ክራባትን የፈለሰፈው ማን ነው?
በጀርመን የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በመላው ዓለም 600 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች አዘውትረው ክራባት ያደርጋሉ። በጀርመን አገር አንድ ወንድ በአማካይ 20 ክራባቶች ይኖሩታል። በርካታ ወንዶች ክራባታቸውን ሲያስሩ ትንሽ በስጨት ብለው ‘ይህን ነገር ያመጣብን ማን ይሆን?’ ይላሉ። ክራባት የመጣው ከየት ነው?
የክራባት “መገኛ” የመሆንን ክብር ያገኘችው በቤልጅየም የምትገኘው ስቲንከርከ የተባለች ከተማ ነች። በ1692 የእንግሊዝ ወታደሮች በዚህች ከተማ በሰፈሩ የፈረንሳይ ወታደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ፍራንክፉርተር አልገማይነ ዞንታግሳይቱንግ የተባለው የጀርመንኛ ጋዜጣ እንዳለው “[ፈረንሳውያኑ] ወታደሮች ልብሳቸውን በአግባቡ ለመልበስ ጊዜ አላገኙም። ቀልጠፍ ብለው የደንብ ልብሳቸው ክፍል የሆነውን መሐረብ መሳይ ጨርቅ ላላ አድርገው አንገታቸው ላይ ካሰሩት በኋላ ጫፉን ወደ ውስጥ ይከቱት ነበር። እነሆ፣ የክራባት ልደት ሆነ።”
ይሁን እንጂ የእነዚህ ወታደሮች አለባበስ የመጀመሪያው አልነበረም። ስለ ክራባት ታሪክ ጥናት ያደረጉ ምሁራን እንደሚሉት የቻይናዊው የአፄ ቻንግ ወታደሮች (ሺ ሁዋንግ ቲ) ማዕረጋቸውን የሚያመለክት መሐረብ መሳይ ጨርቅ አንገታቸው ላይ ያስሩ ነበር።
ከሁሉ በላይ ዝነኛ የሆነው ግን ለፈረንሳዩ ንጉሥ ለሉዊ አሥራ አራተኛ ይዋጉ የነበሩ ክሮአታውያን ይለብሷቸው የነበሩት የአንገት ልብሶች ናቸው። በፓሪስ በተደረገ የድል ሰልፍ ላይ ፈረንሳውያን በክሮአታያውያኑ የአንገት ልብሶች በጣም በመማረካቸው ክራባት ብለው ጠሯቸው። ክራባት ያሉት ክሮአት ለማለት ሲሆን እነሱም የአንገት ልብስ መልበስ ጀመሩ። ከላይ የተጠቀሰው ጋዜጣ እንዳለው “የአንገት ልብሳቸውን ቋጥረው ለመልበስ የመጀመሪያ የሆኑት የስቲንከርከ ወታደሮች ቢሆኑም ከዚያ ጊዜ ወዲህ በክራባት ማጌጥ በጣም እየተስፋፋ ሄደ።”
በፈረንሳይ አብዮት ወቅት (1789-99) አንድ ሰው የሚከተለው የፖለቲካ ፓርቲ አንገቱ ላይ በሚያስረው ክራባት ቀለም ይታወቅ ነበር። በ19ኛው መቶ ዘመን አለባበስ የሚያሳምሩ የአውሮፓ ማኅበረሰብ አባሎች “ከክራባት ጋር መላመድ ጀመሩ።” ክራባት ከውትድርናና ከፖለቲካ ዓለም ወጥቶ የብዙሐን ወንዶቸ ማጌጫ የሆነው በዚህ ጊዜ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ክራባት በመላው ዓለም በሚገኙ በርካታ ኅብረተሰቦች ውስጥ ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ በአንዳንድ ሁኔታዎች ክራባት ማሰር ግዴታ ሆኗል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Historic Costume in Pictures/Dover Publications, Inc., New York