“ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ”
በርዕሱ ላይ የተገለጸው ሐሳብ በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት ነው። (1 ጴጥ. 2:17) ይሁንና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያለብን በዛሬው ጊዜ ነው። ሰፊ ለሆነው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ፍቅር በጠፋበት በዚህ ዓለም ፍቅራችን እንዳይቀዘቅዝ ምን ማድረግ እንችላለን? (ማቴ. 24:12) መላው የወንድማማች ማኅበር የተባለውን ቪዲዮ ስትመለከት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር።
(1) የክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር አባል የምንሆነው ምን ስናደርግ ነው? (2) ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን የሚያከናውናቸው ሦስት እንቅስቃሴዎች ምንድን ናቸው? (3) ወንድሞቻችን (ሀ) ርቆ በሚገኘው በአላስካ ምድር (ለ) በአውሮፓ ትላልቅ ወደቦችና (ሐ) በፔሩ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ውስጥ ምሥራቹን በጽናት እየሰበኩ ያሉት እንዴት ነው? (4) ምሥራቹን መስበክ እንዲያው ተራ ሥራ እንደሆነ አድርገን ማሰብ የማይገባን ለምንድን ነው? (5) የይሖዋ ምሥክሮች (ሀ) መሬት መንቀጥቀጥ (ለ) ዓውሎ ነፋስ እንዲሁም (ሐ) የእርስ በርስ ጦርነት በተከሰተበት ወቅት አንዳቸው ለሌላው እርዳታና ማጽናኛ እንደሰጡ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ተናገር። (6) ሁላችንም የክርስቲያን የወንድማማች ማኅበራችን ተለይቶ የሚታወቅበትን ጉልህ ባሕርይ በየትኞቹ ተግባራዊ መንገዶች ማሳየት እንችላለን? (ዮሐ. 13:35) (7) የራሳችንን የመንግሥት አዳራሽ ለመገንባት በኅብረት መሥራታችን ምን ጥቅም ያስገኛል? (8) በምሥራቅ አውሮፓና በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችን በእገዳ ሥር በነበሩበት ጊዜ መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉት እንዴት ነው? (9) በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ምን የሚደነቁ ጥረቶችን ያደርጋሉ? ለምንስ? (10) ይህ ቪዲዮ (ሀ) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞች ጋር በኅብረት ይሖዋን ለማምለክ (ለ) ለሌሎች በችግራቸው ጊዜ ለመድረስ (ሐ) በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በታማኝነት ለመስበክ ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናከረልህ እንዴት ነው? (11) ይህን ቪዲዮ በአገልግሎታችን እንዴትና መቼ ልንጠቀምበት እንችላለን?
የክርስቲያን የወንድማማች ማኅበር አባል እንድንሆን ያደረገን ዋነኛው ምክንያት ለይሖዋ ያለን ፍቅር ነው። በመሆኑም ስለ አምላክ መማርና ለሌሎች ስለ እሱ ማስተማር ያስደስተናል። ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎችም እንወዳለን። ለወንድሞቻችን በችግራቸው ጊዜ ስንደርስላቸው አምላክ እንዲያመሰግነን አንጠብቅም። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያን የወንድማማች ማኅበርን ከአምላክ እንዳገኘነው ስጦታ አድርገን ስለምንመለከተው ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ይህ ፍቅር የሌለው ዓለም ሊጠፋ የቀረው ጊዜ አጭር ነው፤ እንግዲያው የቀረውን ጊዜ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እንጠቀምበት!