የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w22 ሚያዝያ ገጽ 2-3
  • ጭንቀትን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጭንቀትን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዳዊት ጭንቀትን እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው?
  • ጭንቀት ሲያጋጥምህ የዳዊትን ምሳሌ ተከተል
  • በይሖዋ እርዳታ ይሳካልሃል
  • የሚያስጨንቃችሁን ነገር ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • ጭንቀትህን ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • ጭንቀትን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
w22 ሚያዝያ ገጽ 2-3
አንድ ወንድም ባለቤቱ ታማ ሆስፒታል ተኝታለች፤ ከአጠገቧ ሆኖ እየጸለየላት ነው።

ጭንቀትን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

ጭንቀት ለልባችን ሸክም ነው። (ምሳሌ 12:25) ጭንቀት ሕይወትህን ከባድ አድርጎብሃል? ‘አሁንስ ከአቅሜ በላይ ነው’ ብለህ ታውቃለህ? ከሆነ አይዞህ! እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ብዙዎቻችን በአካል፣ በአእምሮና በስሜት እንድንዝል የሚያደርጉ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ለምሳሌ የቤተሰባችንን አባል እናስታምም ይሆናል፤ የምንወደውን ሰው በሞት አጥተን ሊሆን ይችላል፤ ወይም በአካባቢያችን የተፈጥሮ አደጋ ደርሶ ይሆናል። ታዲያ እነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጥሩብንን ጭንቀት ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?a

የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ በመመርመር ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዳ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ዳዊት በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ችግሮች አጋጥመውታል፤ ከሞት ጋር የተፋጠጠባቸው ጊዜያትም ነበሩ። (1 ሳሙ. 17:34, 35፤ 18:10, 11) ታዲያ ጭንቀትን እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? እኛስ የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

ዳዊት ጭንቀትን እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው?

ዳዊት ችግሮች በላይ በላይ ተደራርበውበት ነበር። በነፍስ ከሚፈልገው ከንጉሥ ሳኦል እየሸሸ በነበረበት ወቅት ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ዳዊትና ሰዎቹ ከጦርነት ሲመለሱ አንድ የሚያስደነግጥ ነገር አጋጠማቸው፤ ጠላቶቻቸው ንብረታቸውን ዘርፈው፣ ቤቶቻቸውን አቃጥለው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን በምርኮ ወስደው ነበር። ዳዊት ምን ተሰማው? “ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ለማልቀስ አቅም እስኪያጡ ድረስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።” ይህ ያስከተለበት ጭንቀት እንዳይበቃው ደግሞ “ዳዊት ሰዎቹ ሊወግሩት እየተማከሩ” እንደሆነ ሰማ። (1 ሳሙ. 30:1-6) ዳዊት ሦስት ከባድ ችግሮች ተደራረቡበት፦ ቤተሰቡ አደጋ ላይ ናቸው፣ ሰዎቹ ይገድሉኛል ብሎ ሰግቷል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ንጉሥ ሳኦል እያሳደደው ነው። ዳዊት ምን ያህል በጭንቀት እንደሚዋጥ አስበው።

ታዲያ ዳዊት ምን አደረገ? ወዲያውኑ “በአምላኩ በይሖዋ ራሱን አበረታ።” ይህን ያደረገው እንዴት ነው? ዳዊት ይሖዋ እንዲረዳው የመጸለይ እንዲሁም በሕይወቱ ውስጥ ስላደረገለት ነገር የማሰላሰል ልማድ ነበረው። (1 ሳሙ. 17:37፤ መዝ. 18:2, 6) የይሖዋን መመሪያ መጠየቅ እንደሚያስፈልገው ስለተገነዘበ ምን ማድረግ እንዳለበት ይሖዋን ጠየቀ። የይሖዋን መመሪያ ካገኘ በኋላ ደግሞ ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደ። ይሖዋም ከዳዊትና ከሰዎቹ ጋር በመሆን ቤተሰቦቻቸውንና ንብረታቸውን እንዲያስመልሱ ረዳቸው። (1 ሳሙ. 30:7-9, 18, 19) ዳዊት ያደረጋቸውን ሦስት ነገሮች ልብ አልክ? ይሖዋ እንዲረዳው ጸለየ፤ ይሖዋ ቀደም ሲል ባደረገለት ነገር ላይ አሰላሰለ፤ እንዲሁም የይሖዋን መመሪያ ተቀብሎ እርምጃ ወሰደ። እኛስ የዳዊትን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ ሦስት መንገዶችን እንመልከት።

ጭንቀት ሲያጋጥምህ የዳዊትን ምሳሌ ተከተል

ፎቶግራፎች፦ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን የሚረዱን እርምጃዎች። 1. መጸለይ። አንድ ወንድም ባለቤቱ ታማ ሆስፒታል ተኝታለች፤ ከአጠገቧ ሆኖ እየጸለየላት ነው። 2. ማሰላሰል። ወንድም፣ ሆስፒታል ተኝቶ የነበረበትን ጊዜ መለስ ብሎ እያሰበ ነው፤ አንድ ወንድም መጥቶ ያነበበለት ጥቅስ ትዝ አለው። 3. እርምጃ መውሰድ። ወንድም፣ ከታመመችው ባለቤቱ አጠገብ ተቀምጦ አንድ ጥቅስ እያነበበላት ነው።

1. ጸልይ። ጭንቀት በሚሰማን በማንኛውም ጊዜ ይሖዋ እንዲረዳንና ጥበብ እንዲሰጠን መጸለይ እንችላለን። ረዘም ያለ ጸሎት በማቅረብ የልባችንን አውጥተን ስንነግረው ቀለል ይለናል። በወቅቱ ያለንበት ሁኔታ የማይፈቅድልን ከሆነ ደግሞ በልባችን አጭር ጸሎት ማቅረብ እንችላለን። እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ባልን ቁጥር እንደ ዳዊት ዓይነት የእርግጠኝነት ስሜት እንዳለን እናሳያለን፤ ዳዊት “ይሖዋ ቋጥኜ፣ ምሽጌና ታዳጊዬ ነው። አምላኬ የምሸሸግበት ዓለቴ ነው” ብሏል። (መዝ. 18:2) ጸሎት እውነት ይረዳል? ካሊያ የተባለች አቅኚ እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከጸለይኩ በኋላ ውስጤ ይረጋጋል። ጸሎት ስለ ሁኔታዬ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረኝ ይረዳኛል፤ በእሱ ላይም ይበልጥ እተማመናለሁ።” ጸሎት፣ ጭንቀታችንን ለመቋቋም እንዲረዳን ይሖዋ የሰጠን ፍቱን መድኃኒት ነው።

2. አሰላስል። እስቲ ሕይወትህን መለስ ብለህ አስብ፤ ‘ይሖዋ ባይረዳኝ ኖሮ ይህን ፈተና ልወጣው አልችልም ነበር’ ያልክበት ወቅት አለ? ይሖዋ እኛንም ሆነ የጥንት አገልጋዮቹን እንዴት እንደረዳቸው ስናሰላስል ውስጣዊ ጥንካሬ እናገኛለን፤ በእሱም ይበልጥ እንተማመናለን። (መዝ. 18:17-19) ጆሹዋ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ የመለሰልኝ ጸሎቶች ዝርዝር አለኝ። ይህም ይሖዋን አንድ ነገር ለምኜው ልክ የሚያስፈልገኝን ነገር የሰጠኝን ጊዜያት እንዳስታውስ ይረዳኛል።” አዎ፣ ይሖዋ ባደረገልን ነገር ላይ ማሰላሰላችን ኃይላችንን ስለሚያድሰው ጭንቀታችንን ለመቋቋም ብርታት እናገኛለን።

3. እርምጃ ውሰድ። አንድ ነገር ለማድረግ ከመወሰናችን በፊት አስተማማኝ መመሪያ ለማግኘት በአምላክ ቃል ላይ ምርምር ማድረግ እንችላለን። (መዝ. 19:7, 11) በጥቅሶች ላይ ምርምር ማድረግ ጥቅሱ ለእኛ ሁኔታ የሚሠራው እንዴት እንደሆነ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት እንደሚረዳ ብዙዎች ተገንዝበዋል። ጄረድ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ምርምር ማድረግ ጥቅሱን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለመመልከት ይረዳኛል። በመሆኑም ይሖዋ ሊለኝ የፈለገው ምን እንደሆነ መገንዘብ እችላለሁ። ይህም ጥቅሱን ከልቤ እንዳምንበትና ሥራ ላይ ለማዋል እንድነሳሳ ይረዳኛል።” የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ምርምር ስናደርግ እንዲሁም ያገኘነውን መመሪያ ሥራ ላይ ስናውል ጭንቀትን መቋቋም ቀላል ይሆንልናል።

በይሖዋ እርዳታ ይሳካልሃል

ዳዊት ጭንቀትን ለመቋቋም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ ለሚያደርግለት ድጋፍ ያለው አመስጋኝነት እንዲህ እንዲል አነሳስቶታል፦ “በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ። ብርታትን የሚያስታጥቀኝ እውነተኛው አምላክ ነው።” (መዝ. 18:29, 32) የሚደርሱብን ፈተናዎች እንደ ቅጥር እንደ ከበቡን ይሰማን ይሆናል። በይሖዋ እርዳታ ግን እንደ ቅጥር የተጋረጠብንን ማንኛውንም ፈተና ማለፍ እንችላለን! ይሖዋ እንዲረዳን እንጸልይ፤ ባደረገልን ነገር ላይ እናሰላስል፤ እንዲሁም መመሪያውን ተከትለን እርምጃ እንውሰድ። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ጭንቀታችንን ለመቋቋም የሚረዳን ብርታትና ጥበብ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን!

a አንድ ሰው ከመጠን ያለፈ ጭንቀት ካጋጠመው የሕክምና እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልገው ይችላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ