በአንድ ወቅት የዘወትር አቅኚ ነበርክ?
1. ብዙዎች ምን መብት አግኝተዋል? ሆኖም አንዳንዶች ምን ማድረግ አስፈልጓቸዋል?
1 ባለፉት ዓመታት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን ‘ምሥራቹን የማስተማርና የማወጅ’ መብት አግኝተዋል። (ሥራ 5:42) ሆኖም አንዳንዶች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ አቅኚነታቸውን ማቋረጥ ግድ ሆኖባቸዋል። በአንድ ወቅት የዘወትር አቅኚ ከነበርክ እንደገና አቅኚ መሆን ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ አሁን ያለህበትን ሁኔታ መርምረሃል?
2. ከዚህ በፊት አቅኚ የነበሩ ወንድሞችና እህቶች አሁን ያሉበትን ሁኔታ መመርመር ያለባቸው ለምንድን ነው?
2 ሁኔታዎች ይለወጣሉ፦ አቅኚነትን እንድታቆም ያደረገህ ሁኔታ አሁን ተወግዶ ይሆናል። ለምሳሌ አቅኚነት ያቆምከው ወርሃዊ የሰዓት ግብህን ማሟላት ስላልቻልክ ከሆነ አሁን የሰዓት ግቡ ከ90 ወደ 70 ዝቅ በማለቱ አቅኚነትህን መቀጠል ትችል ይሆን? አቅኚነት ስታቆም የነበረብህ የሥራ ወይም የቤተሰብ ኃላፊነት አሁን ቀንሶ ይሆን? በጤንነት ምክንያት አቅኚነት ያቆሙ አንዲት እህት በ89 ዓመታቸው እንደገና አቅኚ ሆነዋል። እኚህ እህት ለአንድ ዓመት ያህል ሆስፒታል ባለመግባታቸው የጤንነታቸው ሁኔታ እንደገና አቅኚ ለመሆን እንደሚያስችላቸው ተሰምቷቸዋል።
3. አንድ ሰው አቅኚነቱን እንዲቀጥል ለማድረግ የቤተሰቡ አባላት መተባበር የሚችሉት እንዴት ነው?
3 ከዚህ በፊት አቅኚ ሆነህ አታውቅ ይሆናል፤ ሆኖም ከቤተሰብህ አባላት አንዱ በዕድሜ የገፉ ወላጆችን ወይም ሌላ የቤተሰብ አባልን ለመንከባከብ ሲል አቅኚነቱን አቁሞ ይሆናል። (1 ጢሞ. 5:4, 8) ከሆነ አቅኚ የነበረውን የቤተሰብ አባል ለመርዳት አንተም ሆንክ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ማድረግ የምትችሉት ተጨማሪ ነገር ይኖር ይሆን? በጉዳዩ ላይ ለምን አትወያዩም? (ምሳሌ 15:22) የቤተሰቡ አባላት ከመካከላቸው አንዱ አቅኚ መሆን እንዲችል ለማድረግ የሚተባበሩ ከሆነ ሁሉም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ሊሰማቸው ይገባል።
4. በአሁኑ ወቅት አቅኚ መሆን ቢያቅትህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
4 አሁን ያለህበት ሁኔታ እንደገና አቅኚ እንድትሆን የማያስችልህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። አቅኚ ለመሆን ፈቃደኝነቱ ስላለህ ብቻ ይሖዋ ይደሰትብሃል። (2 ቆሮ. 8:12) ከዚህ በፊት በአቅኚነት ያዳበርከውን ችሎታ አሁንም በአገልግሎት ላይ ተጠቀምበት። እንደገና አቅኚ የመሆን ፍላጎት እንዳለህ ለይሖዋ በጸሎት ንገረው፤ እንዲሁም ሁኔታህን ለማስተካከል የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በንቃት ተከታተል። (1 ዮሐ. 5:14) ከዚህ ቀደም የዘወትር አቅኚ በመሆን የቀመስከውን ደስታ እንደገና ማጣጣም እንድትችል ይሖዋ ወደፊት “ትልቅ የሥራ በር” ይከፍትልህ ይሆናል።—1 ቆሮ. 16:9