦ በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘትና በጥሞናና በአክብሮት በማዳመጥ ይሖዋ ላሳየን ፍቅርና ልጁ ለእኛ ሲል ለከፈለው መሥዋዕትነት ከልብ የምናመሰግን መሆናችንን ልናሳይ እንችላለን። በበዓሉ ላይ ስለ ኢየሱስ የፍቅር ምሳሌ፣ ቤዛውን ለማቅረብ እስከ ሞት ድረስ ስላሳየው ታማኝነትና በተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ስላለው ንጉሣዊ አገዛዝ እንዲሁም መንግሥቱ ለሰው ዘር ስለሚያመጣቸው በረከቶች ጎላ ያለ ማብራሪያ ይሰጣል። በተጨማሪም “በእውነት ውስጥ አብረን የምንሠራ” እንደመሆናችን መጠን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ተስማምተን በቅንዓት በመሥራት እምነታችንን ሁልጊዜ እንድናሳይ ማሳሰቢያ ይሰጠናል።—3 ዮሐ. 8 NW፤ ያዕ. 2:17
5 ሌሎች ከእኛ ጋር እንዲካፈሉ መርዳት፦ የሽማግሌዎች አካላት በአገልግሎት ክልላቸው ውስጥ ያሉት አገልግሎት ያቆሙ ምሥክሮች በሙሉ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ ለማበረታታት ልዩ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ማቴ. 18:12, 13) ማንንም ሳትረሱ ሁሉንም በግለሰብ ደረጃ መጋበዝ ትችሉ ዘንድ የሁሉንም ስም መዝግባችሁ ያዙ።
6 በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የምትፈልጓቸው ሌሎች የምታውቋቸው ሰዎች አሉ? ቅድሚያውን ወስዳችሁ ለበዓሉ ያላቸው አድናቆት እንዲቀሰቀስ አድርጉ። ሞቅ ያለ ግብዣ አቅርብላቸው እንዲሁም ተፈላጊ እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርግ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንንና ሌሎች ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን እንዲሁም የቤተሰባችንን አባላትና የምናውቃቸውን ሰዎች በዚህ ከሁሉ በላቀ የዓመቱ ክንውን ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ የሚቻለንን ሁሉ እናድርግ። ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ‘ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጠው ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ እውቀት’ ለመማር ለሚፈልግ ሰው ሁሉ የተዘረጉ ናቸው። (ፊልጵ. 3:8) በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ እምነት የሚያሳድሩ ሁሉ የተረጋገጠ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘት ይችላሉ።—ዮሐ. 3:16
7 የመታሰቢያው በዓል ቅን በሆኑ ሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ አቅልላችሁ አትመልከቱ። ከሁለት ዓመት በፊት በፓፑዋ ኒው ጊኒ ደሴት 11 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመገኘት ማዕበል በሚያናውጠው ባህር ላይ በትንሽ ጀልባ ለ17 ሰዓታት ተጉዘዋል። ለምን? “የክርስቶስን መታሰቢያ በዓል ከመሰል የይሖዋ አምላኪዎች ጋር አንድ ላይ ማክበር ስለፈለግን ነው፤ ስለዚህ ጉዞው የሚያስቆጭ አልነበረም።” እነዚህ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ያሳዩትን ቅንዓትና ከይሖዋ፣ ከልጁና ከክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር ጋር አስደሳች ሕብረት መፍጠር በመቻላቸው ያሳዩትን አድናቆት እስቲ አስቡ!
8 ፍላጎት ያሳዩ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ግብዣ አቅርቡላቸው። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እንዲገኙና እየተማሩት ያሉትን እውነት ለሌሎች እንዲያካፍሉ አበረታቷቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ‘በብርሃን እንዲመላለሱና’ ‘እውነትን እንዲያደርጉ’ እርዷቸው። (1 ዮሐ. 1:6, 7) ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዲመሠርቱና ፈቃዱን በአንድነት ለማድረግ ላገኙት ልዩ መብት ያላቸውን አድናቆት ማሳደጋቸውን እንዲቀጥሉ እገዛ አድርጉላቸው።
9 ‘በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብሮ እየተጋደሉ፣ በአንድ መንፈስ’ በደስታ አንድ መሆን እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው! (ፊልጵ. 1:27, 28) ለይሖዋና ለልጁ አመስጋኝ በመሆን መጋቢት 28 በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ተገናኝተን የምናሳልፈውን አስደሳች ወቅት በጉጉት እንጠባበቅ!—ሉቃስ 22:19