ከዓለም አካባቢ
በልጆች ላይ የሚፈጸመው በደል እየተስፋፋ ነው
“በጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙ ወንዶች ልጆች ጤና ላይ በተካሄደ አንድ አዲስ [የዩ ኤስ] ጥናት ከ8 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ከ1 በላይ የሚሆኑት አካላዊ ወይም ጾታዊ በደል እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል” ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ጥናቱ እንዳመለከተው “በወንዶች ልጆች ላይ የሚፈጸመው አካላዊ በደል ከጾታዊ በደል ይበልጥ በጣም የተስፋፋ ከመሆኑም በላይ ከሚደርስባቸው አካላዊ በደል መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው የሚፈጸመው በራሳቸው ቤት ውስጥ በሚገኝ የቤተሰባቸው አባል ነው።” ጾታዊ በደል ከሚፈጸምባቸው ወንዶች ልጆች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የእስያ ዝርያ ያላቸው አሜሪካውያን ልጆች ሲሆኑ 9 በመቶ የሚሆኑት ይህ በደል እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል። ከስፓኒሾቹ ልጆች መካከል 7 በመቶ የሚሆኑት ጾታዊ በደል እንደተፈጸመባቸው የተናገሩ ሲሆን ከጥቁሮቹና ከነጮቹ መካከል ደግሞ 3 በመቶ የሚሆኑት ጾታዊ በደል እንደተፈጸመባቸው ተዘግቧል። መጠይቁ የበደሉን ዓይነት ለይቶ የሚያስቀምጥ አልነበረም። ልጆቹ አካላዊም ይሁን ጾታዊ በደል ደርሶባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ የሚጠይቅ ብቻ ነበር።
በትራፊክ አደጋ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው
በየዓመቱ ከ500,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በዓለም ዙሪያ ባሉ አውራ ጎዳናዎች ላይ በሚከሰቱ አደጋዎች የሚሞቱ ሲሆን በትራፊክ አደጋዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እየጨመረ ነው ሲል ፍሊት ሜንተናንስ ኤንድ ሴፍቲ ሪፖርት ዘግቧል። ለከባድ የትራፊክ አደጋ የመጋለጥ ዕድልህ ምን ያህል ነው? ዘገባው እንደሚለው ከሆነ “‘መኪናዎች በብዛት በሚገኙባቸው’ አገሮች በየዓመቱ ከ20 ሰዎች መካከል ቢያንስ ቢያንስ አንዱ በአውራ ጎዳናዎች ላይ በሚከሰት አደጋ ይሞታል ወይም ይቆስላል። በተጨማሪም ከ2 ሰዎች አንዱ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ ቢያንስ አንዴ በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሆስፒታል ይገባል።”
የሮቦት ቀዶ ሐኪም
በአንድ የፓሪስ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ ሁለት ቀዶ ሐኪሞች በኮምፒዩተር የሚሠራ አንድ ሮቦት በመጠቀም የመጀመሪያውን የተሳካ የልብ ቀዶ ሕክምና ማከናወን እንደቻሉ ለ ፊጋሮ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል። በደም ሥር ላይ የተካሄደውን አንድ ቀዶ ሕክምና ጨምሮ ስድስት ቀዶ ሕክምናዎች ማከናወን ተችሏል። ይህ ዘዴ አራት ሴንቲ ሜትር በሚሆን ብጣት በኩል የሚካሄድ ቀዶ ሕክምና ነው። ቀዶ ሐኪሞቹ ከታካሚው የተወሰኑ ሜትሮች ራቅ ብሎ በሚገኝ አውቶማቲክ መሣሪያ አጠገብ ተቀምጠው የታካሚውን ውስጣዊ አካል በካሜራ እያዩ የሮቦቱን ክንድ እንቅስቃሴ ይቆጣጠራሉ። ኮምፒዩተሩ የቀዶ ሐኪሞቹን እንቅስቃሴ ከሦስት እስከ አምስት እጥፍ ስለሚቀንሰው ቀዶ ሕክምናው ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆንና የታካሚው ውስጣዊ አካል ብዙ እንዳይጎዳ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ሌላው ጥቅም ደግሞ ታካሚው በሚያገግምበት ጊዜ ብዙ ሕመም እንዳይሰማው የሚያደርገው መሆኑ ነው።
“የሁሉም የቀድሞ አባት”?
ከመላው እስያ የተውጣጡ ጳጳሳት የካቶሊክን ሃይማኖት በእስያ አገሮች ማስፋፋት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለመወያየት በቅርቡ በቫቲካን ከተማ ተሰብስበው ነበር። “በአብዛኞቹ የእስያ አገሮች ክርስትና ከቅኝ አገዛዝ ጋር አብሮ የመጣ የምዕራባውያን ሃይማኖት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል” ሲሉ የስሪላንካው ተወካይ ሞንሲኞር ኦዝወልድ ጎሚስ ተናግረዋል። ፈታኝ የሆነው ነገር “ኢየሱስን ለእስያውያን እንደሚስማማ አድርጎ ማቅረብ” ነው ሲል አሶስዬትድ ፕሬስ ዘግቧል። “ጳጳሳቱ የሮማን ቤተ ክርስቲያን ከእስያ ባህሎችና ቋንቋዎች ጋር እንዲሁም ባህሎቹን ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር ማጣጣም ስለሚቻልበት ሁኔታ ተወያይተዋል።” ለዚህ አንዱ እንደ ምሳሌ ሆኖ የተጠቀሰው የቀድሞ አባቶች አምልኮ ልማድ ነው። ይህን ጥንታዊ ልማድ የሚከተሉ ሰዎችን ስሜት ለመማረክ ካቶሊኮች የ“ክርስቲያኖች” አምላክ “የሁሉም የቀድሞ አባት” ነው የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ ቀስ በቀስ በሰዎቹ ሕሊና ውስጥ ማስረጹ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል የሆንግ ኮንጉ ተወካይ ሞንሲኞር ጆን ቶንግ ሆን ተናግረዋል።
ንጽሕናቸው ያልተጠበቀ ዕቃዎች
የማይታመን ሊመስል ቢችልም እንኳ በቤትህ የሚገኘው የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ በወጥ ቤትህ ውስጥ ካለው መክተፊያ የተሻለ ንጽሕና ሊኖረው ይችላል። በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ ተመራማሪዎች በ15 ቤቶች ውስጥ በሚገኙ ባክቴሪያዎች ላይ ለ30 ሳምንታት ክትትል ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ እዚህ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ችለዋል። ይህ የተመራማሪዎች ቡድን ቧንቧዎችን፣ ሲንኮችን፣ መክተፊያዎችን፣ የዕቃ ማድረቂያ ጨርቆችንና የመጸዳጃ ቤት መቀመጫዎችን ጨምሮ በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ከሚገኙ 14 ዕቃዎች ላይ ናሙናዎች ወስዶ ነበር። የተገኘው ውጤት ምን ነበር? “ተመራማሪዎቹ ዕቃ ማድረቂያ ጨርቆችን በመጭመቅ በፈሳሹ ውስጥ ያገኟቸው ባክቴሪያዎች በመጸዳጃ ቤት መቀመጫዎች ላይ ካገኟቸው ባክቴሪያዎች ሚልዮን ጊዜ እጥፍ ይበልጣሉ” ሲል ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት ዘግቧል። “በመክተፊያዎች ላይ የተገኙት ባክቴሪያዎች እንኳ ሦስት እጥፍ ይበልጣሉ።” የቡድኑ ቃል አቀባይ የሆኑት ፓት ረሰን “የመጸዳጃ ቤት መቀመጫዎች ደረቅ ስለሚሆኑ እርጥብ ነገሮችን ለሚመርጡት ባክቴሪያዎች መራቢያነት አመቺ አይደሉም” ሲሉ የሰጡትን ግምታዊ ሐሳብ መጽሔቱ ጠቅሶ ዘግቧል። የጤና አጠባበቅ ዘዴን ለማሻሻል የዕቃ ማድረቂያ ጨርቆችን በየሳምንቱ ማጠብ ጠቃሚ እንደሆነ ረሰን ገልጸዋል። “በውኃ የተሞላ ሲንክ ውስጥ አንድ ስኒ ፀረ ጀርም ኬሚካል ጨምሮ ዕቃ ማድረቂያ ጨርቁን ለ10 ደቂቃ መዘፍዘፉ ብቻ በቂ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ለኩላሊት ጠጠር የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን መቀነስ
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ1986 እስከ 1994 ባሉት ዓመታት ከ80,000 በሚበልጡ ነርሶች አመጋገብ ላይ ክትትል ያካሄዱ ተመራማሪዎች አንድ ሰው የኩላሊት ጠጠርን ለመከላከል እንዲችል ይበልጥ ሊረዱት የሚችሉ የተወሰኑ መጠጦች እንዳሉ መገንዘባቸውን ሳይንስ ኒውስ ዘግቧል። ጥናት ከተካሄደባቸው 17 መጠጦች መካከል ሻይ ለኩላሊት ጠጠር የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን 8 በመቶ እንደሚቀንስ የተረጋገጠ ሲሆን ካፌይን ያለውም ሆነ የሌለው ቡና ደግሞ 9 በመቶ ይቀንሳል። ልከኛ በሆነ መጠን ወይን መጠጣት የኩላሊት ጠጠር የሚፈጠርበትን አጋጣሚ 20 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ሊቀንስ ይችላል። “የሚገርመው ነገር፣ 240 ሚሊ ሊትር የባሕረ ሎሚ (ግሬፕ ፍሩት) ጭማቂ በየቀኑ መጠጣት የኩላሊት ጠጠር ሊፈጠር የሚችልበትን አጋጣሚ 44 በመቶ የሚያሳድገው” መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል። “እንዲህ ያለ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሌላ መጠጥ የለም።” በቦስተን ኒፍሮለጂስትና ኤፒዲሞሎጂስት ሆነው የሚሠሩት ዶክተር ጌሪ ከርሃን “የመጠጥ አወሳሰድን መቆጣጠር ለውጥ ሊያመጣ ይችላል” ብለው መናገራቸው ተዘግቧል፤ ሆኖም ይህ አጠቃላይ የሆነ የሕክምና ስልት ነው።
በአውስትራሊያ ለትንሣኤ በዓል የሚሰጠው ትርጉም
ሰን-ሄራልድ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ በዓለ ትንሣኤ (Easter) ለእነሱ ምን ትርጉም እንዳለው የተለያዩ ሰዎችን በመጠየቅ አንድ ጥናት አካሂዶ ነበር። የተገኘውን ውጤት ጋዜጣው እንደሚከተለው በቅደም ተከተል አስቀምጦታል:- የበዓለ ትንሣኤ ዕንቁላሎች (54 በመቶ)፣ ረጅም የቅዳሜና እሁድ በዓል (39 በመቶ)፣ የበዓለ ትንሣኤ ትርዒት (21 በመቶ)፣ ሃይማኖታዊ በዓል (20 በመቶ)። የተባበሩት ቤተ ክርስቲያናት አገልጋይ የሆኑት ዴቪድ ሚሊከን በሲድኒ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል በዓለ ትንሣኤን ከሃይማኖት ጋር ያያያዙት ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸው ብዙም እንዳላስደነቃቸው ተናግረዋል። አክለውም “አቢያተ ክርስቲያናቱ እየከሰሙ ነው . . . ዋና ዋናዎቹ የሃይማኖት ክፍሎች የአባሎቻቸው ቁጥር በእጅጉ እያሽቆለቆለ ነው” ብለዋል። የሲድኒ የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ “ለብዙዎች በዓለ ትንሣኤ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ትርጉም የለውም፤ ልክ እንደ አንድ ዓለማዊ በዓል አድርገው ነው የሚመለከቱት” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ዕቃ የመግዛት ሱስ የተጠናወታቸው
“በጀርመን ውስጥ የሚኖሩ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች ዕቃ የመግዛት ሱስ ተጠናውቷቸዋል” ሲል ግራፍሻፍተር ናችሪችተን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። የንግድ ጉዳዮች ሳይኮሎጂስት የሆኑት አልፍሬት ጌቤርት እንዳሉት ከሆነ ዕቃ የመግዛት ሱስ የተጠናወታቸው ሰዎች ዕቃውን ከገዙ በኋላ ወዲያው የሚጠፋ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ይሰማቸዋል። እንዲያውም ይህን ሱሳቸውን ካላረኩ አካላዊ የሆኑ የሕመም ምልክቶች እንደሚታዩባቸው ጌቤርት ይናገራሉ። “ይንቀጠቀጣሉ፣ ያልባቸዋል፣ እንዲሁም ከባድ ሆድ ቁርጠት ያመጣባቸዋል።” በዚህ የተነሳ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ድሃ ከሆኑት ሰዎች ይበልጥ ለዚህ ሱስ የተጋለጡ ናቸው። ለዚህ ሱስ ሊዳርጉ ይችላሉ ከሚባሉት ነገሮች መካከል ‘ብቸኝነት፣ ራስን ዝቅ አድርጎ መመልከት፣ ውጥረትና በሥራ ቦታ የሚያጋጥሙ ችግሮች’ ይገኙባቸዋል። ይህን ሱስ ለመቋቋም አንድ ዓይነት ልማድ ማዳበር ጠቃሚ እንደሆነ ጌቤርት ይናገራሉ። ለዚህ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ነገር ማኅበራዊ ግንኙነት ነው፣ ይላሉ ጌቤርት። “የሌላ ሰው እርዳታ ካልታከለበት ሱሱ የሚታወቀው ሰውየው ኪሱን አራግፎ ዕዳ ውስጥ ሲዘፈቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ልጆችን በድብቅ መከታተል
በጃፓን የሚኖሩ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን በትምህርት ቤት ከሚያስቸግሯቸው ጉልበተኞች ለመጠበቅ ሲሉ ልጆቻቸውን በድብቅ የሚከታተሉ ሰዎች በግል መቅጠር ጀምረዋል። ዘ ዴይሊ ዮሚዩሪ እንዳለው ከሆነ ከ6,000 በሚበልጡ ተማሪዎች ላይ ጥናት ያካሄዱ በኦሳካ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ አንድ ፕሮፌሰር እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በጥቅሉ ሲታይ ጉልበተኞች የሚያስቸግሯቸው ልጆች የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት መቋቋም ወይም ማስቆም ባለመቻላቸው እንዳይወቀሱ ስለሚሰጉ ሐቁን ከወላጆቻቸው መደበቅ ይፈልጋሉ።” በልጆቻቸው ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር ጥርጣሬ ያደረባቸው አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ከሌሎች ጋር የሚያወሩትን ለመስማት በድብቅ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ያደርጉባቸዋል። ሌሎች ወላጆች ደግሞ “ልጆቻቸውን በርቀት በመከታተል በሚያስቸግሯቸው ልጆች ላይ ማስረጃ የሚይዙና ልክ እንደ ጠባቂ መልአክ ፈጥነው በመድረስ ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀን ልጅ የሚያድኑ” ሰዎችን በግል ቀጥረዋል። የልጆች መብት ተሟጋቾች ግን ይላል ጋዜጣው፣ “ወላጆች በልጆቻቸው ላይ በድብቅ ክትትል ማድረጋቸው በአዋቂ ሰው መታመንና ምሥጢራቸውን ማካፈል የሚገባቸውን ልጆች ይበልጥ ከወላጆቻቸው የሚያቆራርጥ መጥፎ እርምጃ እንደሆነ በመግለጽ ድርጊቱን ያወግዛሉ።” ይሁን እንጂ ወላጆች የልባቸውን አውጥተው የማይናገሩ ልጆቻቸው ችግር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ መርዳት የሚችሉበት መንገድ ይህ እንደሆነ ይናገራሉ።