ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
የተወደዳችሁ የይሖዋ አገልጋዮች
የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የሆነውን የይሖዋን ስም መሸከማችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ይህ ስም ዘላለማዊ፣ የማይጠፋና ተወዳዳሪ የሌለው ነው። ስሙን የመሸከም መብት የሰጠን ይሖዋ ነው፤ በተለይ ከ1931 ጀምሮ በዚህ ልዩ ስም የመጠራት መብት አግኝተናል። (ኢሳ. 43:10) የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን በመጠራታችን ይህ ነው የማይባል ኩራት ይሰማናል።
ዲያብሎስ የአምላክ ስም እንዳይታወቅ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በእሱ ቁጥጥር ሥር ያሉት ብሔራት በይሖዋ ስም ይሳለቃሉ። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው ታላቂቷ ባቢሎን ለመለኮታዊው ስም ጥላቻ ያላት ከመሆኑም በላይ ስሙን ከበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ እንዲወጣ አድርጋለች። ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ ስለ አባቱ ስም መጀመሪያ ላይ በመጥቀስ ስሙን ከፍ ከፍ አድርጓል። “እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ’” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 6:9) በሌላ ጊዜ ደግሞ ለአባቱ ከልብ በመነጨ ስሜት ጸሎት ባቀረበበት ወቅት “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 17:6) እኛም ኢየሱስ የተወውን ግሩም ምሳሌ በመከተል የይሖዋን ስም በምድር ዙሪያ በትጋት ለማወጅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።
‘ምሥራቹን በሚገባ መሥክሩ’ የሚለው የ2009 የዓመት ጥቅስ አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ እንድናከናውን አበረታቶናል። (ሥራ 20:24) ይሖዋ ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ያደረግነውን ጥረት በእጅጉ እንደባረከልን ምንም ጥርጥር የለውም። ለይሖዋ ስም ክብርና ውዳሴ ለማምጣት በዓለም ዙሪያ እጅግ አስደናቂ ምሥክርነት የመስጠት ሥራ ተከናውኗል። በምድር ዙሪያ የሚገኙ 7,313,173 (አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር) አስፋፊዎች ድምፃቸውን አስተባብረው ለሰዎች ሁሉ ሰብከዋል፤ እንዲሁም በየዕለቱ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ የሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችን አስተምረዋል። በክርስቶስ የሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 18,168,323 የሚያህሉ ሰዎች መገኘታቸው ይህ ክፉ ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት የይሖዋን ስም በመጥራቱ ሥራ የሚተባበሩ ገና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚኖሩ ተስፋ ይሰጣል።
ይሖዋ እስከፈቀደው ጊዜ ድረስ በክልላችን የሚገኙ ሰዎችን አግኝተን ለማነጋገር የሚያስችሉንን ዘዴዎች ሁሉ በመጠቀም የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥላለን። (ማቴ. 24:14፤ ማር. 13:10) ምሥክርነት የምንሰጠው ከቤት ወደ ቤት በማገልገልም ይሁን በመንገድ ላይ፣ በደብዳቤ፣ በስልክ ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከር የይሖዋን ስምና ዓላማ በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች ለማሳወቅ ጥረት እናደርጋለን።
ይሖዋ በቅርቡ ስሙን ለማስቀደስ እርምጃ ይወስዳል ብለን እንድናምን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን። (ሕዝ. 36:23) ስሙን የሚያጠፉ ሁሉ ጸጥ የሚሉበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። ይህ ቀን የይሖዋን ስም ላሳወቁና ሉዓላዊ ገዥነቱን ለደገፉ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እንዴት ያለ ክብራማ ቀን ይሆናል!
በ2009 በአብዛኛው የዓለም ክፍል በተደረገው “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” በተባለው የአውራጃና የብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ፍቅራዊ አሳቢነት በግልጽ ታይቷል። የይሖዋን ቀን ነቅቶ የመጠበቅን አስፈላጊነት ይበልጥ እንድንገነዘብ ያደረገው ይህ የአውራጃ ስብሰባ በቲኦክራሲያዊ ታሪካችን ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው።—ማር. 13:37፤ 1 ተሰ. 5:1, 2, 4
በእርግጥም ይሖዋ ጥሩ የሆነ አምላካችን ነው፤ ልባችንን በደስታ ሞልቶታል። በለመለመ መስክ ያሳርፈናል፤ እንዲሁም ውኃ ወዳለበት የእረፍት ቦታም ይመራናል።—መዝ. 23:1, 2፤ 100:2, 5
በመጪዎቹ ወራት በመንግሥቱ አገልግሎት በትጋት መካፈላችሁን ስትቀጥሉ የይሖዋ በረከት ምንጊዜም እንደማይለያችሁ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን!
ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ሞቅ ያለው ክርስቲያናዊ ፍቅራችን ይድረስ፣
ወንድሞቻችሁ
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል