ከዓለም አካባቢ
የባሪያ ንግድ በብራዚል
“ወደ ብራዚል የተወሰዱት ባሮች ቁጥር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተወሰዱት በአሥር እጥፍ የሚበልጥ ቢሆንም ወደ ብራዚል የተወሰዱት ባሮች በብዛት በመሞታቸው በ1860 በብራዚል የሚገኙ ጥቁሮች ቁጥር በዩናይትድ ስቴትስ ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያነሰ” እንደነበረ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት (WCC) የሚያሳትመው ኢ ኤን አይ ቡለቲን ሪፖርት አድርጓል። በባርነት ከተወሰዱት አፍሪካውያን መካከል 40 ከመቶ የሚሆኑት ገና በጉዞ ላይ ሳሉ መርከብ ውስጥ እንደሞቱ ተገምቷል። አፍሪካውያን ባሮችን ቄሶች “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” ብለው ውኃ በመርጨት በጅምላ ያጠምቋቸው ነበር፤ እንዲህ የሚደረገው ከፍተኛ ዋጋ እንዲያወጡ ሲባል ነበር። በብራዚል ሳልቫዶር ውስጥ “ለዝክር፣ ለንስሐና ለመተራረቂያ” በተዘጋጀው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ ካሜሩናዊው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት መሪ አሮን ቶለን እንደሚከተለው ሲሉ ተናግረዋል:- “ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ተጠያቂዎቹ ወደዚህ ያመጡን ሰዎች ብቻ አይደሉም። እኛ አፍሪካውያንም ተጠያቂዎች ነን። ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን እንደ ሸቀጥ በመሸጥ የገዛ ክብራችንን አዋርደናል።”
ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና
“ደም ወለድ የሆኑ በሽታዎች ያሳደሩት ፍርሃትና ከለጋሾች የተገኘው ደም በጣም አነስተኛ መሆኑ በተቻለ መጠን ለበሽተኛ ደም መስጠትን ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረት እንዲደረግ አነሳስቷል” በማለት ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል ጋዜጣ ዘግቧል። ያለ ደም ሕክምና ማከናወን የሚቻለው በቀዶ ሕክምና ወቅት ብዙ ደም እንዳይፈስ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግና “የይሖዋ ምሥክሮችን ለማከም ሲባል ከዚህ ቀደም የተፈለሰፉትን በርካታ አዳዲስ ዘዴዎች” በመጠቀም መሆኑን ግሎብ ገልጿል። ደም ሳይሰጡ ቀዶ ሕክምና ከሚያደርጉ በርካታ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የሆነው የኦቶዋ ዩኒቨርሲቲ የልብ ሕክምና ኢንስትቲዩት አኔስቴቲስት የሆኑት ዶክተር ጀምስ ኤ ሮብሊ “መቼም በዚህ የሕክምና ዘርፍ አእምሮአችንን እንድንጠቀምበት ያንቀሳቀሱን [የይሖዋ ምሥክሮች] ናቸው ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ድምፅ ያሳምማል?
የብሪታንያው ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ያወጣቸው ጥናታዊ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ሌላው ቀርቶ በአንፃራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ ለሚባለው ድምፅ እንኳ መጋለጥ ሊያሳምምህ ይችላል። የዓለም ጤና ድርጅት የሌሊቱን ክፍለ ጊዜ አስመልክቶ በመመሪያው ላይ ያሰፈረውን አማካኝ የድምፅ መጠን ከእነዚህ ጥናታዊ ግኝቶች በመነሳት እንደገና ለማስተካከል ተገድዷል። በተለይ ልጆች ለአደጋው የተጋለጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚጠቁመው መረጃ ልዩ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው። በሙኒክ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የሚኖሩ ልጆች ከፍተኛ የደም ግፊትና የአድሬናሊን ሆርሞን መጨመር እንደሚታይባቸው አንድ ጥናት አረጋግጧል። በተጨማሪም እነዚህ ልጆች የማንበብና አንድን ነገር ለረጅም ጊዜ በአእምሮአቸው የመያዝ ችሎታቸው እየተዳከመ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ደርሰውበታል። ሰዎች አንድን የሚረብሽ ድምፅ የለመዱት ቢመስላቸውም እንኳ “በሰውነታቸው አሠራር ላይ ምንጊዜም ጉዳት ማስከተሉ የማይቀር ነው። ድምፅ ውጥረት ስለሚፈጥር ሰውነት የኋላ ኋላ እጁን ይሰጣል” ሲሉ በዚህ መስክ ስፔሺያሊስት የሆኑት አርላይን ብሮንዛፍት ተናግረዋል።
የፀረ-ተባይ መድኃኒቶች አደገኝነት
በፊሊፒንስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የሩዝ ምርምር ኢንስቲትዩት እንደሚለው ከሆነ ገበሬዎች ማንኛውም ዓይነት ፀረ-ተባይ መድኃኒት ጨርሶ ባይጠቀሙም እንኳ የሩዝ ምርት መጠን አይቀንስም። በዚህ የምርምር ኢንስትቲዩት ውስጥ የሚሠሩ አንድ ሳይንቲስት በሰብሎች ላይ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶችን በሰፊው መርጨት ትርፉ ብክነት ከመሆኑም በላይ አላስፈላጊ መሆኑን በፊሊፒንስ ለተካሄደው ዓለም አቀፍ የምግብ ጉባኤ አስገንዝበዋል። ገበሬዎች ፀረ-ተባይ መድኃኒቶችን የሚረጩት ትክክለኛ ባልሆነ ጊዜ መሆኑ ብቻ ሳይሆን መገደል የሌለባቸውን ነፍሳት ይገድላሉ ሲል ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎቹ ገበሬዎች ከአየር ጋር በመቀላቀል በቀላሉ ወደ ሰውነት ሊገቡ የሚችሉ ኬሚካሎችንና የሚረጩ መድኃኒቶችን ሲጠቀሙ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ቸል ይላሉ፤ ወይም ደግሞ ፀረ-አረም መድኃኒቶችን ከአፈር ጋር ቀላቅለው በእጃቸው ይረጫሉ። በአሁኑ ጊዜ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶች በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 220,000 ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳርጉና ሦስት ሚልዮን ሰዎችን ደግሞ በከባድ ሁኔታ እንደሚመርዙ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት አድርጓል።
አውሮፓውያን አጫሾች
በዓለም ላይ በነፍስ ወከፍ ብዙ ሲጋራ በማጨስ አውሮፓውያንንና ቻይናውያንን የሚተካከላቸው እንደሌለ በጀርመን ፍራንክፈርት የሚታተመው ናሶሽ ኒዩ ፕሬስ ዘግቧል። በአውሮፓውያን ማኅበረሰብ ውስጥ 42 ከመቶ ወንዶችና 28 ከመቶ ሴቶች አጫሾች ናቸው። ከ25 እስከ 39 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሰዎች መካከል ደግሞ የአጫሾች ቁጥር ከዚህም ከፍ ይላል። ማጨስ፣ በየዓመቱ በጀርመን ውስጥ 100,000 ሰዎችን እንዲሁም በብሪታንያ ደግሞ ሌሎች 100,000 ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት ይዳርጋል። ለብዙ ዓመታት በከባድ የሲጋራ ሱስ ተጠምደው የኖሩት የቼክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ቫክላቭ ሃቬል በቅርቡ የሳንባ ካንሰር ሕክምና ተደርጎላቸዋል። ፕሬዚዳንቱ የማጨስ ልማዱን ማቆም ለሚችል ማንኛውም ሰው ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው ማጨስ ወይስ ጤንነት በመባል ለሚታወቀው የአውሮፓውያን ማኅበር በጻፉት ደብዳቤ መግለጻቸውን ሰዱሽ ዘይቱንግ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተሰነዘሩ አስተያየቶች
ሃያ አንደኛው መቶ ዘመን እየተቃረበ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት ብዙ አስተያየቶች እየጎረፉ ነው። ኒውስ ዊክ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት ሰዎች በሚቀጥለው አንድ መቶ ዓመት ምን ይፈጸማል ብለው እንደሚጠብቁ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል 64 በመቶ የሚሆኑት ጠፈርተኞች ማርስን ይረግጣሉ ሲሉ ተንብየዋል። ሀምሳ አምስት በመቶ የሚያክሉት የሰው ልጅ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ባሉ ሌሎች ቦታዎች መኖር ይጀምራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። ሰባ በመቶዎቹ፣ ሳይንቲስቶች ለኤድስ መድኃኒት ያገኛሉ ብለው ሲያስቡ 72 በመቶዎቹ ለካንሰር መድኃኒት ይገኝለታል ሲሉ ተንብየዋል። አሉታዊ በሆኑ ገጽታዎች ላይ ያተኮሩም ነበሩ፤ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል 73 በመቶ የሚያክሉት በሀብታሞችና በድሃዎች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እንደሚሰፋ ሲናገሩ 48 በመቶዎቹ ደግሞ ባለፉት 100 ዓመታት ከተደረጉት የበለጡ ብዙ ጦርነቶች ይኖራሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። 70 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የሰው ልጅ ከዓለም ላይ ረሃብን ጨርሶ ማስወገድ አይችልም ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል።
የፈረሱ ቃለ መሐላዎች
ጀርመን ውስጥ በጋብቻ ቃለ መሐላቸው የጸኑት ባለ ትዳሮች በጣም ጥቂት ናቸው። ከዚህ የተነሣ ናስውሽ ኑው ፕሬስ ሪፖርት እንዳደረገው የፍቺዎችና ለችግር የሚዳረጉ ሕፃናት ቁጥር በእጅጉ አሻቅቧል። በ1995 ወደ 170,000 የሚጠጉ ጋብቻዎች የፈረሱ ሲሆን ይህም የ142,300 ሕጻናትን ሕይወት የሚያናጋ ሆኗል። ለዚህ ችግር የተጋለጡት ልጆች ቁጥር ከቀደሙት ዓመታት 5 በመቶ ጨምሯል። እንደ ጋዜጣው ገለጻ በ1950 ከተፈጸሙት የጋብቻ ቃለ መሐላዎች መካከል በቀጣዮቹ 25 ዓመታት ውስጥ ከአሥሩ አንዱ ፈርሷል። በ1957 ከተጋቡት ባልና ሚስት መካከል በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከስምንቱ አንዱ ጋብቻ ፈርሷል። በ1965 ከተፈጸሙት ጋብቻዎች መካከል በቀጣዮቹ 25 ዓመታት ውስጥ የፈረሱት ቁጥር ደግሞ ከአምስት አንድ ነበር። ከ1970 ወዲህ ከተጋቡት መካከል ከሦስት ትዳሮች አንዱ ፈርሷል።
ከሰማይ የወረደ ገንዘብ?
በፍሎሪዳ ሚያሚ ውስጥ በኦቨርታውን መንደር የሚኖሩ ድሃ ሰዎች ገንዘብ ድንገት ከሰማይ ወረደልን ብለው በደስታ ፈንድቀው ነበር። ለካስ ገንዘቡ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን በሠፈሩ አቅራቢያ በሚያልፍ እንደ ድልድይ ከፍ ብሎ በተሠራ ተደራቢ መንገድ ላይ ይጓዝ የነበረ ጥይት የማይበሳው አንድ ከባድ መኪና ባጋጠመው አደጋ ምክንያት ጭኖት ከነበረው 3.7 ሚልዮን ዶላር ውስጥ የተበተነ ገንዘብ ኖሯል። የተበተነውን ገንዘብ ለመልቀም ወዲያና ወዲህ ይራወጡ የነበሩት ሰዎች ቢያንስ ቢያንስ 100 እንደሚሆኑ ፖሊስ የገመተ ቢሆንም ቁጥራቸው ከዚህ ሳይልቅ አይቀርም። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው “የሚያሚ ፖሊስ ገንዘቡን የወሰዱት ሰዎች በስርቆት ወንጀል ክስ ሳይመሰረትባቸው በፊት በ48 ሰዓት ውስጥ ገንዘቡን እንዲመልሱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።” ሆኖም የተሰጠው የሰዓት ገደብ እስካበቃበት ጊዜ ድረስ የወሰዱትን ገንዘብ የመለሱት ሦስት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ የደረሰበት ያልታወቀ 500,000 ዶላር ይቀር ነበር። አንድ የ18 ዓመት ወጣት “ድሮስ ምን እንዲያደርጉ ትጠብቃላችሁ? ገንዘቡ እኮ የተበታተነው ሰዎቹ ግቢ ውስጥ ነው” ሲል እንደተናገረ ተዘግቧል።
እየሞተ ያለ ባሕር
ሙት ባሕር እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት እንደዘገበው “ቀድሞም ቢሆን በምድር ላይ ካሉት የውኃ አካላት ሁሉ የመጨረሻው ዝቅተኛ ቦታ (በዓለም ላይ ካሉት ውቅያኖሶች አማካይ የባሕር ወለል በታች 403 ሜትር) ላይ የሚገኘው የሙት ባሕር ወለል እየቀነሰ መጥቷል።” ለምን? ትነት ከሚያሳድረው ተጽዕኖ በተጨማሪ ለሙት ባሕር ዋነኛ ምንጭ በሆነው በዮርዳኖስ ወንዝ ላይ የተመሠረቱት በርካታ የመስኖ ልማቶችና ግድቦች የውኃው ኃይል እንዲቀንስ አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ “ማዕድኖችን ለማጥለል ሲሉ የሙት ባሕርን ውኃ ወደ ትናንሽ ባዶ ኩሬዎች በማፍሰስ እንዲተን የሚያደርጉት የኬሚካል ኢንዱስትሪዎችም የውኃው መቀነስ እንዲፋጠን ምክንያት ሆነዋል።” ከ1950ዎቹ አጋማሽ ወዲህ የሙት ባሕር ወለል ከነበረበት በ18 ሜትር ቀንሷል። ችግሩን ለማስተካከል ይረዳል ተብሎ የታመነበትና ገና እየተመከረበት ያለው እርምጃ 180 ኪሎ ሜትር አቋርጦ ከቀይ ባሕር ውኃ የሚመጣበት ቦይ መቆፈር ነው። ውኃው ወደ ሙት ባሕር እንዲገባ ቀጥታ ወደ ጎን 123 ሜትር ከዚያም ቁልቁል 525 ሜትር መገፋት ይኖርበታል።
በቀዶ ሕክምና ወቅት የሙቀት መጠናቸው እንዳይቀንስ የተደረገ ሕሙማን
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ አኔስቴዝዮሎጂስት፣ በዳንኤል ሴስለር የተካሄደ አንድ አዲስ ጥናት አየር ወለድ የሆኑ ባክቴሪያዎችን እድገት ለመግታት ሲባል ቀዶ ሕክምና የሚደረግባቸው የሆስፒታል ክፍሎች ቀዝቃዛ እንዲሆኑ መደረጉ ሕሙማን ለኢንፌክሽን የሚጋለጡበትን ሁኔታ በሦስት እጥፍ እንደሚያሳድገው ይገልጻል። ዶክተር ሴስለር እንዳሉት “የቁስል ኢንፌክሽንን የሚያስከትለው ነገር አየር ውስጥ ያሉት ባክቴሪያዎች ሳይሆኑ በሽተኛው በቆዳው ላይ ወይም ደግሞ በሰውነቱ ውስጥ ያሉትን ባክቴሪያዎች የመቋቋም አቅሙ ደካማ መሆን ነው።” ቀዶ ሕክምና የሚካሄድባቸው ክፍሎች ቀዝቃዛ መሆን የበሽተኛውን የሰውነት ሙቀት መጠን ከ1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ እንዲቀንስ ሊያደርገው ይችላል። የሰውነት ሙቀት መጠን ዝቅተኛ መሆን ደግሞ ኢንፌክሽንን ለመከላከል እጅግ አስፈላጊ የሆነው ኦክስጂን የያዘ ደም እንደ ልብ እንዳይዘዋወር ያደርገዋል። “የሰውነት የሙቀት መጠን በጣም ሲቀንስ በሽታን የሚከላከሉት ሕዋሶችና ኢንዛየሞች ሥራቸውን በሚገባ ማከናወን ይሳናቸዋል” ሲሉ ሴስለር ተናግረዋል። ሴስለርና የሥራ ባልደረቦቻቸው በቀዶ ሕክምና ወቅት የሰውነት ሙቀት መጠናቸው እንዳይቀንስ የተደረጉ በሽተኞች ለኢንፌክሽን የመጋለጣቸው ሁኔታ አነስተኛ ከመሆኑም በላይ የሰውነታቸው የሙቀት መጠን ከቀነሰባቸው ሕሙማን ሦስት ቀን ገደማ አስቀድመው ተሽሏቸው ከሆስፒታል እንደሚወጡ መገንዘብ ችለዋል።