በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ለሚያቀርቡ ወንድሞች የተሰጠ መመሪያ
ከዚህ የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ጀምሮ ክፍል አቀራረብን በሚመለከት በአገልግሎት ስብሰባ ፕሮግራም ላይ የሚወጣው መመሪያ ግልጽና ያልተወሳሰበ እንዲሆን ተደርጓል። ከዚህ በታች የቀረበው መመሪያና ማሳሰቢያ የተዘጋጀው በግንቦት 2009 የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ላይ “ለአገልግሎት ስብሰባ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ በወጣው ትምህርት ላይ የተደረጉትን አንዳንድ ለውጦች ለማስገንዘብና ትምህርቱን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ነው።
◼ ንግግር፦ እንዲህ ያሉ ክፍሎች፣ በመመሪያው ላይ የተጠቀሰውን ጽሑፍ መሠረት በማድረግ በንግግር የሚቀርቡ ሲሆን አድማጮችን አያሳትፉም። ተናጋሪው ለጉባኤው ይበልጥ ጠቃሚ በሆኑ ነጥቦች ላይ ማተኮር ይኖርበታል።
◼ ጥያቄና መልስ፦ ይህ ክፍል በአብዛኛው የሚቀርበው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በሚጠናበት መንገድ ሲሆን በጣም አጠር ያለ መግቢያና መደምደሚያ ይኖረዋል፤ እንዲሁም በሁሉም አንቀጾች ላይ ጥያቄ መጠየቅ ይኖርበታል። ክፍሉን የሚያቀርበው ወንድም ብዙ ሐሳብ መስጠት የለበትም። ጊዜ በፈቀደ መጠን ቁልፍ የሆኑ ጥቅሶች ሊነበቡ ይችላሉ። መመሪያ እስካልተሰጠ ድረስ አንቀጾቹ መነበብ የለባቸውም።
◼ ውይይት፦ ይህ ክፍል የሚቀርበው በንግግር ሲሆን አልፎ አልፎ አድማጮች ሐሳብ እንዲሰጡ ይደረጋል። ክፍሉ በንግግር ብቻ የሚቀርብ አይደለም፤ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ በጥያቄና መልስ መቅረብም የለበትም።
◼ ሠርቶ ማሳያዎችና ቃለ ምልልሶች፦ ሠርቶ ማሳያ እንዲቀርብ የሚያዝ መመሪያ በሚኖርበት ጊዜ ክፍሉን የወሰደው ወንድም ሠርቶ ማሳያውን የማዘጋጀት ኃላፊነት አለበት፤ ሠርቶ ማሳያውን ማቅረብ ያለበት እሱ ራሱ አይደለም። ሠርቶ ማሳያውን እንዲያቀርቡለት የሚመርጣቸው ወንድሞችና እህቶች ምሳሌ የሚሆኑ እንዲሁም ብቃት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፤ የሚቻል ከሆነ በጣም ቀደም ብሎ ሠርቶ ማሳያውን በተመለከተ ከእነሱ ጋር መነጋገር ይኖርበታል። አዲሶችና ተሞክሮ የሌላቸው አስፋፊዎች መድረክ ላይ እንዲወጡ አጋጣሚ ለመስጠት ሲባል ብቻ የመንግሥቱ ሥራ የሚካሄድበትን መንገድ በሠርቶ ማሳያ እንዲያሳዩ እንዲህ ያሉ ግለሰቦችን መጠቀም ተመራጭ አይደለም፤ እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቹን የቤት ባለቤት ሆነው እንዲሠሩ ማድረግ ይቻላል። ወንድሞችና እህቶች ሠርቶ ማሳያ በሚያቀርቡበት ጊዜ ፊታቸውን ወደ አድማጮች ማዞር ይኖርባቸዋል። ቃለ ምልልስ የሚደረግላቸው ደግሞ በተቀመጡበት ሳይሆን መድረክ ላይ ወጥተው ሐሳብ መስጠት ይኖርባቸዋል። ሠርቶ ማሳያዎችና ቃለ ምልልሶች አስቀድሞ ልምምድ ሊደረግባቸው ይገባል። አንድ ወንድም ሰዓቱ እንደሄደ ካስተዋለ ንግግሩን ማሳጠር አለበት እንጂ ሠርቶ ማሳያዎቹን ወይም ቃለ ምልልሶቹን መሰረዝ የለበትም። የጉባኤ አገልጋዮች በሠርቶ ማሳያዎቹ ወይም በቃለ ምልልሶቹ ላይ የሚሳተፉትን ወንድሞችና እህቶች ከመምረጣቸው በፊት የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪውን ወይም ሌላ ሽማግሌን ማማከር ይኖርባቸዋል።
ለየት ያለ ክፍል በሚኖርበት ወቅትና ክፍሉ ስለሚቀርብበት መንገድ የተለየ መመሪያ በሚሰጥበት ጊዜ መመሪያውን በጥብቅ መከተል ይገባል። ወንድሞች የአገልግሎት ስብሰባ ክፍሎችን ከላይ በተገለጸው መመሪያ መሠረት በማቅረብ የአገልግሎት ስብሰባው “በአግባብና በሥርዓት” እንዲከናወን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።—1 ቆሮ. 14:40