በባዕድ አገር ማገልገል ትችላለህን?
“በሚስዮናዊ ሥራ ለመካፈል ዘወትር እመኝ ነበር። ከማግባቴ በፊት ሰባኪዎች በጣም ያስፈልጉ በነበረበት በዩ ኤስ ኤ፣ ቴክሳስ አገልግያለሁ። ከጋብቻችን በኋላ ባለቤቴ በዚያ አብራኝ ማገልገል ጀመረች። ሴት ልጃችን ስትወለድ ‘እንግዲህ ሚስዮናዊ የመሆኔ ጉዳይ አከተመለት’ ብዬ አሰብኩ። ሆኖም ይሖዋ በተለይ ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ ግብ ካወጣን ምኞታችንን ያሳካልናል።”—ጄሲ፣ በአሁኑ ጊዜ በኢኳዶር ከሚስቱና ከሦስት ልጆቹ ጋር በማገልገል ላይ ይገኛል።
“በጊልያድ የሚስዮናውያን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ሳልካፈል በውጭ አገር በአቅኚነት ማገልገል እችላለሁ የሚል ሐሳብ አልነበረኝም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቼ አንዷ የተማሪ ንግግር ስታቀርብ ወይም ስትሰብክ ሳይ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኝ ነበር፤ ለዚህም ይሖዋን አመስግኜዋለሁ።”—ካረን፣ በደቡብ አሜሪካ ለስምንት ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለች ነጠላ እህት።
“ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለ13 ዓመታት ያህል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከተካፈልን በኋላ እኔና ባለቤቴ ለየት ያለ ነገር ማድረግ ፈለግን። ከዚህ በፊት አግኝተን የማናውቀውን ደስታ አግኝተናል፤ በእርግጥም ግሩም የሕይወት መንገድ ነው።”—ቶም፣ በአማዞን ክልል ከባለቤቱ ከሊንዳ ጋር በአቅኚነት ያገለግላል።
እነዚህን አድናቆት የተሞሉ መግለጫዎች የተናገሩት በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሚስዮናዊነት ሥልጣና ለመቀበል ሁኔታቸው ያልፈቀደላቸው ሰዎች ናቸው። የሆነ ሆኖ ወደ ውጭ አገር ሄዶ ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታና ተፈታታኝ ሁኔታ ቀምሰዋል። ይህን ሊያደርጉ የቻሉት እንዴት ነው? በዚህ ዓይነት አገልግሎት መካፈል ትችላለህ?
ትክክለኛ የልብ ግፊት ያስፈልጋል
በባዕድ አገር በማገልገል ስኬታማ ለመሆን አዳዲስ ነገሮችን የመጋፈጥ መንፈስ መያዝ ብቻ አይበቃም። በዚህ ሥራ የጸኑ ሰዎች ሊሳካላቸው የቻለው ትክክለኛ የልብ ግፊት በመያዛቸው ነው። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እነርሱም ለአምላክ ብቻ ሳይሆን ለሰዎችም ባለ ዕዳ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። (ሮሜ 1:14) ከአገራቸው ክልል ሳይወጡ በአገልግሎት በመሳተፍ፣ እንድንሰብክ የተሰጠንን መለኮታዊ ትእዛዝ ማሟላት ይችሉ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ይሁን እንጂ ባለ ዕዳ እንደሆኑ ስለተሰማቸው ምሥራቹን ለመስማት እጅግ አናሳ አጋጣሚ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘትና ለመርዳት ግፊት አደረባቸው።
በአብዛኛው፣ ይበልጥ ፍሬያማ በሆነ የአገልግሎት ክልል ለማገልገል ያላቸው ፍላጎት ሌላው ግብ ሲሆን ይህም ተገቢ ነው። አንድ ዓሣ አጥማጅ ጥሩ አድርጎ እያጠመደ መሆኑን ስናይ እርሱ ወደሚያጠምድበት አካባቢ ጠጋ የማንል ማናችን ነን? በተመሳሳይ በሌሎች አገሮች ስላለው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጭማሪ የሚቀርቡት አበረታች ሪፖርቶች ብዙዎች “እጅግ ብዙ ዓሣ” ወዳለበት አካባቢ እንዲሄዱ አነሳስቷቸዋል።—ሉቃስ 5:4-10
ወጪውን አስሉ
በርካታ አገሮች ሃይማኖታዊ የሆነ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች ተቀጥረው እንዲሠሩ አይፈቅዱም። ስለዚህ በውጭ አገር ለማገልገል የሚፈልጉ አብዛኛውን ጊዜ በገንዘብ ረገድ ራሳቸውን መቻል አለባቸው። በገንዘብ ረገድ የገጠማቸውን ይህን ፈታኝ ሁኔታ የተወጡት እንዴት ነው? አንዳንዶች አስፈላጊውን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ቤታቸውን ሸጠዋል አሊያም አከራይተዋል። ሌሎች ደግሞ የንግድ ቤታቸውን ሸጠዋል። አንዳንዶች ለዚህ ዓላማ ሲሉ ገንዘብ አጠራቅመዋል። እንዲሁም ሌሎች በውጭ አገር ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በመሥራት የተወሰነ ገንዘብ ካጠራቀሙ በኋላ እንደገና ለማገልገል ይሄዳሉ።
በአንድ የበለጸገ አገር ከመኖር ይልቅ በማደግ ላይ ባለ አገር መኖር ካለው ግልጽ የሆነ ብልጫ አንዱ ለኑሮ የሚያስፈልገው ወጪ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ አንዳንዶች መጠነኛ በሆነ የጡረታ አበል በበቂ ሁኔታ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል። እርግጥ የአንድ ሰው ወጪ በአመዛኙ በሚመርጠው የኑሮ ደረጃ ላይ የተመካ ነው። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች እንኳ ሳይቀር በጣም ምቹ የሆኑ መኖሪያዎች ማግኘት ይቻላል፤ ሆኖም ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል።
ቀደም ብሎ ወጪን ማስላት አስፈላጊ እንደሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ለኑሮ የሚያስፈልገውን ወጪ ማስላት ብቻ አይበቃም። ምናልባት በደቡብ አሜሪካ ያገለገሉ አንዳንዶች የሰጡት አስተያየት ትምህርት አዘል ሊሆን ይችላል።
ከሁሉ ይበልጥ ተፈታታኝ የሆነው ነገር
ከፊንላንድ የመጣው ማርኩ “ትልቅ ትግል የሆነብኝ ስፓንኛ መማር ነበር” ሲል ያስታውሳል። “ቋንቋውን ስለማልችል የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ ከመሾሜ በፊት የተወሰነ ጊዜ ያልፈኛል የሚል ግምት ነበረኝ። ከሁለት ወር በኋላ የመጽሐፍ ጥናት እንድመራ ስጠየቅ ፈጽሞ ያልጠበቅሁት ነገር ሆነብኝ! እርግጥ ነው የሚያሳፍሩኝ ብዙ ሁኔታዎች ገጥመውኛል። በተለይ በስም ረገድ እቸገር ነበር። አንድ ቀን ወንድም ሳንቾን ‘ወንድም ቻንቾ (አሳማ)’ ብዬ ጠራሁት። እንዲሁም እህት ሳላሚያን፣ ‘ማላሲያ (ክፉ)’ ብዬ እንደጠራኋት አስታውሳለሁ። ደግነቱ ወንድሞችና እህቶች በጣም ይታገሱኝ ነበር።” ከጊዜ በኋላ ማርኩ ከባለቤቱ ከሴሊን ጋር በዚያ አገር ለስምንት ዓመታት በወረዳ የበላይ ተመልካችነት አገልግሏል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰው የጄሲ ባለቤት ክሪስ እንዲህ ትላለች:- “እዚህ ከመጣን ከሦስት ወር በኋላ የነበረን የመጀመሪያው የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ትዝ ይለኛል። ወንድም ልባችንን ለመንካት በመጣር ምሳሌዎችን እየተጠቀመና አንዳንድ ጥሩ ነጥቦችን እየተናገረ እንደነበር መገመት ብችልም ሐሳቡን መረዳት ግን ሳልችል ቀረሁ። እዚያው አዳራሽ ውስጥ እያለሁ ማልቀስ ጀመርኩ። ስቅስቅ ብዬ በማልቀሴ ድምፄ ሁሉ ይሰማ ነበር። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ለወረዳ የበላይ ተመልካቹ ያለቀስኩበትን ምክንያት ለማስረዳት ሞከርኩ። ወንድም በጣም ያዘነልኝ ሲሆን እንደሌሎቹ ሁሉ ደጋግሞ ‘ቴን ፓሲየንሲያ ኤርማና ’ (‘አይዞሽ እህት፣ ታገሺ’) አለኝ። ከሁለት ይሁን ከሦስት ዓመታት በኋላ በድጋሚ ተገናኘንና ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት በመቻላችን ተደስተን ለ45 ደቂቃ ያህል አወራን።”
ሌላ ወንድም ደግሞ “ማጥናት አስፈላጊ ነው” ሲል ይገልጻል። “ቋንቋውን በማጥናት ረገድ ከፍተኛ ጥረት ባደረግን መጠን የሐሳብ ግንኙነት የማድረግ ችሎታችን ይበልጥ ይሻሻላል።”
እንዲህ ዓይነቱ ጥረት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉም ይስማሙበታል። አንድ ሰው አንድ አዲስ ቋንቋ ለመማር ጥረት ሲያደርግ ትሕትናን፣ ትዕግሥትንና ጽናትን ያዳብራል። ለሌሎች ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችለው ከፍተኛ አጋጣሚ ይከፈትለታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ስፓንኛ መማሩ በዓለም ዙሪያ ከ400 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ የሐሳብ ግንኙነት እንዲያደርግ ያስችለዋል። ከጊዜ በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ የተገደዱ ብዙ ወንድሞች ባካበቱት የቋንቋ ችሎታ ተጠቅመው አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ስፓንኛ የሆኑ ሰዎችን መርዳት ችለዋል።
የቤተሰብ ናፍቆትን በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል?
በአማዞን ክልል ከባለቤቷ ከጋሪ ጋር ያገለገለችው ዴብራ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “በ1989 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢኳዶር ስንመጣ ቤተሰቦቼ በጣም ይናፍቁኝ ነበር። በጉባኤ ባሉ ወንድሞችና እህቶች ላይ ይበልጥ መመካትን ተምሬአለሁ። ልክ እንደ ቤተሰቤ ናቸው።”
መግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ካረን እንዲህ ትላለች:- “በየቀኑ ወደ አገልግሎት በመውጣት የሚሰማኝን የናፍቆት ስሜት ተዋግቼዋለሁ። እንዲህ በማድረግ ስለ ቤተሰቦቼ እያሰብኩ በሐሳብ አልዋጥም ነበር። እንዲሁም ወላጆቼ እዚያ ሆነው በውጭ አገር መስክ በማከናውነው የአገልግሎት ሥራ እንደሚደሰቱ አስታውስ ነበር። እማማ፣ ‘ከእኔ ይልቅ ይሖዋ በተሻለ ሁኔታ ሊንከባከብሽ ይችላል’ በማለት ሁልጊዜ ታበረታታኝ ነበር።”
ከጃፓን የመጣችው ማኪኮ በቀልድ መልክ እንዲህ ስትል ታክላለች:- “ቀኑን ሙሉ ሳገለግል ከዋልኩ በኋላ በጣም ድክም ይለኛል። ስለዚህ ቤት ተመልሼ ቤተሰቦቼን መናፈቅ ስጀምር አብዛኛውን ጊዜ እንቅልፍ ይወስደኛል። በመሆኑም የሚሰማኝ ናፍቆት ለረጅም ጊዜ አይቆይም።”
ልጆችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል?
በጉዳዩ ልጆች የሚካተቱ ከሆነ እንደ ትምህርት ለመሳሰሉ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ትኩረት መሰጠት አለበት። በዚህ ረገድ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በቤት የሚሰጥ ትምህርት እንዲከታተሉ የመረጡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በአካባቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አስገብተዋቸዋል።
አል ወደ ደቡብ አሜሪካ የሄደው ሚስቱን፣ ሁለት ልጆቹንና እናቱን ይዞ ነው። እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ልጆቹን ትምህርት ቤት ማስገባታችን ቋንቋውን ወዲያውኑ ለመልመድ እንደረዳቸው ተገንዝበናል። በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ አቀላጥፈው መናገር ችለው ነበር።” በሌላ በኩል በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙት የማይክና የካሪ ሁለት ወንዶች ልጆች ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በአንድ እውቅ የመላላክ ትምህርት ቤት አማካኝነት ነው። ወላጆቹ እንዲህ ይላሉ:- “እንዲህ ዓይነቱን የትምህርት አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ በራሳቸው እንዲወጡት ለልጆቻችን ልንተውላቸው እንደማንችል ተረድተናል። እኛም በትምህርቱ መሳተፍና ልጆቹ ከተመደበላቸው ሥርዓተ ትምህርት ጋር እኩል መራመዳቸውን ማረጋገጥ ነበረብን።”
ከአውስትራሊያ የመጡት ዴቪድ እና ጃኒታ ስለ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው ያላቸውን ስሜት ገልጸዋል። “ሌሎች ሰዎች በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖሩ ልጆቻችን ራሳቸው እንዲያዩ ፈለግን። ሰው ሁሉ የእኛ ዓይነት የኑሮ ደረጃ እንዳለው አድርጎ ማሰብ ቀላል ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንዲህ ዓይነት የኑሮ ደረጃ ያላቸው ከዓለም ሕዝብ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። በተጨማሪም አገሩም ሆነ ባሕሉ ምንም ይሁን ምን በዓለም ዙሪያ ቲኦክራሲያዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ ማየት ችለዋል።”
“በ1969 ቤተሰባችን እንግሊዝን ለቅቆ ሲወጣ ገና የአራት ዓመት ልጅ ነበርኩ” ሲል ኬን ያስታውሳል። “ምንም እንኳ አስቤው እንደነበረ የሳር ክዳን ባለው ከጭቃ የተሠራ ጎጆ ውስጥ ባለመኖራችን ቅር ብሰኝም አንድ ልጅ ሊያገኘው የሚችለው በጣም አስደሳች የሆነ አስተዳደግ እንደነበረኝ ይሰማኛል። እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ላላገኙ ሌሎች ልጆች አዝንላቸው ነበር! ከሚስዮናውያንና ከልዩ አቅኚዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ስለነበረኝ በዘጠኝ ዓመቴ ረዳት አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ።” በአሁኑ ጊዜ ኬን ተጓዥ የበላይ ተመልካች ነው።
የጄሲ ልጅ ገብርኤላ “አሁን ኢኳዶር አገራችን ሆኗል!” ስትል በጉዳዩ መስማማቷን ገልጻለች። “ወላጆቼ እዚህ ለመምጣት መወሰናቸው በጣም ያስደስተኛል።”
በአንጻሩ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የመጡበት አገር ያልተስማማቸው ልጆች ነበሩ። በመሆኑም ቤተሰባቸው ወደ ትውልድ አገሩ ለመመለስ ተገድዷል። ከዚህ የተነሳ ወደ ውጭ አገር ከመዛወራችሁ በፊት አገሩን መጎብኘታችሁ የተሻለ ነው። በዚህ መንገድ በቀጥታ ራሳችሁ ባገኛችሁት መረጃ ላይ ተመሥርታችሁ ውሳኔ ማድረግ ትችላላችሁ።
ወደ ሌላ አገር ተዛውሮ ማገልገል የሚያስገኛቸው በረከቶች
ወደ ባዕድ አገር ሄዶ ማገልገል ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዳሉትና መሥዋዕትነት እንደሚጠይቅ የተረጋገጠ ነው። ታዲያ ይህን ያደረጉ ሰዎች የሚክስ ሆኖ አግኝተውታልን? እስቲ ከራሳቸው አንደበት እንስማ።
ጄሲ:- “በአምባቶ ከተማ ባሳለፍናቸው አሥር ዓመታት ውስጥ የጉባኤዎቹ ቁጥር ከ2 ተነስቶ 11 ሲደርስ ተመልክተናል። ከእነዚህ ውስጥ አምስት ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ የመርዳት መብት አግኝተናል፤ እንዲሁም በሁለት የመንግሥት አዳራሽ ግንባታዎች ላይ ተሳትፈናል። በተጨማሪም በአማካይ በዓመት ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለጥምቀት ብቁ እንዲሆኑ በመርዳት ደስታ አግኝተናል። የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር ከአሥር ዓመት በፊት አለመምጣቴ ብቻ ነው።”
ሊንዳ:- “ሰዎቹ ለምሥራቹና እኛ ለምናደርገው ጥረት ያላቸው አድናቆት ከፍተኛ ብርታት ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል ጫካ ውስጥ በሚገኝ መንደር ውስጥ የሚኖር አልፎንሶ የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እርሱ በሚኖርበት አካባቢ የሕዝብ ንግግር ቢሰጥ በጣም ጠቃሚ እንደሚሆን ተሰማው። አዲስ ተሠርቶ ወዳለቀው የእንጨት ቤት የገባው በቅርቡ ነበር። ቤቱ ደግሞ መንደሩ ውስጥ ካሉት ጥቂት ቤቶች አንዱ ነው። ከተማው ውስጥ ካሉት ሕንፃዎች ለይሖዋ ሊሰጥ የሚገባው የእርሱ ቤት ብቻ እንደሆነ ስለተሰማው በፊት ይኖርበት ወደነበረው የሳር ጎጆ በመመለስ ቤቱን የመንግሥት አዳራሽ አድርገው እንዲጠቀሙበት ለወንድሞች ሰጣቸው።”
ጂም:- “አገልግሎት ላይ በትክክል ሰዎችን እያነጋገርን የምናሳልፈው ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከምናሳልፈው በአሥር እጥፍ ይበልጣል። በተጨማሪም እዚህ ለመኖር የሚደረገው ሩጫ ይበልጥ ቀላል ነው። ጥናትና መስክ አገልግሎት ላይ የሚውል ሰፋ ያለ ጊዜ እንደሚገኝ ምንም ጥርጥር የለውም።”
ሳንድራ:- “የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሰዎች ከበፊቱ የተሻለ አቋም እንዲኖራቸው እንዴት መለወጥ እንደሚችል ማየት ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልኛል። አንድ ወቅት ላይ፣ የአንድ ትንሽ ግሮሰሪ ባለቤት የሆነችውን የ69 ዓመቷን አማዳ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናት ነበር። ሁልጊዜ በእያንዳንዱ አሥር እጅ ወተት ውስጥ ሁለት እጅ ውኃ ትጨምር ነበር። በተጨማሪም ይህን በውኃ የቀጠነ ወተት ከመለኪያው አሳንሳ በመሸጥ ደንበኞቿን ታጭበረብር ነበር። ይሁን እንጂ አማዳ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ 13ኛ ምዕራፍ ላይ ‘ሐቀኝነት ደስታ ያስገኛል’ በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የቀረበውን ትምህርት ካጠናች በኋላ እነዚህን መጥፎ ተግባሮች አቆመች። ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ስትጠመቅ ማየቴ ምንኛ አስደስቶኝ ነበር!”
ካረን:- “ይህን ያህል በይሖዋ ላይ ትምክህት ኖሮኝም ሆነ እዚህ እያለሁ ለሥራው የተጠቀመብኝን ያህል እርሱን አገልግየው አላውቅም። ከይሖዋ ጋር ያለኝ ጓደኝነት ይበልጥ ጥብቅና ጠንካራ ሆኗል።”
አንተስ ምን ታስባለህ?
ባለፉት ዓመታት በሙሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በባዕድ አገር ለማገልገል ከአገራቸው ወጥተዋል። አንዳንዶች ለአንድ ወይም ለሁለት ዓመት ሲቆዩ ሌሎች ደግሞ እዚያው ቀጥለዋል። በውጭ አገር የአገልግሎት መስክ የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማስፋፋት ግብ በማውጣት ያካበቱትን ልምድ፣ መንፈሳዊ ጉልምስናና ቁሳዊ ሃብት ይዘው ይመጣሉ። በአካባቢው ያሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በዓለማዊ ሥራ እጦት ምክንያት አገልግሎታቸውን ማከናወን ባልቻሉባቸው አካባቢዎች ማገልገል ችለዋል። በባለ ከባድ ማርሽ መኪና ካልሆነ ሊደረስባቸው የማይችሉ ክልሎችን ለመሸፈን ሲሉ ብዙዎች ሪዶታ ያላቸው መኪናዎች ገዝተዋል። ሌሎች ደግሞ ከተማ ውስጥ ለመኖር በመምረጥ ጥቂት ሽማግሌዎች ባሉባቸው ትልልቅ ጉባኤዎች ውስጥ ጉባኤውን በማጠናከር ድርሻ አበርክተዋል። ሆኖም ሁሉም በመንፈሳዊ በረከቶች ረገድ ከሰጡት ይልቅ ያገኙት እጅግ እንደሚበልጥ ይስማማሉ።
በባዕድ አገር ለማገልገል ባለው መብት መካፈል ትችላለህን? ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ ሌላ አገር ሄዶ ለማገልገል ያለውን አጋጣሚ ለምን አታጤነውም? የመጀመሪያውና አስፈላጊ የሆነው እርምጃ ለማገልገል ባሰብከው አገር ወደሚገኘው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ መጻፍ ይሆናል። ከማኅበሩ የምታገኘው ግልጽ የሆነ መረጃ እዚያ ሄደህ ማገልገልህ ስኬታማ የመሆኑን አጋጣሚ እንድታመዛዝን ይረዳሃል። በተጨማሪም በነሐሴ 15, 1988 የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ “ከአገርህና ከዘመዶችህ ተለይተህ ውጣ” ከሚለው ርዕስ ብዙ ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦች ማግኘት ትችላለህ። ጥሩ ዕቅድ በማውጣትና የይሖዋን በረከት በማግኘት ምናልባት አንተም በባዕድ አገር ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ መቅመስ ትችላለህ።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቶም እና ሊንዳ ረጅሙን የእግር መንገድ ተከትለው የሽዋር ሕንዶች ማኅበረሰብ ወደሚኖሩበት ሲያቀኑ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎች በኢኳዶር ዋና ከተማ በኩዌቶ ያገለግላሉ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማኪኮ በኤንዲስ ተራራዎች ሲሰብክ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሂልቢግ ቤተሰብ ላለፉት አምስት ዓመታት በኢኳዶር ሲያገለግል ቆይቷል