መጽሐፍ ቅዱስን የምታውቀው ምን ያህል ነው?
‘መጽሐፈ ቶማስ? አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ። መጽሐፈ ዮናስ ግን የለም። ክርስቶስ የተወለደው የት ነው? ኢየሩሳሌም ነዋ! የለም ናዝሬት ነው መሰለኝ የተወለደው። የኢሳይያስ መጽሐፍ የሚገኘው በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይሁን በሁለተኛው ክፍል እርግጠኛ አይደለሁም። ሐዋርያት ስንት ናቸው? እንጃ በትክክል አላውቅም።’
“ይህን የተናገሩት ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ አያስደንቅም ነበር።” ይላል ክርስቲያን ቱደይ የተባለው መጽሔት። መጽሔቱ በመቀጠል “በጣም የሚያስደንቀውና የሚያሳዝነው ዳግም ልደት አግኝተናል በሚሉ ክርስቲያኖች መካከል የሚታየው ድንቁርና ነው” ይላል።
ለምሳሌ ያህል ጥናት ከተደረገባቸው የስም ክርስቲያኖች መካከል 22 በመቶ የሚያክሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጽሐፈ ቶማስ እንዳለ ሲያስቡ 13 በመቶ የሚያክሉት እርግጠኛ አልነበሩም። ስለ መጽሐፈ ዮናስ ደግሞ 27 በመቶ የሚያክሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም ሲሉ 12 በመቶ የሚሆኑት ምንም የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል። 6 በመቶ የሚያክሉት ኢየሱስ የት እንደተወለደ እንኳን መገመት ሲያቅታቸው 16 በመቶ የሚሆኑት በኢየሩሳሌም፣ 8 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በናዝሬት ተወለደ ብለዋል። ከ13 በመቶ ያላነሱ ሰዎች የኢሳይያስ ትንቢት በየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሚገኝ አናውቅም ሲሉ 11 በመቶ የሚያክሉት በክርስቲያን ግሪክኛ ጽሑፎች (“አዲስ ኪዳን” ) ውስጥ ነው ብለዋል። በተጨማሪም አብዛኞቹ ተጠያቂዎች 12 ሐዋርያት እንደነበሩ ቢያውቁም 12 በመቶ የሚያክሉት ከ2 እስከ 20 የሚደርስ የተለያየ ቁጥር ሲሰጡ 10 በመቶ የሚሆኑት ምንም አናውቅም ብለዋል።
ከሁሉ ይበልጥ አስቸጋሪ የሆነባቸው ጥያቄ “እርዱኝ እረዳችኋለሁ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል ወይ? የሚለው ነበር። ከተጠየቁት “ክርስቲያኖች” መካከል ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይገኝ ያወቁት 38 በመቶ የሚያክሉት ብቻ ናቸው። 42 በመቶ የሚያክሉት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ጥቅስ መስሎአቸዋል። የቀሩት ደግሞ ምንም እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ክርስቲያኒቲ ቱደይ “ይህን ያህል ድንቁርና የተስፋፋው ለምንድንነው?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ “መጽሐፍ ቅዱስን ካለማንበብ የመጣ ይመስላል። ከአሜሪካውያን መካከል ግማሽ የሚያክሉት መጽሐፍ ቅዱስን አያነቡም። ዳግም ልደት አግኝተናል ከሚሉ ክርስቲያኖች መካከል አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡት በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ ሲሆን አንዳንዶቹ ፈጽመው አንብበው አያውቁም። ይህን የሚያክሉ ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች ያላቸው ዕውቀት በጣም አነስተኛ መሆኑ አያስደንቅም” ብሎአል።