የተሻለ ዓለም መምጣቱ ሕልም ነውን?
ዞራስተር በተባለው ኢራናዊ ነቢይ የተሰበከው የማዝዳይዝም እምነት ተከታይ ብትሆን ኖሮ ምድር ወደ መጀመሪያ ውበቷ የምትመለስበትን ቀን በተስፋ ትጠባበቅ ነበር። በጥንቷ ግሪክ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ሔሲዮድ የተባለው ባለቅኔ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በገለጸው ፍጹም የሆነ የብልጽግና ደሴት ለመኖር ወይም ወርቃማው ዘመን ሲመለስ ለማየት ትናፍቅ ነበር። በደቡብ አሜሪካ የሚኖር የጉዋራኒ ህንድ አሁንም ክፋት የሌለበትን አገር ለማግኘት በመፈለግ ላይ ይሆናል። ዘመናዊ ሰው ከሆንክ ደግሞ በአንዳንድ የፖለቲካ ፍልስፍናዎች አማካኝነት ወይም በዘመናችን የሚኖሩ ሰዎች የአካባቢያችን ሁኔታ በጣም እያሳሰባቸው በመምጣቱ ምክንያት የዓለማችን ሁኔታ ይሻሻላል ብለህ ተስፋ ታደርግ ይሆናል።
ወርቃማው ዘመን፣ የብልጽግና ደሴት፣ ክፋት የሌለበት አገር፤ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ለተሻለ ዓለም ያላቸውን ናፍቆትና ተስፋ ከሚገልጹባቸው ቃላት ጥቂቶቹ ናቸው።
ይህ የእኛ ዓለም ፍጹም አለመሆኑ የተረጋገጠ ነው። የጭካኔ ወንጀሎች መብዛት፣ በአሠቃቂነታቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው ጦርነቶች፣ የወንድማማቾች መጨራረስ፣ የእርስ በርስ እልቂት፣ ለሌሎች ሥቃይ ደንታ ቢስ መሆን፣ ድህነትና ረሐብ፣ ሥራ አጥነትና እርስ በርስ ለመረዳዳት ፈቃደኛ አለመሆን፣ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያሠቃዩ ፈውስ የሌላቸው በሽታዎች፤ የዘመናችንን ወዮታዎች ዘርዝሮ ለመጨረስ አይቻልም። አንድ ኢጣልያዊ ጋዜጠኛ በዘመናችን ስለሚደረጉት ጦርነቶች በማሰብ “ማንም ሰው በአእምሮው ውስጥ በጣም ኃይለኛው የዘመናችን ስሜት ጥላቻ ስለመሆኑ መጠየቁ አይቀርም” ብሏል። ይህን ሁሉ ስትመለከት ከዚህ የተለየ ወይም የተሻለ ነገር ይመጣል ብሎ ተስፋ ማድረግ ምክንያታዊ ነው ብለህ ታስባለህን? ወይም እንደዚህ ያለው ምኞት ሊገኝ የማይችል የሕልም እንጀራ አይሆንምን? ከዚህ ከምንኖርበት ዓለም የተሻለ ዓለም ሊገኝ አይችልምን?
እንዲህ ያለው ጭንቀት በዘመናችን ብቻ የተፈጠረ አይደለም። ለብዙ መቶ ዘመናት ሰዎች ስምምነት፣ ፍትሕ፣ ብልጽግና እና ፍቅር ስለ ሰፈነበት ዓለም ሲያልሙ ኖረዋል። ባለፉት ጊዜያት ሁሉ በርካታ ፈላስፋዎች፣ የተሻለና ለመኖሪያ ተስማሚ የሆነ ዓለም እንዴት ያለ መሆን እንደሚገባው የየራሳቸውን ሐሳብ በዝርዝር ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ዓለም እንዴት እንደሚመጣ ሳይገልጹ መቅረታቸው ያሳዝናል።
እነዚህ ለብዙ ዘመናት የኖሩት ሕልሞች፣ ፍጹም ሁኔታዎች እና ምኞቶች የሚያስተምሩን አንዳች ነገር ይኖር ይሆንን?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሁሉም የተሻለው ዓለም ይህ ነውን?