ከዓለም አካባቢ
ተጨማሪ የሳተርን ጨረቃዎች ተገኙ
የሐብል የጠፈር ቴሌስኮፕ ያነሳቸው ፎቶግራፎች ከዚህ በፊት የማይታወቁ፣ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ጨረቃዎች በሳተርን ዙሪያ እንደሚዞሩ አሳይቷል። ፎቶግራፎቹ የተነሱት ምድር የሳተርንን ቀለበት ከጠርዝ ብቻ ለመመልከት በምትችልበት ጊዜ ነው። ይህ ሁኔታ ብዙ ጊዜ የማያጋጥም ሲሆን በዚህ ጊዜ ከቀለበቱ የሚንጸባረቀው ብርሃን ደከም ያለ ስለሚሆን ጨረቃዎቹን ለማየት ይበልጥ ቀላል ይሆናል። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ጨረቃዎቹ ከ11 እስከ 64 ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳላቸው ይገምታሉ። አዲስ የተገኙት ጨረቃዎች ሳተርንን የሚዞሩት ከፕላኔቷ እምብርት ከ136,000 እስከ 182,000 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ርቀት ነው። ይህ ርቀት በምድርና በጨረቃዋ መካከል ካለው የ400,000 ኪሎ ሜትር ርቀት በጣም የቀረበ ነው። ሳተርን ከአንድ ቢልዮን ኪሎ ሜትር በላይ ከምድር ትርቃለች።
የሳንባ ነቀርሳ፣ “በመላው ዓለም ላይ የመጣ አደጋ”
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው በየዓመቱ በሳንባ ነቀርሳ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በኤድስ፣ በወባና በሌሎች የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ከሚሞቱ ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ይበልጣል። በእያንዳንዱ ሴኮንድ በሳንባ ነቀርሳ የሚለከፍ ሰው አለ። የሳንባ ነቀርሳ የሚያስይዘው ባክቴሪያ በሳል ወይም በማስነጠስ ሊጋባ ይችላል። የዓለም ጤና ድርጅት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት 300 ሚልዮን ሰዎች በበሽታው ሲለከፉ 30 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በዚሁ በሽታ ጠንቅ ይሞታሉ ብሎ ያስባል። ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ በማንኛውም ዓይነት ፀረ ሳንባ ነቀርሳ መድኃኒት የማይደፈር የሳንባ ነቀርሳ ዓይነት እየተስፋፋ መሄዱ ነው። በዚህ ምክንያት የዓለም ሕዝብ ፈውስ በማይገኝለት የሳንባ ነቀርሳ የመያዝ አደጋ ተደቅኖበታል። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው “በሳንባ ነቀርሳ ከሚለከፉት ሰዎች መካከል በበሽታው የሚያዙት ወይም በሽታውን ለሌላ ሰው የሚያስተላልፉት ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ይህ የሆነው የሰውነት በሽታ ተከላካዮች ባክቴሪያዎቹን አጥምደው ስለሚይዟቸው ነው።” ቢሆንም የዚህ በሽታ ወረርሽኝ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ ምክንያት የዓለም ጤና ድርጅት “በመላው ዓለም ላይ የመጣ አደጋ” ብሎታል። በዓለም ጤና ድርጅት ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ መግለጫ ሲሰጥ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።
አለ ዕድሜ እናት መሆን
በ1994 የብራዚል የጂኦግራፊና የስታትስቲክስ ተቋም እንዳስታወቀው በብራዚል አገር 15 ዓመት ያልሞላቸው 11,457 ወጣት ሴቶች ልጅ ወልደዋል። ይህን የመሰለው ያለ ዕድሜ እናት መሆን ባለፉት 18 ዓመታት በ391 በመቶ ሲያድግ ጠቅላላው የሕዝብ ቁጥር በዚሁ ጊዜ ውስጥ ያደገው 42.5 በመቶ ብቻ ነው። ከ15 እስከ 19 የዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ እናቶች የሆኑት ሴቶች ቁጥር 60 በመቶ አድጓል። የሪዮ ዲ ጃኔይሮ ፌዴራል ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሪካርዶ ሬጎ ባሮስ “ወጣቶች በአካባቢያቸው፣ በቴሌቪዥን፣ በመጻሕፍትና በመጽሔቶች እየተገፋፉ ገና በአፍላ ዕድሜያቸው ሩካቤ ሥጋ ይፈጽማሉ” በማለት ማብራራታቸውን ቬጃ የተባለው መጽሔት ገልጿል። ሌላው ባለሙያ ደግሞ ወላጆችና ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን ስለ እነዚህ ጉዳዮች እንዴት ሊያስተምሩ እንደሚችሉ ግራ ተጋብተዋል ብለዋል።
የብልግና ጠባይ በሴቶች ዘንድ እየተስፋፋ ሄዷል
የብሪስበን ሳንደይ ሜይል ጋዜጣ ሪፖርት ባደረገው መሠረት በአውስትራሊያ ጸያፍ ቃላት የሚናገሩ ወጣት ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። የአውስትራሊያ ዘመናዊ ቋንቋዎች ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ማክስ ብራንድል እንዲህ በማለት ያብራራሉ:- “በአሁኑ ጊዜ ሴቶችን ከወንዶች በምናወዳድርበት ጊዜ ከቀድሞው ይበልጥ ይጠጣሉ፣ ያጨሳሉ። በተጨማሪም ከቀድሞው ይበልጥ በብልግና ቃላት ይጠቀማሉ። በዚህ ምክንያት በወንዶችና በሴቶች መካከል የነበረው መተፋፈርና መከባበር መጥፋቱ ያሳዝናል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በብልግና ቃላት ሲናገሩ ከዚህ በፊት እናውቀው የነበረው የፍቅር ግንኙነት ይጠፋል። የቀደሙት ትውልዶች ይጠቀሙባቸው የነበሩት የፍቅር ቃላት በአሁኑ ኅብረተሰብ ውስጥ ቦታ የላቸውም። በአሁኑ ጊዜ ጸያፍ ንግግር በወጣቶች መካከል ተስፋፍቶ አገኛለሁ።”
ጳጳሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው መሆኑን ገለጹ
ፑሎስ ማር ፑሎስ የተባሉት ኔስቶሪያዊ ጳጳስ በሕንድ አገር “ለክርስቲያኖች ጋብቻና ፍቺ መሠረት ስለሚሆኑ ሕጎች” በተዘጋጀ ሴሚናር ላይ ባደረጉት ንግግር መጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕግጋት መጽሐፍ አድርጎ መመልከት እንደማይቻል ገልጸዋል። በኢንድያን ኤክስፕሬስ ላይ እንደተዘገበው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቺ የሚሰጠው ትምህርት ሊሻር የማይችል ነው ማለት ዘመናዊው ሰው በባልና ሚስት መካከል ያለውን ዝምድና በመረዳት ረገድ የደረሰበትን እድገት እንደ መካድ ይቆጠራል ብለዋል። በኤክስፕሬስ ሪፖርት መሠረት ጳጳሱ አንድ የሂንዱ ምሁር የተናገሩትን በመጥቀስ እያንዳንዱ ቅዱስ ጽሑፍ ሁለት ጎኖች እንዳሉትና አንደኛው ጎን ጽሑፉ በተጻፈበት አገርና ጊዜ ይኖሩ በነበሩ ሰዎች አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ፣ ጊዜያዊና ጠፊ ሲሆን ሌላው ጎን ግን በማንኛውም ዘመንና አገር ለሚኖሩ ሰዎች ተፈጻሚነት ያለው ዘላለማዊና ሊጠፋ የማይችል ነው ብለዋል። ጳጳሱ በመቀጠል “በመጽሐፍ ቅዱስ ረገድም ፍሬውን ከገለባ መለየት ይኖርብናል። ዘላቂነት ያለውን እውነት ከባሕላዊ አስተሳሰብ መለየትና . . . ለሕይወታችን መመሪያ የሚሆነውን መወሰን ይገባናል” ብለዋል።
የሐሳብ ግንኙነት አያደርጉም
የብሪስበን አውስትራሊያ ጋዜጣ የሆነው ዘ ኩሪየር ሜይል በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከአባቶቻቸው ጋር ትርጉም ያለው ውይይት በበቂ መጠን እንደማያደርጉ የተረጋገጠ መሆኑን ዘግቧል። ጥናቱ እንዳመለከተው በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆች መካከል አብዛኞቹ ከአባቶቻቸው ጋር በየቀኑ የሚያሳልፉት ጊዜ ከ15 ደቂቃ ያነሰ ሲሆን ከእናቶቻቸው ጋር ግን አንድ ሰዓት ለሚያክል ጊዜ ይነጋገራሉ። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ሥነ ምግባርን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች እምብዛም የማይወያዩ ሲሆን የሚያዩዋቸውንም የቴሌቪዥንና የቪዲዮ ፕሮግራሞች አይቆጣጠሩም። በወንዶች ልጆችና በአባቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚያተኩሩት እንደ መኪናና ስፖርት ባሉት ተራ ነገሮች ላይ ነው። ከእናቶች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ደግሞ በጓደኞች፣ በትምህርት ቤትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን ጥልቀት ስላላቸው ቁምነገሮች እምብዛም አይነጋገሩም። የአባቶችና የሴት ልጆች ጭውውት ደግሞ ከመቀላለድና ከመላፋት አያልፍም።
የትራፊክ አደጋ የሚደርሰው ለምንድን ነው?
የብራዚል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው አንድ ጥናት 90 በመቶ የሚሆኑ አደጋዎች የሚደርሱት አሽከርካሪዎች በሚፈጽሙት ስህተት ወይም ቸልተኝነት እንደሆነ ያመለክታል። በዚህ ሪፖርት መሠረት አሽከርካሪዎች ቀጥ ባለ ጎዳና ወይም በጠራ የአየር ሁኔታ በሚነዱበት ጊዜ አደጋ ይደርስብናል ብለው አያስቡም። በተጨማሪም ሪፖርቱ በመንገድ ብልሽትና በመኪና ጉድለት ምክንያት የሚፈጠሩ አደጋዎች በብራዚል አገር በየዓመቱ 25,000 ለሚያክሉ ሰዎች መሞትና 350,000 ለሚያክሉ ሰዎች አካላዊ ጉዳት ምክንያት እንደሚሆኑ አመልክቷል።
መስቀል፣ የዓመፅ ምልክት ነው?
ዘ ዳላስ ሞርኒንግ ኒውስ እንደዘገበው አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሊቃውንት መስቀል የዓመፅ ምልክት በመሆኑ የክርስትና ምልክት መሆን የለበትም ይላሉ። እነኚህ ሊቃውንት የኢየሱስን አሟሟት ሳይሆን አኗኗሩን የሚያንጸባርቅ ምልክት ቢመረጥ የተሻለ ይሆናል ይላሉ። በማዲሰን ኒው ጀርሲ የሚገኘው የድሪው ዩኒቨርሲቲ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ካተሪን ኬለር መስቀል “የሞትን አምልኮ ያስፋፋል። የሞት ቅጣት የሚፈጸምበት የኤሌክትሪክ ወንበር ወይም የገመድ ሸምቀቆ የእምነት ዋነኛ ምልክት እንዲሆን የሚፈልግ ሰው ሊኖር አይችልም። ግን ኢየሱስ በአሁኑ ዘመን በሚኖር መንግሥት ቢገደል ኖሮ እነዚህን መሣሪያዎች የእምነታችን ምሳሌ አድርገን እንጠቀምባቸው ነበር ማለት ነው” ብለዋል።
ማሳሰቢያ ለእንስሳት ወዳጆች
እንስሳትን ትወዳለህን? ከሆነ የምትወደው ውሻ ፊትህን ወይም እጅህን ሳይልስ አይቀርም። የጥገኛ ተሐዋስያን ሊቅና የማኒቶባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሌን ግራሃም እንዳሉት ግን በዚህ ምክንያት ወስፋት ወይም የሌሎች ትሎች እጭ ሊጋባብህ ይችላል። ዊኒፔግ ፍሪ ፕሬስ “የውሻችሁ አፍ ወደ እናንተ ባይጠጋ የተሻለ ይሆናል” ሲል ዘግቧል። ውሾች ራሳቸውን የሚያጸዱት በምላሳቸው ሲሆን፤ ምላሳቸውም ከእዳሪ ጋር የሚወጡ ቆሻሻዎችን ጨምሮ በጣም ብዙ ነገሮች ሰብስቦ ሊያስቀር የሚችል ዓይነት ነው። ጋዜጣው እንዳለው “የውሾች ፀጉር የጀርሞች መሰብሰቢያ ነው።” በዚህ ምክንያት በበሽታ ለመያዝ ያለው ዕድል አነስተኛ ቢሆንም “እናንተንም ሆነ ልጆቻችሁን ውሻ ከላሳችሁ ለጥንቃቄ ያህል እጃችሁንና ፊታችሁን መታጠቡ ጥሩ ይሆናል” የሚል ምክር ተሰጥቷል።
እባብ በሚነድፍበት ጊዜ መደረግ የማይኖርበት
በእባብ ለተነደፉ ሰዎች የሚሰጠውን ሕክምና በተመለከተ ባለሙያዎች አንዳንድ ጊዜ እርስ በርሳቸው አይስማሙም። ይሁን እንጂ ኤፍ ዲ ኤ ኮንስዩመር በተባለው መጽሔት መሠረት አብዛኞቹ የዩናይትድ ስቴትስ ሕክምና ባለሙያዎች “መደረግ ስለማይኖርበት አንድ ነገር ይስማማሉ።” ከ30 እስከ 40 ደቂቃ በሚሆን ጊዜ ውስጥ ወደ አንድ የሕክምና ተቋም ለመድረስ የምትችል ከሆነ እባቡ በነከሰህ ቦታ ላይ በረዶ አታድርግ፣ በጨርቅ አትሰር፣ ቁስሉን አትብጣ ወይም በኤሌክትሪክ አታስመታ። ማንኛውም ዓይነት እባብ፣ መርዘኛም ይሁን አይሁን በሚነክስበት ጊዜ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። የተነከሰው ሰው በተቻለ ፍጥነት ወደ ሆስፒታል መወሰድ ይኖርበታል። ከሁሉ የሚሻለው የእባብ ንክሻ መከላከያ ዘዴ “ወደ እባቦች አለመቅረብ ነው። ብዙ ሰዎች የሚነከሱት እባቡን ለመግደል ሲሞክሩ ወይም ቀረብ ብለን እንየው ሲሉ ነው” ይላል ኤፍ ዲ ኤ ኮንስዩመር።
ማስጠንቀቂያ ለቫይታሚን ኤ ወሳጆች
ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲሲን ያወጣው በ22,000 ነፍሰ ጡሮች ላይ የተደረገ ጥናት እርጉዝ ሴቶች ቫይታሚን ኤ በብዛት መውሰድ እንደማይገባቸው አስጠንቅቋል። ለአንድ ጽንስ እድገት የተወሰነ መጠን ያለው ቫይታሚን ኤ አስፈላጊ ቢሆንም መጠኑ ከበዛ ግን ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ተገልጿል። ነፍሰ ጡር ሴቶች በቀን መውሰድ ይኖርባቸዋል የሚባለው መጠን 4,000 ኢንተርናሽናል ዩኒት ሲሆን ተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ዳይት ኤንድ ኒውትሪሽን ሌተር እንዳለው በቀን ከ10,000 ዩኒት በላይ የሚወስዱ ሴቶች “ጉድለት ያለው ሕፃን የመውለድ ዕድላቸው ቫይታሚን ኤ አብዝተው ካልወሰዱ እናቶች በሁለት ተኩል ጊዜ ይበልጣል።” የሰው ሰውነት ቫይታሚን ኤ አከማችቶ ስለሚይዝ ከእርግዝና በፊት እንኳን ቫይታሚኑን አብዝቶ መውሰድ በሚወለደው ሕፃን ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ከአትክልቶች የሚገኘውና ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ በከፊል ወደ ቫይታሚን ኤ የሚለወጠው ቤታ-ካሮቲን ምንም ችግር እንደማያስከተል ተደርሶበታል።
ሴቶች ያለባቸው ተጨማሪ ሥራ
ወንዶችና ሴቶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን በእኩል መጠን ይካፈላሉን? የጀርመን ፌዴራላዊ የስታትስቲክስ ቢሮ ባደረገው ጥናት መሠረት አይካፈሉም። ኖርበርት እሽቫርስ እና ዲተር ሻፈር የተባሉት ኢኮኖሚስቶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት የሚጠፋውን ጊዜ ለመመርመርና ለመመዝገብ 7,200 ለሚያክሉ ቤተሰቦች ጥያቄ አቅርበው ነበር። ጥናቱ ሣህን እንደማጠብ፣ ገብያ እንደመገብየት፣ የታመሙ ዘመዶችን እንደማስታመምና መኪና እንደመጠጋገን የመሰሉትን ሥራዎች ያጠቃለለ ነበር። ሱድዶቸ ሳይቱንግ ሪፖርት እንዳደረገው “ሴቶች ሥራ ኖራቸውም አልኖራቸው ያለ ክፍያ የሚሠሯቸው ሥራዎች ከወንዶቹ በእጥፍ ይበልጣል።”