በንግድ አካባቢዎች በድፍረት መመሥከር
1. በንግድ አካባቢዎች መመሥከር የሚያስፈራን ከሆነ ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?
1 በንግድ አካባቢዎች መመሥከር ያስፈራሃል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ፤ ልበ ሙሉ እና ደፋር የነበረው ጳውሎስ እንኳ በአንድ ወቅት የሰበከው ‘እንደምንም’ ድፍረት አግኝቶ እንደነበር ተናግሯል። (1 ተሰ. 2:2) በንግድ አካባቢዎች ከመመሥከር ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ የሚጋጥሙንን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችና እነዚህን ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚረዱንን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች ከዚህ በታች እንመለከታለን።
2. ሠራተኞቹ ይበሳጫሉ ብለን መጨነቅ የሌለብን ለምንድን ነው?
2 ሠራተኞቹን በሥራ መሃል ሳናግራቸው ቢበሳጩስ? በንግድ አካባቢ የሚሠሩ አብዛኞቹ ሠራተኞች ሕዝቡን የማገልገል ኃላፊነት እንዳለባቸው ስለሚሰማቸው አንድ ሰው በሥራ መሃል ቢያናግራቸው እንግዳ ነገር አይሆንባቸውም። እንዲያውም ወደፊት ደንበኛቸው ልትሆን እንደምትችል በማሰብ አብዛኛውን ጊዜ በትሕትና ያነጋግሩህ ይሆናል። ሥርዓታማ ልብስ መልበስህ እንዲሁም ተግባቢ መሆንህና ሞቅ ያለ መንፈስ ማሳየትህ በአክብሮት እንዲያነጋግሩህ ሊገፋፋቸው ይችላል።
3. ደንበኞች እንዳይበሳጩ ምን ማድረግ እንችላለን?
3 በርካታ ደንበኞች እያሉ ሠራተኞቹን ማናገር ይኖርብኛል? የሚቻል ከሆነ ደንበኞች በማይበዙበት ሰዓት ለምሳሌ፣ የንግድ ቦታዎቹ እንደተከፈቱ መሄዱ የተሻለ ነው። ሻጩ ወይም ኃላፊው ብቻውን የሚሆንበትን ጊዜ ጠብቃችሁ አናግሩ። መልእክታችሁን በአጭሩ ተናገሩ።
4. በንግድ አካባቢዎች ስንመሠክር ምን ልንል እንችላለን?
4 ምን ብዬ ማናገር ይኖርብኛል? በንግድ ቦታው ያሉት ሠራተኞች ብዙ ከሆኑ ኃላፊውን አነጋግሩ። እንዲህ ልትሉ ትችላላችሁ፦ “ዛሬ ወደ ሥራ ቦታችሁ የመጣሁት በንግድ አካባቢ የሚሠሩ ሰዎችን በቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ ነው። ሥራ ላይ ስለሆናችሁ መልእክቴን አጠር አድርጌ ለመናገር እሞክራለሁ።” ነጋዴዎች እንደሆንን ሊሰማቸው ስለሚችል ሥራችን የሚደገፈው በምን እንደሆነ ካልጠየቁን በስተቀር የገንዘብ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ባንጠይቃቸው የተሻለ ነው። የድርጅቱ ሁኔታ የሚያመች ከሆነ ደግሞ ሌሎቹን ሠራተኞች ለአጭር ጊዜ ለማነጋገር እንዲፈቅድልን ኃላፊውን ልንጠይቀው እንችላለን። እነዚህን ሠራተኞች ለማነጋገርም ቢሆን ከላይ የተጠቀሰውን አቀራረብ መጠቀም ይቻላል። አንድ ሠራተኛ ሥራ እንደበዛበት ከተሰማን መልእክታችንን በአጭሩ ከነገርነው በኋላ አንድ ትራክት ልንሰጠው እንችላለን። ሠራተኞቹን ማነጋገር ካልቻላችሁ ሠራተኞቹ ሊያዩት በሚችሉበት ቦታ ላይ ጽሑፎች አስቀምጣችሁ እንድትሄዱ ይፈቀድላችሁ ይሆናል።
5. በንግድ አካባቢ በድፍረት እንድንመሠክር የሚስችሉን የትኞቹ ምክንያቶች ናቸው?
5 ኢየሱስና ጳውሎስ በሥራ ቦታቸው ለነበሩ ሰዎች በድፍረት ሰብከዋል፤ አንተም ቢሆን እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። (ማቴ. 4:18-21፤ 9:9፤ ሥራ 17:17) ይሖዋ ልባችንን እንዲያረጋጋልን እንዲሁም ደፋሮች እንድንሆን እንዲረዳን እንጸልይ። (ሥራ 4:29) በንግድ አካባቢ ስናገለግል ሰው የማናገኝበት ቤት የለም ማለት ይቻላል፤ ታዲያ ፍሬያማ በሆነው በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ለምን አትሞክርም?