ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ የሆነው ሥራ
1. ለአገልግሎት ያለን ጥልቅ አድናቆት ምን ዓይነት መሥዋዕቶችን እንድንከፍል ያነሳሳናል?
1 ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ጥሪታችንን ለአገልግሎት እንድናውል በየጊዜው ማበረታቻ የሚሰጠን ለምንድን ነው? ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሌላ ሥራ ስለሌለ ነው! አገልግሎት በሚያስገኘው ከፍተኛ ጥቅም ላይ ማሰላሰላችን በማይደገመው በዚህ ሥራ ላይ የመካፈል ፍላጎታችን እንዲጨምር ይረዳናል።—ሥራ 20:24
2. የስብከቱ ሥራችን የይሖዋን ታላቅ ስም የሚያስቀድሰው እንዴት ነው?
2 የይሖዋን ስም ያስቀድሳል፦ የስብከቱ ሥራ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራው የይሖዋ መንግሥት የሰው ልጆች ያቋቋሟቸውን መንግሥታት በሙሉ እንደሚተካና ለሰው ዘር ችግሮች በሙሉ መፍትሔ እንደሚያመጣ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ማቴ. 6:9, 10) ከበሽታም ሆነ ከሞት ሊታደገን የሚችለው ብቸኛ አካል ይሖዋ እንደሆነ በመግለጽ ይሖዋን ያስከብራል። (ኢሳ. 25:8፤ 33:24) እኛም የይሖዋን ስም ስለምንሸከም መልካም ምግባራችንንና ቅንዓታችንን የሚመለከቱ ሰዎች እሱን ለማክበር ሊነሳሱ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 2:12) የሉዓላዊው ጌታ የይሖዋ ስም በመላው ምድር ላይ እንዲታወቅ ማድረግ እንዴት የሚያስደስት ነው!—መዝ. 83:18 NW
3. ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ምን በረከቶችን ያገኛሉ?
3 የሰዎችን ሕይወት ያድናል፦ ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።” (2 ጴጥ. 3:9) ይሁን እንጂ ሰዎች የሚያስተምራቸው ሳይኖር በይሖዋ ፊት ተገቢ ስለሆነውና ተገቢ ስላልሆነው ምግባር እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? (ዮናስ 4:11፤ ሮም 10:13-15) ሰዎች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ ጎጂ የሆኑ ልማዶችን ስለሚተዉ ሕይወታቸው እየተሻሻለ ይሄዳል። (ሚክ. 4:1-4) ከዚህም በላይ አስደሳች የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይኖራቸዋል። በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በትጋት መካፈላችን የእኛንም ሆነ የሚሰሙንን ሰዎች ሕይወት ያድናል። (1 ጢሞ. 4:16) ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ በሆነው በዚህ ሥራ ውስጥ እንዴት ያለ የተከበረ ድርሻ አለን!
4. ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት መካፈል ያለብን ለምንድን ነው?
4 በቅርቡ ታላቁ መከራ በዚህ ዓመፀኛ ዓለም ላይ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣል። ከይሖዋ ጎን የሚቆሙ ሁሉ በሕይወት ይተርፋሉ። በመሆኑም የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ተልእኮ በዛሬው ጊዜ ከምንም በላይ አጣዳፊ፣ አስፈላጊና ጠቃሚ የሆነ ሥራ ነው። እንግዲያው በሕይወታችን ውስጥ ለዚህ ሥራ ከምንም ነገር በላይ ቀዳሚውን ቦታ እንስጥ!—ማቴ. 6:33