ወደ ኋላ አትበሉ—ብቃት ይጎድለኛል የሚለውን ስሜት ማሸነፍ
1. አንዳንዶች ጥናት ከማስጀመር ወደ ኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?
1 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት እንደማትችል በማሰብ ጥናት ከማስጀመር ወደ ኋላ ትላለህ? እንደ ሙሴና ኤርምያስ ያሉ በጥንት ጊዜ የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመወጣት ብቃቱ እንደሚጎድላቸው ተሰምቷቸው ነበር። (ዘፀ. 3:10, 11፤ 4:10፤ ኤር. 1:4-6) በመሆኑም እንዲህ ያለው ስሜት እንግዳ ነገር አይደለም። ታዲያ ይህን ስሜት ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?
2. ጥናት መምራትን ለሌሎች በመተው ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው የስብከት ሥራ ብቻ መርካት የሌለብን ለምንድን ነው?
2 ይሖዋ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ የማይጠይቀን መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝ. 103:14) በመሆኑም ሰዎችን ‘በማስተማር ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ’ የተሰጠንን ተልእኮ መወጣት እንችላለን። (ማቴ. 28:19, 20) ይሖዋ ይህን መብት የሰጠው ተሞክሮ ላካበቱ ወይም የማስተማር ተሰጥኦ ላላቸው ክርስቲያኖች ብቻ አይደለም። (1 ቆሮ. 1:26, 27) እንግዲያው ጥናት መምራትን ለሌሎች በመተው ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው የስብከት ሥራ ብቻ መርካት አይኖርብንም።
3. ይሖዋ ጥናት የመምራት ብቃት እንዲኖረን የሚያደርገው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ ብቁ እንድንሆን ያደርገናል፦ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ብቃት ያገኘነው ከይሖዋ ነው። (2 ቆሮ. 3:5) ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት በዓለም ላይ ያሉ የተማሩ ሰዎች እንኳ ያላወቋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አስተምሮናል። (1 ቆሮ. 2:7, 8) የታላቁ አስተማሪ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንድንችል የእሱን የማስተማር ዘዴ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እንዲቆይልን ያደረገ ከመሆኑም በላይ በጉባኤ አማካኝነትም ቀጣይነት ያለው ሥልጠና ይሰጠናል። በተጨማሪም ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የሚረዱ ጽሑፎችን በራሳችን እንድናዘጋጅ አልተወንም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደሚለው ያሉ እውነትን አሳማኝና ግልጽ በሆነ መንገድ የሚያስቀምጡ መሣሪያዎችን ሰጥቶናል። አዎን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ከምናስበው በላይ ቀላል ሆኖ ልናገኘው እንችላለን።
4. ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
4 ሙሴና ኤርምያስ በይሖዋ እርዳታ የተሰጣቸውን ተልእኮ መወጣት ችለዋል። (ዘፀ. 4:11, 12፤ ኤር. 1:7, 8) እኛም ይሖዋ እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን። ደግሞም አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና ስለ ይሖዋ እውነቱን እያስተማርነው ነው፤ ይህ በአምላክ ፊት ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። (1 ዮሐ. 3:22) በመሆኑም አርኪና አስደሳች በሆነው መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናቱ ሥራ ላይ ለመካፈል ግብ አውጡ።