አምላክን ስታገለግል የሚያጋጥምህን ናፍቆት ታግሎ ማሸነፍ
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን፦ “እንግዲህ ሂዱና. . . አሕዛብን ሁሉ ደቀመዛሙርት አድርጉ” በማለት አዝዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19) ለብዙ ክርስቲያኖች ይህንን ትእዛዝ መፈጸም ከቤት ርቀው መሄድና እዚያ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቀበልን የሚጠይቅባቸው ሆኗል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ሚስቶቻቸውና ሌሎችም ለአምላክ አገልግሎት ሲሉ ከኋላቸው ብዙ ነገሮችን ትተዋል። ለእነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ሁሉ ናፍቆት ትግል የሚጠይቅ ሊሆንባቸው ይችላል።
ናፍቆት የሚከሰተው አእምሮህ ወደኋላ መለስ ብሎ በፊት ያሳለፍከውን እርጋታና ፍቅር ታገኝ የነበረበትን ትዝታ ሲቀሰቅስብህ ነው። ይህም እንድትጨነቅ የሚያደርግና ልትቀጥል እንደማትችል እንዲሰማህ የሚያደርግ የስሜት ውጥረት ሊያስከትል ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ንብረታቸውን ሸጠውና ብዙ ወጪ አድርገው ወደ ውጭ አገር ከተጓዙ በኋላ እቅዳቸውን ሰርዘው ተመልሰዋል። ናፍቆት አሸነፋቸው።
በአብዛኛው በስሜት ላይ የሚደርሰው እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ለመጀመሪያ ጊዜ ቦታቸውን ለቀው ከሄዱ በኋላ መታየቱ የተለመደ ሲሆን በአንዳንዶቹ ላይ ግን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ የሚከሰት ነው። ለ20 ዓመታት ያህል ከቤቱ ርቆ ከኖረ በኋላ ያዕቆብ ‘የአባቱን ቤት አጥብቆ ናፍቆ ነበር።’ (ዘፍጥረት 31:30) በናፍቆት እጠቃለሁ ብሎ ሊጠብቅ የሚችለው ምን ዓይነት ሰው ነው? ናፍቆትን የሚቀሰቅሱት ነገሮች ምንድን ናቸው? አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን ስሜት እንዴት ታግሎ ሊያሸንፈው ይችላል?
ሐዘኑን የሚቀሰቅሱት ነገሮች ምንድን ናቸው?
ናፍቆት ሁሉንም ሰው ሊነካ ይችላል። የአሦር ንጉሥ የአስቴያገስ ልጅ አሜተስ ላይ ላዩን ሲታይ ሊያስደስታት የሚችል ነገር ሁሉ ነበራት፤ ሀብት፣ ትልቅ ክብርና ያማረ ቤት ነበራት። ይሁን እንጂ የሜዶን ተራሮች ከፊቷ ድቅን እያሉ ናፍቆቱን ስላልቻለችው ባሏ ናቡከደነፆር እርሷን ለማስደሰት ታዋቂውን የባቢሎን የአትክልት ሥፍራ አዘጋጀላት።
አንድ ሰው አካባቢውን ለቆ ከመሄዱ በፊት ከነበረበት ይልቅ አሁን ኑሮ አስቸጋሪ ሲሆንበት ናፍቆቱ በጣም ፈታኝ ሊሆንበት ይችላል። የይሁዳ ሕዝብ ምርኮኛ በሆኑ ጊዜ እንዲህ በማለት አማርረዋል፦ “በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ በዚያ አለቀስን። የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?”—መዝሙር 137:1, 4
ናፍቆትን የሚቀሰቅሱት ብዙ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ካናዳን ለቅቃ የሄደችው ቴሪ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን ከመጽሐፍ ውስጥ የቤተሰባችን ፎቶግራፍ ወደቀ። ከመሬት ብድግ ሳደርገው የናፍቆት ጎርፍ ዋጠኝና አለቀስኩ።” ከእንግሊዝ አገር በጣም ድኻ ወደሆነ ሌላ አገር የሄደው ክሪስ፦ “የድሮ ዘፈን ስሰማ ወይም የማውቀው ዓይነት ምግብ ሽታ ሲሸተኝ ከኋላዬ ትቻቸው የመጣኋቸውን ነገሮች እንድናፍቅ ያደርገኛል” ብሏል።—ከዘኁልቁ 11:5 ጋር አወዳድር።
ሌላው ለዚህ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ደግሞ ከቤተሰብ ጋር በጣም መቀራረብ ነው። አሁን በጎረቤት አገር የሚኖር ሮዜሊ የተባለ አንድ ብራዚላዊ እንዲህ በማለት አስተያየቱን ይሰጣል፦ “ከቤት አንድ መጥፎ ዜና ሲደርሰኝ በዚያ ተገኝቼ ልረዳቸው ባለመቻሌ እተክዛለሁ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ምንም ወሬ ሳልሰማ እቀርና ምን ሆኑ ይሆን እያልኩ ሳወጣና ሳወርድ ይበልጥ ይከፋኛል።” ጃኒስ ከሰሜን አሜሪካ በአማዞናውያን ሞቃታማ ስፍራ ወደምትገኝ ትንሽ ከተማ ሄዳ ትኖራለች። እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ከቤት አንድ ደስ የሚል ዜና ሲደርሰኝ እናፍቃለሁ። አንድ ላይ ሆነው ጥሩ ጊዜ እንደሚያሳልፉ ስሰማ ከእነርሱ ጋር መሆንን እመኛለሁ።”
ናፍቆትን የሚያመጣው ከሰዎች ተለይቶ መሄዱ ብቻ አይደለም። ሊንዳ እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “የምፈልጋቸውን ነገሮች የምገዛበትን ቦታ ሳላውቀው ስቀር ተስፋ እቆርጥ ነበር። ዋጋው ስንት እንደሆነና እንዴት ዋጋውን ማስቀነስ እንደሚቻል አላውቅም ነበር። መኪና መግዛት በጣም ውድ ስለነበር በጣም ጭንቅንቅ ያለውን የሕዝብ ማመላለሻ ለመጠቀም ሁልጊዜ መጋፋት ነበረብኝ። ይህ ቤቴን እንድናፍቅ ያደርገኝ ነበር።” በባህልና በኢኮኖሚ አኳያ ስለሚኖረው ልዩነት ስትናገር ጃኔት እንዲህ ብላለች፦ “እኔን ያበሳጨኝ ድህነቱ ነው። እንጀራ የሚለምኑ ወይም የቧንቧ ውሃ እንኳን ሳይኖራቸው በአንድ ክፍል ውስጥ የሚኖር የትልቅ ቤተሰብ አባላት ከዚያ በፊት ፈጽሞ አይቼ አላውቅም . . . እነዚህ ነገሮች በጣም ስላበሳጩኝ እዚያ አገር መቀጠል እንደማልችል ተሰማኝ።”
ስሜቶችህን ታግለህ ማሸነፍ
ለምናፈቅራቸው ሰዎች ወይም በልጅነታችን ላደግንበትና ለለመድነው አካባቢ ጠንካራ ውስጣዊ ስሜት ቢሰማን ነገሩ የሚያሳፍር አይደለም። ይሖዋ አምላክ ስሜቶችን የፈጠረልን ሞቅ ባሉ ፍቅራዊ ዝምድናዎች እንድንደሰት ነው። በኤፌሶን የነበሩት ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በስሜት የበሰሉ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ የሐዋርያው ጳውሎስ ጉብኝት ሲጠናቀቅ ምን ነገር ተፈጸመ? “ሁሉም እጅግ አለቀሱ፣ ጳውሎስንም አቅፈው ይስሙት ነበር”! (ሥራ 20:37) እርግጥ ነው ይህ ናፍቆት አልነበረም። ይሁን እንጂ አንድ ነገር ያስገነዝበናል። ስሜቶች መኖራቸው ያለ ነገር ነው፤ ግን እኛን እንዲቆጣጠሩን መፍቀድ የለብንም። ታዲያ ናፍቆትን ታግለህ ልታሸንፈው የምትችለው እንዴት ነው?
የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማን የሚረዳው አንዱ ቁልፍ ነገር የአካባቢውን ቋንቋ መማር ነው። የውጭ አገሩን ቋንቋ ባለማወቅህ የተነሣ ከሌሎች ጋር መነጋገር ሳትችል ስትቀር የናፍቆቱ ስሜት ከፍ ሊል ይችላል። እንግዲያው የሚቻል ከሆነ ወደ እዚያ አገር ከመሄድህ በፊት የዚያን አካባቢ ቋንቋ ማንበብንና መናገርን ተማር። አለበለዚያም ወደዚያ እንደደረስክ ባሉት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ቋንቋውን በማጥናት ላይ አተኩር። ቋንቋውን ለማጥናት ከፍተኛው ግፊትና ከሁሉ የተሻለው አጋጣሚ የሚኖርህ በዚህ ወቅት ነው። እነዚህን ሳምንታት በቀዳሚነት ቋንቋውን ለማጥናት ከተጠቀምክባቸው ወዲያው በቋንቋው ለመግባባት መቻልህ ስለሚያስደስትህ ይህ የናፍቆት ስሜትህን ሊያቃልልልህ ይችላል።
በተቻለህ መጠን በቶሎ አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት ሞክር። ምክንያቱም ይህ በቤትህ እንዳለህ እንዲሰማህ ያደርጋል። እውነተኛ ጓደኞችን ለማግኘት ከሁሉ የተሻለው ቦታ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ነው። አንተ ቀዳሚ በመሆን ጓደኝነታቸውን እንደምትፈልግ አሳያቸው። አስተዳደጋቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ችግራቸውንና ፍላጎታቸውን ለማወቅ ጣር። የእምነት ወንድሞችህን ወደቤት ጋብዛቸው። በምላሹ ደግሞ ሌሎች አንተን የሚያቀርቡህ ሆኖ ታገኘዋለህ።
በአምላክ ሕዝቦች መካከል ጓደኝነት እንደ ቤተሰብ ትስስር የጠበቀ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ወንድሜ ነው እህቴም እናቴም።” (ማርቆስ 3:35) ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንደሚከተለው በማለትም አረጋግጦላቸዋል፦ “እውነት እላችኋለሁ ስለእኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንም እህቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል የለም።” (ማርቆስ 10:29, 30) እንዲህ ባለው ግሩም መንፈሳዊ የወንድማማችነት ማኅበር ውስጥ ስለምንገኝ ሌላ አገርም ብንሄድ ብቻችንን አይደለንም።
በአገርህ ካሉት ጋር የነበረህን ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረግህም ናፍቆትህን ለማሸነፍ ሊረዳህ ይችላል። አሁን አካባቢህን ለቀህ ስለሄድክ በደብዳቤ የምታደርገው ግንኙነት ትርጉም ያለው ሆኖ ስታገኘው ትገረም ይሆናል፤ ምክንያቱም በደብዳቤው ላይ የምታሠፍራቸውን ቃላት በደንብ ታስብባቸዋለህ። የምትጽፋቸው አስገራሚ ነገሮች ይኖሩሃል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጃኔት እንዲህ በማለት ያላትን አስተያየት ትሰጣለች፦ “ከረጅም ርቀት የሚደረጉ የቴሌፎን ጥሪዎች ውድ ናቸው፤ ድምጽ የተቀዳበትን ካሴት በፖስታ ቤት መላክ ግን ከዚያ ጋር ሲወዳደር ርካሽ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ማሽን ጋር መነጋገሩ እንግዳ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ከአንድ ሰው ጋር በማይክሮፎን በኩል መነጋገሩ ቀላልና ደስ የሚል ነው።” ምናልባትም መልሱ በካሴት ተቀድቶ እንዲላክልህ ትጠይቅ ይሆናል።
ከ25 ዓመታት በፊት ከአሜሪካ ወደ ላቲን አሜሪካ የሄደችው ሺርልይ እንዲህ ትላለች፦ “ችግሮችን ከመደርደር ይልቅ ሁልጊዜ የምጽፈው የሚያንጹ ተሞክሮዎችን ነው። ይህ ደግሞ ሌሎች ሳያቋርጡ እንዲጽፉልኝ ያበረታታቸዋል።” ይሁን እንጂ ብዙ ደብዳቤ መጻፍህ አዳዲስ ጓደኞችን እንዳታፈራ እንዳያደርግህ ተጠንቀቅ። ከካናዳ ወደ ሌላ አገር የተጓዘው ዴል እንዲህ ይላል፦ “በቤት ቁጭ ብለህ ስለጎደሉብህ ነገሮች ማሰላሰልን ተው። ከዚያ ይልቅ ወጣ ብለህ በአዲሱ የመኖሪያ አካባቢህ ተደሰት።”
ከአዲሱ አካባቢ ባሕል፣ ታሪክ፣ ቀልዶች እንዲሁም ደስ የሚሉና ትኩረትን የሚስቡ ቦታዎች ጋር ተዋወቅ። ይህም አፍራሽ የሆኑ ነገሮችን ብቻ እንዳታስብ ያደርግሃል። በሄድክበት ቦታ ለመቆየት ሐሳብ ካለህ ብዙ ሳትቆይ ወይም ቶሎ ቶሎ ወደ አገርህ ባትመላለስ የተሻለ ይሆናል። አዲስ ጓደኞችን ለማፍራትና ከአካባቢው ጋር ለመተዋወቅ ጊዜ ይወስድብሀል። ወደ አገርህ ተመልሰህ ረዘም ያለ ጊዜ የምታሳልፍ ከሆነ ይህንን ሂደት ያቋርጥብሃል። አዲሱን አገር አንዴ ከለመድከው በኋላ ግን ጠይቀሃቸው ለመመለስ ወደ አገርህ መሄዱ አስደሳች ሊሆንልህ ይችላል። ከመመለስህ በፊት ባለው ጊዜ ግን በአዲሱ አካባቢ ያለህን ግንኙነት ለማጠናከር ጣር።
ወደፊት አሻግረህ ተመልከት
ይሖዋ መላዋን ምድር መኖሪያ እንድትሆነን ሰጥቶናል። (መዝሙር 115:16) ደስተኛ ክርስቲያናዊ መንፈስ ካለን በየትኛውም ምድር ብንኖር ሕይወት አስደሳች ሊሆንልን ይችላል። የመንግሥቱን ሥራ ለማራመድና ምሥራቹን ለመስበክ ብለህ ወደ ሌላ አገር ወይም በአገርህ ውስጥ ወደሚገኝ ማንኛውም ቦታ ሄደህ ከሆነ የወደፊቱን ጊዜ በደስታ በመጠባበቅ ይህንን ሥራህን ፈጽም። አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራት፣ የተለያዩ ባሕሎችን ለመማር፣ ደቀመዛሙርት ለማድረግ ወይም በአምላክ አገልግሎት የሚክሱ ነገሮችን ለማከናወን እንደምትችል ወደ ሐሳብህ እያመጣህ ወደፊት አሻግረህ ተመልከት።
ይሖዋ አምላክ የትም ብትሆን ሁልጊዜ የማይለይ ጓደኛ ነው። (መዝሙር 94:14፤ 145:14, 18) ስለዚህ ከእርሱ ጋር በጸሎት ተቀራርበህ ኑር። (ሮሜ 12:12) ይህም የአምላክ አገልጋይ በመሆንህ በሕይወትህ ውስጥ ያለህን ዓላማ እንድታስታውስ ይረዳሃል። አብርሃምና ሣራ በኡር ከተማ የነበራቸውን የተመቻቸ ኑሮ ትተው ሲሄዱ የመጡበትን ዓላማ ሁልጊዜ ያስታውሱ ነበር። በይሖዋ ትዕዛዝ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ትተው ሄዱ። (ሥራ 7:2–4) ትተውት ስለሄዱት ቦታ ማስታወሳቸውንና መናፈቃቸውን ቀጥለው ቢሆን ኖሮ የሚመለሱበት አጋጣሚ ነበራቸው። ግን ወደተሻለ ቦታ ለመድረስ ግብ አድርገው ነበር። እርሱም በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ሥር በምድራዊ ገነት ውስጥ ወደሚኖረው ሕይወት ለመድረስ ነበር።—ዕብራውያን 11:15, 16
ወደ ውጭ አገር ወይም በአገር ውስጥ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ መስበክ በጣም ፈታኝ ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 15:8) ለጊዜውም ቢሆን አፍራሽ አስተሳሰቦች የሚከቡህ ከሆነ ግብህን በማስታወስና አሻግረህ በመመልከት ሁኔታውን ልትወጣው ትችላለህ። አንዲት ያላገባች ሚስዮናዊ እህት እንዲህ ብላለች፦ “የሐዘን ስሜት ሲሰማኝ ስለ አዲሱ ዓለምና የሰው ዘር እንዴት አንድ ቤተሰብ እንደሚሆን አስባለሁ።” እንደነዚህ ያሉ አስደሳች ሐሳቦች ደስታህን ጠብቀህ ለማቆየትና በናፍቆት ላለመሸነፍ ይረዱሃል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናፍቆት በክርስቲያናዊ አገልግሎት ውስጥ ቦታ ሊኖረው አይገባም