የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሚያዝያ 2020
ከሚያዝያ 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 31
“ያዕቆብና ላባ የሰላም ቃል ኪዳን ገቡ”
(ዘፍጥረት 31:44-46) በል አሁን ና፣ እኔና አንተ ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ይህም በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር ሆኖ ያገለግላል።” 45 ስለዚህ ያዕቆብ ድንጋይ ወስዶ እንደ ዓምድ አቆመው። 46 ከዚያም ያዕቆብ ወንድሞቹን “ድንጋይ ሰብስቡ!” አላቸው። እነሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ። በኋላም እዚያው ድንጋዩ ክምር ላይ በሉ።
it-1 883 አን. 1
ጋልኢድ
ያዕቆብ እና ላባ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከፈቱ በኋላ ቃል ኪዳን ተጋቡ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ያዕቆብ የድንጋይ ዓምድ ያቆመ ሲሆን በኋላም “ወንድሞቹን” የድንጋይ ክምር (በጠረጴዛ መልክ ሳይሆን አይቀርም) እንዲሠሩ አዘዛቸው፤ ከዚያም በድንጋዩ ክምር ላይ የቃል ኪዳኑን ማዕድ ተመገቡ። ላባም ቦታውን በአረማይክ (በሶርያኛ) “ያጋርሳሃዱታ” በማለት በዚህ ክምር ስም ሰየመው፤ ያዕቆብ ግን “ጋልኢድ” በማለት በዕብራይስጥ አቻ ስያሜ ሰጠው። ላባ “ይህ የድንጋይ ክምር [ዕብ. ጋል] ዛሬ በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር [ዕብ. ኤድ] ነው” በማለት ተናግሯል። (ዘፍ 31:44-48) የድንጋዩ ክምር (እና የድንጋዩ ዓምድ) በዚያ ለሚያልፉ ሰዎች ሁሉ እንደ ምሥክር ሆኖ ያገለግል ነበር። ቁጥር 49 እንደሚለው፣ ያዕቆብና ላባ በመካከላቸውም ሆነ በቤተሰቦቻቸው መካከል ሰላም ለማስፈን እንደተስማሙ የሚመሠክር “መጠበቂያ ግንብ [ዕብ. ሚጽፓህ]” ነበር። (ዘፍ 31:50-53) ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም ድንጋይ በተመሳሳይ መንገድ ድምፅ አልባ ምሥክር ሆኖ አገልግሏል።—ኢያሱ 4:4-7፤ 24:25-27
(ዘፍጥረት 31:47-50) ላባም የድንጋዩን ክምር ያጋርሳሃዱታ አለው፤ ያዕቆብ ግን ጋልኢድ ሲል ጠራው። 48 ከዚያም ላባ “ይህ የድንጋይ ክምር ዛሬ በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር ነው” አለ። ከዚህም የተነሳ ያዕቆብ ጋልኢድ 49 እና መጠበቂያ ግንብ የሚል ስም አወጣለት፤ ምክንያቱም ላባ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እርስ በርስ በማንተያይበት ጊዜ ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ጠባቂ ይሁን። 50 ልጆቼን ብትበድላቸውና በእነሱ ላይ ሌሎች ሚስቶችን ብታገባ ማንም ሰው ባያይም እንኳ አምላክ በእኔና በአንተ መካከል ምሥክር እንደሆነ አትርሳ።”
it-2 1172
መጠበቂያ ግንብ
ያዕቆብ የድንጋይ ክምር ከሠራ በኋላ “ጋልኢድ” (“የምሥክር ክምር” ማለት ነው) እና “መጠበቂያ ግንብ” በማለት ሰይሞታል። ከዚያም ላባ “እርስ በርስ በማንተያይበት ጊዜ ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ጠባቂ ይሁን” በማለት ተናግሯል። (ዘፍ 31:45-49) ይህ የድንጋይ ክምር ያዕቆብና ላባ፣ የገቡትን የሰላም ቃል ኪዳን ይጠብቁ እንደሆነና እንዳልሆነ ይሖዋ እንደሚያይ የሚያመለክት ምሥክር ሆኖ ያገለግላል።
(ዘፍጥረት 31:51-53) ላባም ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “የድንጋይ ክምሩ ይኸው፤ በእኔና በአንተ መካከል ያቆምኩት ዓምድም ይኸው። 52 እኔ አንተን ለመጉዳት ይህን የድንጋይ ክምር አልፌ ላልመጣ፣ አንተም እኔን ለመጉዳት ይህን የድንጋይ ክምርና ይህን ዓምድ አልፈህ ላትመጣ ይህ የድንጋይ ክምር ምሥክር ነው፤ ዓምዱም ቢሆን ምሥክር ይሆናል። 53 የአብርሃም አምላክና የናኮር አምላክ የሆነው የአባታቸው አምላክ በእኛ መካከል ይፍረድ።” ያዕቆብም አባቱ ይስሐቅ በሚፈራው አምላክ ማለ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 31:19) በዚህ ጊዜ ላባ በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባቷን የተራፊም ቅርጻ ቅርጾች ሰረቀች።
it-2 1087-1088
ተራፊም
የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በሜሶጶጣሚያና በአቅራቢያው ባሉ አካባቢዎች ያገኟቸው ግኝቶች እንደሚጠቁሙት የተራፊም ምስሎች ያሉት ሰው የቤተሰቡን ውርስ የማግኘት አጋጣሚው ሰፊ ነው። በኑዚ በተገኘ ጽላት ላይ የሰፈረው ሐሳብ፣ አንድ ሰው የቤተሰቡ አማልክት በእጁ የሚገኙ ከሆነ አማቱ ሲሞት ፍርድ ቤት ቀርቦ የአማቱ ርስት እንዲሰጠው ሊጠይቅ እንደሚችል ይጠቁማል። (በፕሪቻርድ የተዘጋጀው ኤንሸንት ኒር ኢስተርን ቴክስትስ፣ 1974፣ ገጽ 219፣ 220 እና ግርጌ 51) ከዚህ አንጻር ራሔል አባቷ ባለቤቷን ያዕቆብን ስላጭበረበረው ተራፊሙን መውሰዷ ተገቢ እንደሆነ ተሰምቷት ሊሆን ይችላል። (ከዘፍ 31:14-16 ጋር አወዳድር።) ላባም ቢሆን ተራፊሞቹን መልሶ የማግኘቱ ጉዳይ በጣም ያሳሰበው እነዚህ ምስሎች ከውርስ መብት ጋር ተያያዥነት ስላላቸው ሊሆን ይችላል፤ እንዲያውም ያዕቆብ ላይ ለመድረስ ወንድሞቹን አስከትሎ ለሰባት ቀን ያህል ተጉዟል። (ዘፍ 31:19-30) እርግጥ ያዕቆብ፣ ራሔል ስለፈጸመችው ድርጊት ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም (ዘፍ 31:32)፤ እንዲሁም ተራፊሞቹን ተጠቅሞ ከላባ ልጆች ላይ ውርሱን ለመውሰድ እንደሞከረ የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። ያዕቆብ ከጣዖታቱ ጋር አንዳች ንክኪ አልነበረውም። ተራፊሞቹ ያዕቆብ ጋር የቆዩት ግፋ ቢል ያዕቆብ ባዕዳን አማልክትን በሙሉ ከቤተሰቡ አባላት ተቀብሎ በሴኬም አቅራቢያ ባለው ትልቅ ዛፍ ሥር እስከቀበረበት ጊዜ ነው።—ዘፍ 35:1-4
(ዘፍጥረት 31:41, 42) እንግዲህ 20 ዓመት ሙሉ በቤትህ የኖርኩት በዚህ ሁኔታ ነበር። ለሁለት ሴቶች ልጆችህ ስል 14 ዓመት፣ ለመንጋህ ስል ደግሞ 6 ዓመት አገለገልኩህ። አንተ ግን ደሞዜን አሥር ጊዜ ትቀያይርብኝ ነበር። 42 የአባቴ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክና ይስሐቅ የሚፈራው አምላክ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ታሰናብተኝ ነበር። አምላክ ጉስቁልናዬንና ልፋቴን አየ፤ ትናንት ሌሊት የገሠጸህም ለዚህ ነው።”
(1 ጴጥሮስ 2:18) አገልጋዮች ጥሩና ምክንያታዊ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ለማይደሰቱ ጌቶቻቸውም እንኳ ተገቢ ፍርሃት በማሳየት ይገዙ።
ይሖዋ መጠጊያችን ነው
8 ያዕቆብ ካራን ሲደርስ አጎቱ ላባ ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረገለት ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ልያንና ራሔልን ዳረለት። ይሁንና ውሎ አድሮ ላባ የያዕቆብን ደሞዝ አሥር ጊዜ በመለዋወጥ ጉልበቱን አላግባብ ለመበዝበዝ ሞክሯል። (ዘፍ. 31:41, 42) ያም ሆኖ ያዕቆብ ይሖዋ እሱን መንከባከቡን እንደማይተው በመተማመን የደረሰበትን ግፍ ችሎ ኖሯል፤ ደግሞም ይሖዋ ተንከባክቦታል። አምላክ ወደ ከነዓን ምድር እንዲመለስ በነገረው ጊዜ ያዕቆብ “የብዙ መንጎች፣ የሴትና የወንድ አገልጋዮች፣ እንዲሁም የግመሎችና የአህዮች ባለቤት” ሆኖ ነበር። (ዘፍ. 30:43) ያዕቆብ ይሖዋ ያደረገለትን ነገር በእጅጉ በማድነቅ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “እኔ ባሪያህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በስተቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሰራዊት ሆኛለሁ።”—ዘፍ. 32:10
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 31:1-18) ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ፣ የላባ ልጆች “ያዕቆብ የአባታችንን ንብረት እንዳለ ወስዷል፤ ይህን ሁሉ ሀብት ያካበተው እኮ ከአባታችን ንብረት ነው” ሲሉ ሰማ። 2 ያዕቆብ የላባን ፊት ሲመለከት ፊቱ እንደተለወጠበት አስተዋለ። 3 በመጨረሻም ይሖዋ ያዕቆብን “ወደ አባቶችህና ወደ ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” አለው። 4 ከዚያም ያዕቆብ ራሔልና ሊያ መንጎቹን ወዳሰማራበት መስክ እንዲመጡ መልእክት ላከባቸው፤ 5 እንዲህም አላቸው፦ “አባታችሁን ሳየው ፊቱ ተለውጦብኛል፤ የአባቴ አምላክ ግን ከእኔ አልተለየም። 6 መቼም አባታችሁን ባለኝ አቅም ሁሉ እንዳገለገልኩት እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ። 7 አባታችሁ ሊያጭበረብረኝ ሞክሯል፤ ደሞዜንም አሥር ጊዜ ቀያይሮብኛል፤ አምላክ ግን ጉዳት እንዲያደርስብኝ አልፈቀደለትም። 8 ‘ደሞዝህ ዥጉርጉር የሆኑት ይሆናሉ’ ሲለኝ መንጎቹ ሁሉ ዥጉርጉር ወለዱ፤ ‘ደሞዝህ ሽንትር ያለባቸው ይሆናሉ’ ሲለኝ ደግሞ መንጎቹ ሁሉ ሽንትር ያለባቸው ወለዱ። 9 ስለዚህ አምላክ የአባታችሁን ከብቶች ከእሱ እየወሰደ ለእኔ ይሰጠኝ ነበር። 10 በአንድ ወቅት፣ መንጎቹ ለስሪያ በሚነሳሱበት ጊዜ እንስቶቹን የሚያጠቁት አውራ ፍየሎች ሽንትር ያለባቸው፣ ዥጉርጉር የሆኑና ጠቃጠቆ ያለባቸው መሆናቸውን በሕልሜ አየሁ። 11 ከዚያም የእውነተኛው አምላክ መልአክ በሕልሜ ‘ያዕቆብ!’ ሲል ጠራኝ፤ እኔም ‘አቤት’ አልኩት። 12 እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘እንስቶቹን የሚያጠቁት አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽንትር ያለባቸው፣ ዥጉርጉር የሆኑና ጠቃጠቆ ያለባቸው መሆናቸውን እባክህ ቀና ብለህ ተመልከት፤ ምክንያቱም ላባ እየፈጸመብህ ያለውን ነገር ሁሉ ተመልክቻለሁ። 13 ዓምድ አቁመህ የቀባህበትና በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልክበት የቤቴል እውነተኛው አምላክ እኔ ነኝ። በል አሁን ተነስተህ ከዚህ ምድር ውጣ፤ ወደተወለድክበትም ምድር ተመለስ።’” 14 በዚህ ጊዜ ራሔልና ሊያ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “እንደው ለመሆኑ በአባታችን ቤት ልንወርሰው የምንችለው የቀረ ነገር ይኖራል? 15 እሱ እኛን የሸጠንና ለእኛ የተሰጠውን ገንዘብ የበላው እንደ ባዕድ ስለሚያየን አይደለም? 16 አምላክ ከአባታችን ላይ የወሰደበት ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው። ስለሆነም አምላክ አድርግ ያለህን ነገር ሁሉ አድርግ።” 17 ከዚያም ያዕቆብ ተነሳ፤ ልጆቹንና ሚስቶቹን ግመል ላይ አስቀመጣቸው፤ 18 እንዲሁም መንጎቹን ሁሉና ያከማቸውን ንብረት ሁሉ፣ በጳዳንአራም ሳለ ያገኛቸውንም ከብቶች ሁሉ እየነዳ በከነአን ምድር ወደሚገኘው ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ።
ከሚያዝያ 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 32–33
“በረከት ለማግኘት እየታገላችሁ ነው?”
(ዘፍጥረት 32:24) በመጨረሻም ያዕቆብ ብቻውን ቀረ። ከዚያም አንድ ሰው ጎህ እስኪቀድ ድረስ ሲታገለው ቆየ።
ይሖዋን ከልብ እየፈለግኸው ነውን?
ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋን ከልብ ስለፈለጉ ሰዎች የሚናገሩ በርካታ ምሳሌዎችን ይዘዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ያዕቆብ ሲሆን ሥጋ ከለበሰ የአምላክ መልአክ ጋር ሌሊቱን ሙሉ ሲታገል አድሯል። ከአምላክ ጋር ‘ስለታገለ’ ማለትም ስለ ጸና፣ ከፍተኛ ጥረት ስላደረገ ወይም ሳይታክት ስለታገለ እስራኤል (ከአምላክ ጋር የታገለ) የሚል ስም ተሰጥቶታል። ያዕቆብ ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ መልአኩ ባርኮታል።—ዘፍጥረት 32:24-30
(ዘፍጥረት 32:25, 26) ሰውየውም ሊያሸንፈው እንዳልቻለ ሲያይ የጭኑን መጋጠሚያ ነካው፤ ያዕቆብም ከእሱ ጋር በሚታገልበት ጊዜ የጭኑ መጋጠሚያ ከቦታው ተናጋ። 26 በኋላም ሰውየው “ጎህ እየቀደደ ስለሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው። እሱም “ካልባረክኸኝ አለቅህም” አለው።
it-2 190
አንካሳ፣ ማነከስ
የያዕቆብ ማነከስ። ያዕቆብ ዕድሜው 97 ዓመት ገደማ በነበረበት ጊዜ፣ ሥጋ ከለበሰ የአምላክ መልአክ ጋር ሌሊቱን ሙሉ ሲታገል አድሮ ነበር። እስኪባርከው ድረስ መልአኩን ይዞ በማቆየት አሸንፎታል። በትግሉ ወቅት መልአኩ ያዕቆብን የጭኑ መጋጠሚያ ላይ ስለነካው መጋጠሚያው ከቦታው ተናጋ። በዚህም የተነሳ ያዕቆብ ማነከስ ጀመረ። (ዘፍ 32:24-32፤ ሆሴዕ 12:2-4) ያዕቆብ ያጋጠመው ይህ ነገር፣ መልአኩ እንዳለው ‘ከአምላክም [ከአምላክ መልአክ] ሆነ ከሰዎች ጋር ታግሎ በመጨረሻ ቢያሸንፍም’ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የአምላክን ኃያል መልአክ ድል እንዳላደረገ ያስታውሰዋል። ያዕቆብ ከመልአኩ ጋር መታገል የቻለው የአምላክ ዓላማና ፈቃድ ስለሆነ ብቻ ነው፤ አምላክ ይህ ሁኔታ ያዕቆብ የእሱን በረከት ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የሚያሳይ ማስረጃ ሆኖ እንዲያገለግል ፈልጎ ነበር።
(ዘፍጥረት 32:27, 28) በመሆኑም ሰውየው “ስምህ ማን ነው?” አለው፤ እሱም “ያዕቆብ” ሲል መለሰለት። 28 ሰውየውም “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ ያዕቆብ አይባልም፤ ምክንያቱም ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ታግለህ በመጨረሻ አሸንፈሃል” አለው።
it-1 1228
እስራኤል
1. ያዕቆብ ዕድሜው 97 ዓመት ገደማ በነበረበት ጊዜ አምላክ ያወጣለት ስም ነው። ይህ ስም የወጣለት ከወንድሙ ከኤሳው ጋር ለመገናኘት በያቦቅ መልካ ከተሻገረ በኋላ ከአንድ መልአክ ጋር ሲታገል ባደረበት ሌሊት ነው። ያዕቆብ ከመልአኩ ጋር በጽናት ታግሏል፤ በመሆኑም የቀድሞ ስሙ ተቀይሮ የአምላክን በረከት እንዳገኘ የሚያሳይ እስራኤል የሚል ስም ተሰጠው። ያዕቆብ ለዚህ ክንውን መታሰቢያ እንዲሆን የቦታውን ስም ጰኒኤል ወይም ጰኑኤል በማለት ሰየመው። (ዘፍ 32:22-31፤ ያዕቆብ ቁ. 1ን ተመልከት።) በኋላም አምላክ የያዕቆብ ስም መለወጡን በቤቴል ዳግመኛ አረጋግጧል፤ ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ያዕቆብ በተደጋጋሚ እስራኤል ተብሎ ተጠርቷል። (ዘፍ 35:10, 15፤ 50:2፤ 1ዜና 1:34) ይሁን እንጂ እስራኤል የሚለው ስም ከተጠቀሰባቸው ከ2,500 የሚበልጡ ቦታዎች መካከል አብዛኞቹ የያዕቆብን ዘሮች በብሔር ደረጃ የሚያመለክቱ ናቸው።—ዘፀ 5:1, 2
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 32:11) ከወንድሜ ከኤሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ ምክንያቱም መጥቶ በእኔም ሆነ በእነዚህ እናቶችና በልጆቻቸው ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝር ፈርቻለሁ።
(ዘፍጥረት 32:13-15) እሱም በዚያ ሌሊት እዚያው አደረ። ከንብረቱም መካከል የተወሰነውን ወስዶ ለወንድሙ ለኤሳው ስጦታ አዘጋጀ፤ 14 ስጦታውም የሚከተለው ነበር፦ 200 እንስት ፍየሎች፣ 20 ተባዕት ፍየሎች፣ 200 እንስት በጎች፣ 20 አውራ በጎች 15 እንዲሁም 30 የሚያጠቡ ግመሎች፣ 40 ላሞች፣ 10 በሬዎች፣ 20 እንስት አህዮችና 10 ተባዕት አህዮች።
ለዛ ያለው አነጋገር ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ያደርጋል
10 ለዛ ያለው ወይም ደግነት የሚንጸባረቅበት ንግግርና ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመመሥረትም ሆነ ይህን ወዳጅነት ጠብቀን ለማቆየት ይረዳል። በመሆኑም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማሻሻል የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን የተሻለ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ከልብ ተነሳስተን ለሌሎች ደግነት የሚንጸባረቅበት ነገር ማድረጋችን ለምሳሌ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፈለጋችን፣ ስጦታ መስጠታችንና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየታችን ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል። እንዲያውም እንዲህ ያለ ተግባር መፈጸማችን በአንድ ሰው ላይ ‘ፍም በመከመር’ መልካም ባሕርያቱ ጎልተው እንዲወጡ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህም ጉዳዩን በግልጽ ተነጋግሮ መፍታት ቀላል እንዲሆን ያደርጋል።—ሮም 12:20, 21
11 በጥንት ዘመን የኖረው ያዕቆብ እንዲህ ማድረግ ያለውን ጥቅም ተገንዝቦ ነበር። ያዕቆብ፣ መንትያ ወንድሙ የሆነው ዔሳው በጣም ተበሳጭቶበት ስለነበር እንዳይገድለው በመፍራት ሸሽቶ ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ያዕቆብ ከሸሸበት ተመለሰ። ዔሳውም 400 ሰዎችን አስከትሎ ወንድሙን ለመገናኘት ወጣ። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ይሖዋ እንዲረዳው ጸለየ። ከዚያም በርካታ እንስሳትን ለዔሳው ስጦታ አድርጎ ላከ። ያዕቆብ የላከው ስጦታ የታለመለትን ግብ መቷል። ወንድማማቾቹ ሲገናኙ የዔሳው አመለካከት ተለውጦ ስለነበረ ያዕቆብን ሮጦ አቀፈው።—ዘፍ. 27:41-44፤ 32:6, 11, 13-15፤ 33:4, 10
(ዘፍጥረት 33:20) በዚያም መሠዊያ አቆመ፤ መሠዊያውንም አምላክ፣ የእስራኤል አምላክ ብሎ ጠራው።
it-1 980
አምላክ፣ የእስራኤል አምላክ
ያዕቆብ በጰኒኤል ከይሖዋ መልአክ ጋር ከተገናኘ በኋላ እስራኤል የሚል ስም ተሰጠው፤ ከዚያም ከወንድሙ ከኤሳው ጋር በሰላም ከተለያየ በኋላ በሱኮት ቀጥሎም በሴኬም መኖር ጀመረ። በዚህ ስፍራ ከኤሞር ወንዶች ልጆች መሬት ገዝቶ ድንኳኑን ተከለ። (ዘፍ 32:24-30፤ 33:1-4, 17-19) “በዚያም መሠዊያ አቆመ፤ መሠዊያውንም አምላክ፣ የእስራኤል አምላክ [ወይም “አምላክ የእስራኤል አምላክ ነው”] ብሎ ጠራው።” (ዘፍ 33:20) ያዕቆብ አዲስ የተሰጠውን ስም ከመሠዊያው ስም ጋር አያይዞ በመጠቀም ስሙን እንደተቀበለውና ለስሙ አድናቆት እንዳለው እንዲሁም አምላክ በሰላም እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር መልሶ ስላስገባው አመስጋኝ እንደሆነ አሳይቷል። ይህ አገላለጽ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 32:1-21) ከዚያም ያዕቆብ ጉዞውን ቀጠለ፤ የአምላክ መላእክትም አገኙት። 2 ያዕቆብም ልክ እንዳያቸው “ይህ የአምላክ ሰፈር ነው!” አለ። በመሆኑም የቦታውን ስም ማሃናይም አለው። 3 ከዚያም ያዕቆብ በኤዶም ክልል ሴይር በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ኤሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤ 4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፦ “ጌታዬን ኤሳውን እንዲህ በሉት፦ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “ከላባ ጋር እስካሁን ድረስ ለረጅም ጊዜ ኖሬአለሁ። 5 አሁን በሬዎች፣ አህዮች፣ በጎች እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮች አሉኝ፤ ይህን መልእክት ለጌታዬ የላክሁት በፊትህ ሞገስ እንዳገኝ ለመጠየቅ ነው።”’” 6 ከተወሰነ ጊዜ በኋላም መልእክተኞቹ ወደ ያዕቆብ ተመልሰው በመምጣት እንዲህ አሉት፦ “ወንድምህን ኤሳውን አግኝተነው ነበር፤ እሱም ከአንተ ጋር ለመገናኘት ወደዚህ እየመጣ ነው፤ ከእሱም ጋር 400 ሰዎች አሉ።” 7 ያዕቆብም እጅግ ፈራ፤ በጭንቀትም ተዋጠ። በመሆኑም አብረውት ያሉትን ሰዎች፣ መንጎቹን፣ ከብቶቹንና ግመሎቹን በሁለት ቡድን ከፈላቸው። 8 እሱም “ምናልባት ኤሳው በአንደኛው ቡድን ላይ ጥቃት ቢሰነዝር፣ ሌላኛው ቡድን ሊያመልጥ ይችላል” አለ። 9 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ አለ፦ “‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም መልካም ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልከኝ የአባቴ የአብርሃም አምላክና የአባቴ የይስሐቅ አምላክ የሆንከው ይሖዋ ሆይ፣ 10 እኔ ባሪያህ ይህን ያህል ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ልታሳየኝ የሚገባኝ ሰው አልነበርኩም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር ከበትር ሌላ ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ቡድን ሆኛለሁ። 11 ከወንድሜ ከኤሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ ምክንያቱም መጥቶ በእኔም ሆነ በእነዚህ እናቶችና በልጆቻቸው ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝር ፈርቻለሁ። 12 አንተው ራስህ ‘በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፤ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሳ ሊቆጠር እንደማይችል የባሕር አሸዋ አደርገዋለሁ’ ብለኸኛል።” 13 እሱም በዚያ ሌሊት እዚያው አደረ። ከንብረቱም መካከል የተወሰነውን ወስዶ ለወንድሙ ለኤሳው ስጦታ አዘጋጀ፤ 14 ስጦታውም የሚከተለው ነበር፦ 200 እንስት ፍየሎች፣ 20 ተባዕት ፍየሎች፣ 200 እንስት በጎች፣ 20 አውራ በጎች 15 እንዲሁም 30 የሚያጠቡ ግመሎች፣ 40 ላሞች፣ 10 በሬዎች፣ 20 እንስት አህዮችና 10 ተባዕት አህዮች። 16 እሱም በመንጋ በመንጋ ለይቶ ለአገልጋዮቹ ሰጣቸው። አገልጋዮቹንም “ቀድማችሁኝ ተሻገሩ፤ አንዱን መንጋ ከሌላው መንጋ አራርቁት” አላቸው። 17 በተጨማሪም የመጀመሪያውን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ወንድሜ ኤሳው ቢያገኝህና ‘ለመሆኑ አንተ የማን ነህ? የምትሄደው ወዴት ነው? እነዚህ የምትነዳቸው እንስሳትስ የማን ናቸው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣ 18 ‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው። ይህ ለጌታዬ ለኤሳው የተላከ ስጦታ ነው፤ እንዲያውም እሱ ራሱ ከኋላችን እየመጣ ነው’ በለው።” 19 እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎቹን የሚነዱትን በሙሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ኤሳውን ስታገኙት ይህንኑ ንገሩት። 20 ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ ማለት እንዳለባችሁም አትዘንጉ።” ይህን ያላቸው ‘ስጦታውን አስቀድሜ በመላክ ቁጣው እንዲበርድለት ካደረግኩ ከእሱ ጋር ስገናኝ በጥሩ ሁኔታ ይቀበለኝ ይሆናል’ ብሎ ስላሰበ ነው። 21 በመሆኑም ስጦታው ከእሱ ቀድሞ ተሻገረ፤ እሱ ግን እዚያው የሰፈረበት ቦታ አደረ።
ከሚያዝያ 27–ግንቦት 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፍጥረት 34–35
“መጥፎ ጓደኝነት የሚያስከትለው ከባድ መዘዝ”
(ዘፍጥረት 34:1) ያዕቆብ ከሊያ የወለዳት ዲና የተባለችው ልጅ እዚያ አገር ካሉ ወጣት ሴቶች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ትወጣ ነበር።
ሴኬም—በሸለቆ ውስጥ የምትገኝ ከተማ
ዘወትር ወደ ከተማቸው የምትመጣውን (ብቻዋን ሳይሆን አይቀርም) ይህችን ድንግል ወጣት በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ወንዶች እንዴት ተመልክተዋት ይሆን? የአገሩ አለቃ ልጅ “አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፣ አስነወራትም።” ዲና ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ከነዓናውያን ጋር በመዋል በራስዋ ላይ ችግር የፈጠረችው ለምን ነበር? በእሷ ዕድሜ ካሉ ልጃገረዶች ጋር አብራ ለመዋል በመፈለጓ ምክንያት ነበርን? እንደ አንዳንዶቹ ወንድሞቿ ሁሉ ግትርና በራሷ ሐሳብ የምትመራ ነበረችን? የዘፍጥረትን መጽሐፍ ዘገባ አንብብና ልጃቸው ወደ ሴኬም መሄዷ ባስከተለባቸው አሳዛኝ ውጤቶች ምክንያት ያዕቆብና ልያ የተሰማቸውን ጭንቀትና ሐፍረት ለመረዳት ሞክር።—ዘፍጥረት 34:1-31፤ 49:5-7፤ በተጨማሪም ሰኔ 15, 1985 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31 ተመልከት።
(ዘፍጥረት 34:2) የአገሩ አለቃ የሆነው የሂዋዊው የኤሞር ልጅ ሴኬም ዲናን አያት፤ ከዚያም ወሰዳትና አብሯት ተኛ፤ አስገድዶም ደፈራት።
“ከፆታ ብልግና ሽሹ!”
14 ሴኬም ዲናን ስለወደዳት ተገቢ መስሎ የታየውን ነገር አደረገ። ዲናን “ወሰዳት”፤ ከዚያም ‘አስገድዶ ደፈራት።’ (ዘፍጥረት 34:1-4ን አንብብ።) ሴኬም በዲና ላይ ያደረሰው በደል እሷንም ሆነ መላ ቤተሰቧን ለሐዘን የዳረጉ ክስተቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል።—ዘፍጥረት 34:7, 25-31፤ ገላትያ 6:7, 8
(ዘፍጥረት 34:7) ሆኖም የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ስለ ሁኔታው ሰሙ፤ ወዲያውኑም ከመስክ መጡ። ሴኬም የያዕቆብን ሴት ልጅ በመድፈር ፈጽሞ መደረግ የማይገባውን ድርጊት ስለፈጸመና በዚህም እስራኤልን ስላዋረደ በጣም ተበሳጩ፤ እጅግም ተቆጡ።
(ዘፍጥረት 34:25) ሆኖም በሦስተኛው ቀን፣ ሰዎቹ ገና ቆስለው እያሉ የዲና ወንድሞች የሆኑት ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ማለትም ስምዖንና ሌዊ ማንም ሳይጠረጥራቸው ሰይፋቸውን ይዘው ወደ ከተማዋ በመግባት ወንዶቹን ሁሉ ገደሉ።
ሰዎች ሲያናድዱህ
አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ለመበቀል የሚነሳሱት የደረሰባቸው በደል ያስከተለባቸውን የስሜት ሥቃይ ለማስታገስ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የዕብራዊው የያዕቆብ ልጆች፣ ከነዓናዊው ሴኬም እህታቸውን ዲናን እንዳስነወራት በሰሙ ጊዜ እጅግ በጣም ‘እንዳዘኑና ክፉኛ እንደተቈጡ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 34:1-7) ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች በእህታቸው ላይ ለተፈጸመው ድርጊት የበቀል እርምጃ ለመውሰድ በሴኬምና በቤተሰቡ ላይ ተንኮል ጠነሰሱ። ስምዖንና ሌዊ የጠነሰሱት ሴራ ስለተሳካላቸው ወደ ከነዓናውያን ከተማ በመግባት ሴኬምን ጨምሮ ሁሉንም ወንዶች ገደሉ።—ዘፍጥረት 34:13-27
ታዲያ ስምዖንና ሌዊ ደም ማፍሰሳቸው ሁኔታው እንዲስተካከል አድርጓል? ያዕቆብ ልጆቹ ያደረጉትን ነገር ከሰማ በኋላ እንዲህ በማለት ገሥጿቸዋል፦ “በዚህ አገር በሚኖሩት . . . እንደ ጥምብ አስቈጠራችሁኝ፣ ጭንቀትም እንዲደርስብኝ አድርጋችኋል። . . . ተባብረው ቢነሡብኝና ቢያጠቁኝ እኔና ቤተ ሰቤ መጥፋታችን አይደለምን?” (ዘፍጥረት 34:30) አዎን፣ እነዚህ ሰዎች የወሰዱት የበቀል እርምጃ ችግሩ እንዲፈታ አላደረገም፤ እንዲያውም ያዕቆብና ቤተሰቡ ‘ጎረቤቶቻችን መልሰው ይበቀሉናል’ በሚል ስሜት የሰቀቀን ሕይወት እንዲመሩ አድርጓቸዋል። አምላክ በያዕቆብ ቤተሰብ ላይ አደጋ እንዳይደርስ አስቦ ሳይሆን አይቀርም ያዕቆብ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ቤቴል እንዲሄድ አዘዘው።—ዘፍጥረት 35:1, 5
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፍጥረት 35:8) በኋላም የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ ሞተች፤ በቤቴል አቅራቢያ በሚገኝ የባሉጥ ዛፍ ሥርም ተቀበረች። በመሆኑም ስሙን አሎንባኩት አለው።
it-1 600 አን. 4
ዲቦራ
1. የርብቃ ሞግዚት። ርብቃ ከአባቷ ከባቱኤል ቤት ወጥታ ይስሐቅን ለማግባት ወደ ፓለስቲና በተጓዘች ጊዜ ዲቦራ አብራት ሄዳ ነበር። (ዘፍ 24:59) ለበርካታ ዓመታት በይስሐቅ ቤት ውስጥ ስታገለግል ቆይታ፣ ምናልባትም ርብቃ ከሞተች በኋላ ሳይሆን አይቀርም፣ በያዕቆብ ቤት ውስጥ ማገልገል ጀመረች። ርብቃ ይስሐቅን ካገባች ከ125 ዓመት ገደማ በኋላ ዲቦራ ሞተች፤ ከዚያም በቤቴል በአንድ ትልቅ ዛፍ ሥር ተቀበረች። ለዛፉ የተሰጠው ስም (አሎንባኩት፣ “ግዙፍ የለቅሶ ዛፍ” ማለት ነው) ዲቦራ በያዕቆብና በቤተሰቡ ዘንድ ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበረች ይጠቁማል።—ዘፍ 35:8
(ዘፍጥረት 35:22-26) አንድ ቀን፣ እስራኤል በዚያ ምድር ሰፍሮ ሳለ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋር ተኛ፤ እስራኤልም ይህን ሰማ። ያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ነበሩት። 23 ከሊያ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ የበኩር ልጁ ሮቤል ከዚያም ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር እና ዛብሎን ነበሩ። 24 ከራሔል የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ዮሴፍና ቢንያም ነበሩ። 25 ከራሔል አገልጋይ ከባላ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ዳንና ንፍታሌም ነበሩ። 26 ከሊያ አገልጋይ ከዚልጳ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ደግሞ ጋድና አሴር ነበሩ። እነዚህ ያዕቆብ በጳዳንአራም ሳለ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ናቸው።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በጥንቷ እስራኤል በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የሚካተቱት የብኩርና መብት ያላቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ?
በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የሚካተቱት የብኩርና መብት ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ የተናገርንባቸው ጊዜያት ነበሩ። በዕብራውያን 12:16 ላይ ከሰፈረው ሐሳብ በመነሳት እዚህ ድምዳሜ መድረስ የሚቻል ይመስል ነበር። ጥቅሱ ኤሳው “ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው” እንደነበረና “ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን [ለያዕቆብ] አሳልፎ እንደሰጠ” ይናገራል። ይህ ሐሳብ ያዕቆብ ‘የብኩርና መብት’ ማግኘቱ በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ ለመካተት የሚያስችል አጋጣሚም እንደከፈተለት የሚጠቁም ይመስላል።—ማቴ. 1:2, 16፤ ሉቃስ 3:23, 34
ይሁን እንጂ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስንመረምር በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተቱት፣ የበኩር ልጆች ብቻ እንዳልሆኑ ማስተዋል እንችላለን። እስቲ አንዳንድ ማስረጃዎችን እንመልከት፦
ከያዕቆብ (እስራኤል) ልጆች መካከል በኩሩ ከልያ የተወለደው ሮቤል ነው። ያዕቆብ በጣም ከሚወዳት ሚስቱ ከራሔል የወለደው የበኩር ልጁ ደግሞ ዮሴፍ ነው። ሮቤል በሠራው ስህተት የተነሳ፣ የብኩርና መብቱ ወደ ዮሴፍ ተላለፈ። (ዘፍ. 29:31-35፤ 30:22-25፤ 35:22-26፤ 49:22-26፤ 1 ዜና 5:1, 2) ያም ሆኖ የመሲሑ የዘር ሐረግ የመጣው በሮቤልም ሆነ በዮሴፍ በኩል አልነበረም። መሲሑ የመጣው የያዕቆብ አራተኛ ልጅ በሆነውና ከልያ በተወለደው በይሁዳ በኩል ነበር።—ዘፍ. 49:10
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፍጥረት 34:1-19) ያዕቆብ ከሊያ የወለዳት ዲና የተባለችው ልጅ እዚያ አገር ካሉ ወጣት ሴቶች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ትወጣ ነበር። 2 የአገሩ አለቃ የሆነው የሂዋዊው የኤሞር ልጅ ሴኬም ዲናን አያት፤ ከዚያም ወሰዳትና አብሯት ተኛ፤ አስገድዶም ደፈራት። 3 እሱም ልቡ በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ወጣቷንም አፈቀራት፤ በሚያባብሉ ቃላትም አነጋገራት። 4 በመጨረሻም ሴኬም አባቱን ኤሞርን “ከዚህች ልጅ ጋር አጋባኝ” አለው። 5 ያዕቆብ፣ ሴኬም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት በሰማ ጊዜ ወንዶች ልጆቹ በመስክ መንጎቹን እየጠበቁ ነበር። በመሆኑም ያዕቆብ ልጆቹ እስኪመለሱ ድረስ ዝም አለ። 6 በኋላም የሴኬም አባት ኤሞር ከያዕቆብ ጋር ለመነጋገር ወጣ። 7 ሆኖም የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ስለ ሁኔታው ሰሙ፤ ወዲያውኑም ከመስክ መጡ። ሴኬም የያዕቆብን ሴት ልጅ በመድፈር ፈጽሞ መደረግ የማይገባውን ድርጊት ስለፈጸመና በዚህም እስራኤልን ስላዋረደ በጣም ተበሳጩ፤ እጅግም ተቆጡ። 8 ኤሞርም እንዲህ አላቸው፦ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን በጣም ወዷታል። እባካችሁ ሚስት እንድትሆነው ስጡት፤ 9 በጋብቻም እንዛመድ። ሴቶች ልጆቻችሁን ዳሩልን፤ የእኛንም ሴቶች ልጆች አግቡ። 10 አብራችሁንም መኖር ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት። ኑሩባት፤ ነግዱባት፤ ሀብትም አፍሩባት።” 11 ከዚያም ሴኬም አባቷንና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፦ “በፊታችሁ ሞገስ ላግኝ እንጂ የምትጠይቁኝን ሁሉ እሰጣለሁ። 12 ብዙ ጥሎሽና ስጦታ ልትጠይቁኝ ትችላላችሁ። እኔ የጠየቃችሁኝን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ። ብቻ ይህችን ወጣት ሚስቴ እንድትሆን ስጡኝ።” 13 የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም ሴኬም እህታቸውን ዲናን ስላስነወረ ለእሱና ለአባቱ ለኤሞር ተንኮል ያዘለ መልስ ሰጧቸው። 14 እንዲህም አሏቸው፦ “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አናደርግም፤ እህታችንን ላልተገረዘ ሰው አንሰጥም፤ ምክንያቱም ይህ ለእኛ ውርደት ነው። 15 በሐሳባችሁ የምንስማማው እኛን ከመሰላችሁና የእናንተ የሆነው ወንድ ሁሉ እንዲገረዝ ካደረጋችሁ ብቻ ነው። 16 ከዚያም ሴቶች ልጆቻችንን እንድርላችኋለን፤ እኛም ሴቶች ልጆቻችሁን እናገባለን፤ አብረናችሁም እንኖራለን፤ አንድ ሕዝብም እንሆናለን። 17 የምንላችሁን የማትሰሙና ለመገረዝ ፈቃደኛ የማትሆኑ ከሆነ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።” 18 የተናገሩትም ነገር ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን ደስ አሰኛቸው። 19 ወጣቱም ያሉትን ነገር ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም፤ ምክንያቱም የያዕቆብን ልጅ ወዷት ነበር፤ ደግሞም በአባቱ ቤት ካሉት ሰዎች ሁሉ እጅግ የተከበረ ነበር።