የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 3/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የዓለም የንጽሕና አጠባበቅ ደረጃ አሽቆልቁሏል
  • “የሞት መልእክተኞች”
  • እንግዳ የሆነ ወዳጅነት
  • ቤትን የመሰለ ነገር የለም
  • ረጅም ዕድሜ መኖር
  • ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ልማድ
  • ዛሬም የቀዳሚነቱን ሥፍራ እንደያዘ ነው
  • ኮሌራ አገረሸ
  • ሕፃናት ምን ይመገቡ?
  • የኤድስ ተጠቂ የሆኑ እናቶች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል
    ንቁ!—2000
  • በጉዞ ላይ ያለ ሠራዊት!
    ንቁ!—2003
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1996
  • የእናት ጡት ወተት የሚመረጥበት ምክንያት
    ንቁ!—1994
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 3/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

የዓለም የንጽሕና አጠባበቅ ደረጃ አሽቆልቁሏል

“ከዓለም ሕዝብ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው ማለትም ወደ ሦስት ቢልዮን የሚጠጋ ሕዝብ ተራ የመጸዳጃ ቤት እንኳ የለውም” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ዩኒሴፍ (የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት) የሚያካሂደው ፕሮግረስ ኦቭ ኔሽንስ የተባለው ዓመታዊ ጥናት አካል የሆኑት እነዚህ ግኝቶች “የንጽሕና አጠባበቅን የሚያሳዩት አኃዛዊ መረጃዎች በዓለም ላይ እየተሻሻሉ ሳይሆን እየከፉ ከሚሄዱት ነገሮች መካከል” መሆናቸውን የጠቆሙ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል ለድኾች ንፁሕ የመጠጥ ውኃ በማቅረብ ረገድ መሻሻል ያደረጉ አንዳንድ አገሮች እንኳ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴዎችን በሚመለከት እጅ አጥሯቸዋል። ይህ መሠረታዊ የሆነ የንጽሕና መሥፈርት ሳይሟላ መቅረቱ ደግሞ አዳዲስ ወረርሽኞች እንዲዛመቱና የቆዩትም እንዲያንሠራሩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ሪፖርቱ አስታውቋል። በየዓመቱ ከንጽሕና ጉድለት ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች ምክንያት ከሁለት ሚልዮን የሚበልጡ ልጆች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ተገምቷል። ይህን ጥናት የመሩት አክታር ዛሚድ ካን እንዲህ ብለዋል:- “የንጽሕና አጠባበቅ ዘዴህ ከመካከለኛው ዘመን ያልተሻለ ከሆነ የመካከለኛው ዘመን በሽታዎች ይይዙሃል።”

“የሞት መልእክተኞች”

የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) በ1997 ባወጣው ሪፖርቱ ላይ የበለጸጉት የምዕራባውያን አገሮች በታዳጊ አገሮች ላይ በበሽታ ረገድ “ድርብ ጫና” እየፈጠሩ ነው ሲል ገልጿል። የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ እንደገለጸው ታዳጊዎቹ አገሮች የምዕራባውያኑን አኗኗር በመኮረጅ ሲጋራ ስለሚያጨሱ፣ ከፍተኛ የካሎሪና የስብነት መጠን ያላቸውን ምግቦች ስለሚመገቡና የአካል እንቅስቃሴ ስለማያደርጉ እንደ ልብ ሕመም፣ በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ (stroke)፣ የስኳር በሽታ ያሉ እንዲሁም አንዳንድ የካንሠር ዓይነቶች እየተበራከቱባቸው ነው። በዓለም ዙሪያ ሲታይ ሰዎች ከበፊቱ ይበልጥ ረጅም ዕድሜ ቢኖሩም የዓለም የጤና ድርጅት ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ፖል ክሌሁስ ይህ ‘የሕይወት ለዛ የሌለው ባዶ ሽልማት ነው’ ብለውታል። አክለውም “እኛ የሞት መልእክተኞች መሆናችንን የሚናገሩ ሰዎች ትክክል ናቸው” ብለዋል። የዓለም የጤና ድርጅት፣ ሰዎች ጤናማ የአኗኗር ልማድ እንዲያዳብሩ ለማበረታታት ሰፊ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ እንዲካሄድ እየጎተጎተ ነው። አለዚያ ግን “በምድር ዙሪያ መከራ ይነግሣል” ሲል ገልጿል።

እንግዳ የሆነ ወዳጅነት

ሳይንቲስቶች በጉንዳኖችና በአፍሪካ የግራር ዛፎች መካከል ባለው ዝምድና ለረጅም ጊዜ ሲደነቁ ቆይተዋል። ዛፎቹ ለጉንዳኖቹ የምግብና የመጠለያ ምንጭ ናቸው። ጉንዳኖቹ ደግሞ በተራቸው ዛፎቹን ሊያጠፉ የሚችሉ ነፍሳትን ከመብላታቸውም በተጨማሪ በቅጠሎቹ ላይ የሚንሸራሸሩትን እንስሳት ይነክሳሉ። ዛፎቹ በሕይወት እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸው ይህ የጉንዳኖቹ ጥበቃ ይመስላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ዛፎች ዘር ለማራባት በራሪ ነፍሳት ያስፈልጓቸዋል። ታዲያ የአበባውን ዘር የሚያራቡት ነፍሳት ሥራቸውን እንዴት ማከናወን ይችላሉ? ኔቸር የተባለው የሳይንስ ጋዜጣ እንዳለው ከሆነ ‘የአበባዎቹ መራቢያ ጊዜ ሲደርስ’ ዛፎቹ ጉንዳኖቹን የሚያባርር ኬሚካል ያፈልቃሉ። ይህም ነፍሳቱ “በዚህ ወሳኝ ወቅት” ወደ ዛፉ እንዲመጡ በር ይከፍትላቸዋል። አበቦቹ ከተራቡ በኋላ ጉንዳኖቹ እንደገና ወደ ጥበቃ ሥራቸው ይመለሳሉ።

ቤትን የመሰለ ነገር የለም

ወላጆች ወደ ሥራ ሲሄዱ ልጆቻቸው በልጆች ማዋያ እንዲጠበቁላቸው ማድረጋቸው ለልጆቹ ጥሩ ነውን? ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦቭ ቻይልድ ሄልዝ ኤንድ ሂውማን ዴቨሎፕመንት በተባለው ድርጅት አማካኝነት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተካሄደው ጥናት ይህንን ጉዳይ ለማረጋገጥ የታለመ ነበር። ለልጆች የሚደረገውን እንክብካቤ የሚያጠኑ በ14 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ የታወቁ ተመራማሪዎች በ1,364 ልጆች ላይ ጥናት ያደረጉ ሲሆን ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ ሦስት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ያላቸውን ሁኔታ ተከታትለዋል። ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት ልጆች በቤት ውስጥ የእናቶቻቸውን እንክብካቤ ያገኙ ሲሆኑ የተቀሩት ግን በልጆች ማዋያ ተቋማት ወይም በቅጥር ሞግዚቶች ቤት እንክብካቤ እየተደረገላቸው ያደጉ ናቸው። ውጤቱስ? ታይም መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ተመራማሪዎቹ ለልጆቹ የሚደረገው እንክብካቤ አነስተኛ ከሆነባቸው ጣቢያዎች ይልቅ ከፍተኛ ደረጃቸውን በጠበቁት ማለትም ልጆቹ የዐዋቂዎችን የቅርብ ክትትል በሚያገኙባቸው የልጆች ማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ የነበሩት ልጆች በቋንቋና በትምህርት ችሎታ ረገድ ትንሽ ብልጫ እንዳላቸው ተረድተዋል። ይሁን እንጂ በልጆቹ አእምሯዊና ስሜታዊ ብስለት ረገድ የልጆች ማቆያ ጣቢያዎች የሚኖራቸው ውጤት የቤተሰብ ሕይወት ከሚኖረው ውጤት ጋር ሲወዳደር እጅግ አነስተኛ ነው ወደሚል መሠረታዊ መደምደሚያ ደርሰዋል። . . . ተመራማሪዎቹ እንዳሰሉት በልጆቹ መካከል እስከ አንድ በመቶ የሚደርስ ልዩነት እንዲኖር ምክንያት የሆነው በልጆች ማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ ያለው ሁኔታ ሲሆን 32 በመቶ የሚያክለው ልዩነት የተከሰተው ግን በቤተሰቦቻቸው ውስጥ ከሚንጸባረቀው የባሕርይ ልዩነት የተነሣ ነው። ታዲያ መልእክቱ ምንድን ነው? ትልቅ ሚና የሚጫወተው የትምህርት ማዕከል ቤት ነው።”

ረጅም ዕድሜ መኖር

ጤናማ ለመሆንና ረጅም ዕድሜ ለመኖር የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው? “ከአካል እንቅስቃሴ ወይም ከአመጋገብ ልማድ ይበልጥ ጤናማ እንድንሆን ትልቅ ድርሻ የሚያበረክተው ከሥነ ልቦናዊ ውጥረት በእጅጉ ነፃ የሆነና ተለዋዋጭ ያልሆነ ስሜት ይዘን ለመኖር መጣራችን ነው” ሲሉ በቦስተን የሚገኘው የብሪጋም የሴቶች ሆስፒታል ዶክተር የሆኑት ጆርጅ ቬላንት ተናግረዋል። ቬላንት ለዚህ ሐሳብ መነሻ የሆናቸው ከ1942 ጀምሮ በ230 ወንዶች ላይ እየተደረገ ያለው ቀጣይነት ያለው ጥናት ነው። በ52 ዓመት ዕድሜያቸው በጥሩ ጤና ላይ ይገኙ የነበሩት ወንዶች “ውጥረት ያለባቸው” (የአልኮል መጠጦችን አላግባብ ተጠቅመዋል፣ ስሜት የሚያረጋጉ መድኃኒቶችን አዘውትረው ወስደዋል ወይም የሥነ አእምሮ ሐኪም አማክረዋል)፣ “ውጥረት የሌለባቸው” (አልኮል አላግባብ ተጠቅመው አያውቁም፣ ተለዋዋጭ ስሜታቸውን ለማረጋጋት መድኃኒቶች ወስደው አያውቁም ወይም የሥነ አእምሮ ሐኪም አማክረው አያውቁም) እንዲሁም “መካከለኞች” (በሁለቱ መደብ መካከል ያሉ) ተብለው ለሦስት ተከፈሉ። [ውጥረት የሌለባቸው] ተብለው ከተመደቡት መካከል በ75 ዓመት ዕድሜያቸው የሞቱት 5 በመቶ የሆኑት ብቻ ሲሆኑ በመካከለኛው መደብ ውስጥ ከነበሩት መካከል 25 በመቶው እንዲሁም ውጥረት ያለባቸው ከተባሉት መካከል 38 በመቶው እንደሞቱ ሳይንስ ኒውስ ሪፖርት አድርጓል። ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓት መከተልና ዘወትር የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ለጥሩ ጤንነት እንደሚረዳ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ሳይንስ ኒውስ እንዳለው ከሆነ “ቢያንስ ወንዶች ረጅም ዕድሜ መኖራቸው የተመካው ከልክ በላይ መጨነቅን ለማስወገድ የሚረዳው የስሜት መረጋጋት እንዲኖራቸው በማድረጋቸው ላይ ይመስላል።”

ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ልማድ

ማጨስ ወጪ ይጠይቃል። ምን ያህል? ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ካሊፎርኒያ በርክሌይ ዌልነስ ሌተር እንዳለው ከሆነ ለረጅም ጊዜ የምታጨስ ከሆነ ዋጋው የኋላ ኋላ እስከ 230,000 ወይም 400,000 የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል። ይህ እንግዲህ በቀን በምታጨሰው ፓኮ መጠን (አንድ ወይም ሁለት) የሚወሰን ይሆናል። ዌልነስ ሌተር እንዲህ ይላል:- “በወጣትነት ዕድሜህ ላይ ነው ያለኸው እንበል፤ ዛሬ ሲጋራ ማጨስ ጀምረህ ለ50 ዓመታት አጨስክ፤ ለዚያውም ከዚያ በፊት ካልገደለህ ነው። በ2.50 የአሜሪካ ዶላር እየገዛህ በቀን አንድ ፓኮ ብታጨስ (ነገሩ እንዳይወሳሰብ ከጊዜ በኋላ የሚኖረውን የዋጋ ጭማሪ እንተወው) በዓመት 900 ዶላር ይሆናል፤ ከ50 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ደግሞ 45,000 የአሜሪካ ዶላር ታወጣለህ። ይህን ገንዘብ ባንክ ብታስቀምጠውና በየዓመቱ 5 በመቶ ወለድ ብታገኝ የመጀመሪያው ገንዘብ በትንሹ አራት እጥፍ ሆኖ ታገኘዋለህ።” እንደ ሕይወት ኢንሹራንስና ሌሎች የንጽሕና ወጪዎች (ለቤት፣ ለልብስ እና ለጥርስ) ያሉ ተጨማሪ ሂሳቦች የገንዘቡን መጠን ከላይ ወደተጠቀሰው አኃዝ ያደርሱታል። ዌልነስ ሌተር እንዲህ ሲል ጨምሮ ገልጿል:- “ይህ እንዲያውም የጤና ኢንሹራንስህ ሁሉንም ወጪ የማይሸፍን ከሆነ የማጨስ ልማድህ የሚያስከትለውን የሕክምና ወጪ ሳይጨምር ነው።”

ዛሬም የቀዳሚነቱን ሥፍራ እንደያዘ ነው

“ከየትኛውም ሌላ መጽሐፍ ይበልጥ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች እየታተሙ ነው” ሲል ኢ ኤን አይ ቡለቲን ዘግቧል። ከፍተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርጭት ያላቸው አገሮች ቻይና፣ ዩናይትድ ስቴትስና ብራዚል ናቸው። ከተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት (UBS) የወጣው ሪፖርት እንደሚጠቁመው በ1996 ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በ19.4 ሚልዮን ቅጂዎች ተሠራጭቷል። ይህን ያህል ቁጥር ሲሠራጭ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በ1995 ከነበረው አኃዝ 9.1 በመቶ ብልጫ ነበረው። የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት የኅትመት አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ጆን ቦል “በተወሰኑ የምድር ክፍሎች ሥርጭቱ አስገራሚ እድገት ቢያሳይም እያንዳንዱ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎችን በቀላሉ እንዲያገኝ ለማድረግ ከፈለግን ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።

ኮሌራ አገረሸ

ኮሌራ ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት ጠፍቶ ከቆየ በኋላ በደቡብ አሜሪካ በሚያስደነግጥ ሁኔታ አገርሽቷል። የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት “በደቡብ አሜሪካ ከ1991 አንስቶ 1.4 ሚልዮን ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ ሪፖርት ሲደረግ ለ10,000 ሰዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል” ሲል ዘግቧል። የጤና ጥበቃ ባለ ሥልጣኖችን ጭንቀት ይበልጥ ያባባሰው ደግሞ በ1992 በሕንድ፣ በባንግላዴሽና በአጎራባች አገሮች ውስጥ አዲስ ዓይነት የኮሌራ አስተላላፊ ባክቴሪያ ብቅ ማለቱ ነው። በእነዚህ አገሮች ውስጥ እስከ አሁን ድረስ 200,000 የሚያክሉ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል። ኮሌራ ከባድ የተቅማጥ በሽታ ሲሆን በበሽታው ከተያዙት መካከል ተገቢውን ሕክምና ካላገኙ እስከ 70 በመቶ የሚያክሉት ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ። ይሁንና መድኃኒት ከመፈለግ ይልቅ አስቀድሞ መከላከሉ የተሻለ ይሆናል። የሚጠጡትን ውኃና ወተት ማፍላትና ዝንቦችን ማስወገድ እንዲሁም ሳይበስሉ የሚበሉ ምግቦችን ክሎሪን ባለው ውኃ ማጠብ ለጥንቃቄ የሚረዱ መሠረታዊ እርምጃዎች ናቸው።

ሕፃናት ምን ይመገቡ?

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው “ላለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ዶክተሮችና የሕዝብ ጤና ጣቢያዎች በድኻ አገሮች ውስጥ ለሚገኙ አዳዲስ እናቶች “የልጆቻችሁን ጤና ለመጠበቅ ከፈለጋችሁ ጡት አጥቧቸው” እያሉ አንድ ዓይነት ምክር ሲሰጡ ቆይተዋል። “አሁን ግን የኤድስ ወረርሽኝ ይህን ምክር መና አስቀርቶታል። በኤድስ ቫይረስ የተለከፉ እናቶች በጡት ወተት አማካኝነት በማይናቅ መጠን በሽታውን ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ጥናቶች እየጠቆሙ ነው። . . . የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርቡ እንደገመተው ከሆነ በኤች አይ ቪ ቫይረስ ከተለከፉት ሕፃናት መካከል አንድ ሦስተኛ የሚያክሉት በቫይረሱ የተያዙት በእናቶቻቸው የጡት ወተት አማካኝነት ነው።” ያለው አማራጭ ለሕፃናት የሚዘጋጅ ወተት መጠቀም ነው። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን የራሱ ችግሮች አሉት። በብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ እናቶች ሌላ ወተት ለማግኘትም ሆነ ጡጦዎችን ለመቀቀል አቅማቸው የማይፈቅድላቸው ከመሆኑም ሌላ ንጹሕ ውኃ የማግኘት ችግር አለባቸው። ከዚህ የተነሣ ሕፃናት በተቅማጥ፣ በሆድ ድርቀት እንዲሁም በመተንፈሻና በምግብ መውረጃ አካላት ላይ በሚከሰቱ በሽታዎች ይሰቃያሉ። ድኻ የሆኑ ቤተሰቦች ወተቱ ላይ ብዙ ውኃ በመጨመር ስለሚያቀጥኑት ልጆቹ የተመጣጠነ ምግብ ሳያገኙ ይቀራሉ። የጤና ጥበቃ ባለ ሥልጣናት ለእነዚህ ሁለት አንገብጋቢ ጉዳዮች እልባት ለመስጠት እየጣሩ ነው። በዓለም ዙሪያ በእያንዳንዱ ዕለት ከ1,000 የሚበልጡ ሕፃናትና ልጆች በኤች አይ ቪ ቫይረስ ይለከፋሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ