ቤዛውን በአድናቆት ማሰብ
1, 2. ቤዛውን በአድናቆት እንድናስብ የሚያደርጉን ምን ምክንያቶች አሉ?
1 በዓለም ዙሪያ ያሉ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የሞቱን መታሰቢያ ለማክበር ቅዳሜ፣ መጋቢት 22, 2008 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ይሰበሰባሉ። (ሉቃስ 22:19፤ 1 ቆሮ. 11:23-26) እንዲህ እንድናደርግ የሚያነሳሳን ከዛሬ 1,975 ዓመት በፊት ለተፈጸመ አንድ ክንውን ያለን ጥልቅ አድናቆት ነው። ኢየሱስ ፍጹም አቋሙን ጠብቆ በመከራ እንጨት ላይ ተሠቃቶ በመሞት ለሰይጣን ስድብ የማያዳግም ምላሽ ሰጥቷል። ኢየሱስ ይህን በማድረግ የአባቱን ስም አስቀድሷል።—ኢዮብ 1:11፤ ምሳሌ 27:11
2 የፈሰሰው የኢየሱስ ደም፣ አዲሱ ቃል ኪዳን ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ያደረገ ሲሆን ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች የአምላክ ልጆች ሆነው እንዲቆጠሩ አስችሏል። እነዚህ የአምላክ ልጆች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር አብረው የመግዛት ተስፋ አላቸው። (ኤር. 31:31-34፤ ማር. 14:24) ከዚህ በተጨማሪም ኢየሱስ ራሱ ለኒቆዲሞስ እንደገለጸለት፣ አምላክ በጣም የሚወደውን ልጁን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ለሰው ልጆች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው በግልጽ አሳይቷል።—ዮሐ. 3:16
3. በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚጠቀሙት እንዴት ነው?
3 ሌሎችን ጋብዝ:- በጥር ወር የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ላይ የምናውቃቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር እንድንይዝና እያንዳንዳቸውን በግለሰብ ደረጃ እንድንጋብዛቸው ሐሳብ ተሰጥቶን ነበር። ታዲያ ባወጣኸው ስም ዝርዝር መሠረት ሰዎችን መጋበዝ ጀምረሃል? ከመጋቢት 1, 2008 ጀምሮ ሰዎችን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዘመቻ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመካፈል ዝግጅት አድርገሃል? በበዓሉ ላይ የሚገኙ ሰዎች በቤዛው ላይ እምነት እንዲያሳድሩ የሚያደርግ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት የሚያዳምጡ ሲሆን እንዲህ ያለው እምነት ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።—ሮሜ 10:17
4. በመታሰቢያው በዓል ላይ ቀደም ብለን መገኘት ያለብን ለምንድን ነው?
4 ይህን ልዩ ግብዣ ተቀብለው ለሚመጡ ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ለማድረግ እንዲቻል፣ ሁኔታችን የሚፈቅድልን ሁሉ ቀደም ብለን ወደ አዳራሹ ለመድረስ እቅድ ማውጣት ይገባናል። በመታሰቢያው በዓል ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሰብሳቢዎች ስለሚገኙ ለአዲሶችም ሆነ አልፎ አልፎ በስብሰባ ላይ የመገኘት ልማድ ላላቸው ሰዎች የተለየ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ነው።
5. ለበዓሉ ልብህን ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?
5 ልብህን አዘጋጅ:- ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2008 እና የ2008 ቀን መቁጠሪያ ከመጋቢት 17 ጀምሮ የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ይዘዋል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ የተፈጸሙ ወሳኝ ክንውኖችን መመርመርህ ለመታሰቢያው በዓል ልብህን እንድታዘጋጅ ይረዳሃል። (ዕዝራ 7:10 የ1954 ትርጉም) በእነዚህ ዘገባዎች ላይ በጸሎት ማሰላሰልህ ይሖዋና ልጁ ቤዛውን በማዘጋጀት ላሳዩህ ፍቅር ያለህን አድናቆት ይጨምርልሃል።—መዝ. 143:5
6. ለቤዛው ዝግጅት ያለንን አድናቆት ከፍ ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
6 የመታሰቢያው በዓል እየቀረበ በመጣ መጠን ለዚህ ልዩ በዓል ትኩረት ሰጥተን ራሳችንንም ሆን ሌሎችን እናዘጋጅ። ቤዛውን በአድናቆት ማሰባችን ከይሖዋና ከልጁ ጋር ያለንን ወዳጅነት ያጠናክርልናል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) በተጨማሪም የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ለሌሎች በማሳየት ረገድ ይሖዋንና ልጁን እንድንመስል ያነሳሳናል።—1 ዮሐ. 4:11