‘ወደ መቄዶንያ መሻገር’ ትችላለህ?
1. ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?
1 በ49 ዓ.ም. አካባቢ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ለማድረግ በሶርያ ከምትገኘው አንጾኪያ ተነሳ። የጉዞው ዓላማ ኤፌሶንንና በትንሿ እስያ የሚገኙ ሌሎች ከተሞችን መጎብኘት ነበር። ሆኖም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ባየው ራእይ ላይ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” የሚል ግብዣ ቀረበለት። ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ይህን ግብዣ በደስታ ተቀብለው ወደዚያ አካባቢ በመሄዳቸው በቦታው የመጀመሪያውን ጉባኤ የማቋቋም መብት አግኝተዋል። (ሥራ 16:9, 10፤ 17:1, 2, 4) ዛሬም በአንዳንድ የምድር ክፍሎች ተጨማሪ የመከሩ ሥራ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። (ማቴ. 9:37, 38) አንተስ ወደዚያ ሄደህ መርዳት ትችላለህ?
2. አንዳንዶች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረው ለማገልገል ሳያስቡ የቀሩት ለምን ሊሆን ይችላል?
2 ምናልባት አንተም ልክ እንደ ጳውሎስ የሚስዮናዊነት መንፈስ ሊኖርህ ይችላል፤ ሆኖም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ስለመዛወር በቁም ነገር አስበህ አታውቅ ይሆናል። አሊያም በዕድሜህ ምክንያት ወይም ትንንሽ ልጆች ስላሉህ ጊልያድ ገብተህ ሥልጠና መውሰድ አልቻልክ ይሆናል፤ ነጠላ እህት በመሆንሽ ደግሞ በዚህ ትምህርት ቤት መካፈል አልቻልሽ ይሆናል። ምናልባትም “መቄዶንያ” ለመሄድ ያላሰብከው አዲስ ቋንቋ መማር እንደማትችል ስለተሰማህ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አሁን ወዳለህበት አገር በስደት የመጣኸው በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች የተነሳ በመሆኑ ወደነበርክበት ቦታ ለመመለስ እያቅማማህ ይሆናል። ይሁንና ጉዳዩን በጸሎት ብታስብበት እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረህ ከማገልገል ሊያግዱህ እንደማይችሉ ልትገነዘብ ትችላለህ።
3. የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውሮ ለማገልገል የተለየ ሥልጠና ማግኘት የግድ አስፈላጊ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
3 የተለየ ሥልጠና ማግኘት የግድ ያስፈልጋል? ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ውጤታማ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ምን ነበር? በይሖዋና እሱ በሚሰጠው ቅዱስ መንፈስ መተማመናቸው ነው። (2 ቆሮ. 3:1-5) ስለዚህ ያለህበት ሁኔታ የተለየ ሥልጠና እንድትወስድ ባይፈቅድልህም እንኳ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደህ በማገልገል ረገድ ውጤታማ ልትሆን ትችላለህ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በአገልግሎት ስብሰባ አማካኝነት ዘወትር ሥልጠና እያገኘህ መሆኑን አትዘንጋ፤ የምታገለግልበት ቦታ የትም ይሁን የት ከዚህ ሥልጠና ጥቅም ማግኘትህ አይቀርም።
4. በጡረታ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ክልል ተዛውረው ማገልገል እንደማይችሉ ሊሰማቸው የማይገባው ለምንድን ነው?
4 በጡረታ ዕድሜ የሚገኙ፦ በመንፈሳዊ የጎለመሱና አንጻራዊ ጤንነት ያላቸው በጡረታ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ተዛውረው በማገልገል ከፍተኛ እገዛ ሊያበረክቱ ይችላሉ። አንተስ ጡረታ ወጥተሃል? መጠነኛ የጡረታ አበል የሚያገኙ አንዳንድ ወንድሞች ከመጡበት አካባቢ ጋር ሲወዳደር በጣም ዝቅተኛ የሆነ ወጪ ስለሚያወጡ በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ጥሩ ኑሮ መምራት ይችላሉ።
5. ጡረታ ከወጣ በኋላ እርዳታ ወደሚያስፈልገው ቡድን ስለተዛወረ አንድ ወንድም ተሞክሮ ተናገር።
5 የጉባኤ ሽማግሌና አቅኚ የሆነ አንድ ጡረታ የወጣ ወንድም ዘጠኝ አስፋፊዎች ያሉበትን አንድን ቡድን ለመርዳት ወደዚያ ተዛወረ። በሁለት ዓመት ውስጥ የቡድኑ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ወደ 50 ከፍ አለ። ይህ ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወደ እዚህ ክልል መምጣቴ እስከ ዛሬ አግኝቼው የማላውቀውን የተትረፈረፈ በረከት እንዳገኝ አስችሎኛል። ያገኘሁትን በረከት በጥቂቱ እንኳ ልናገር ብል ጊዜ አይበቃኝም!”
6. የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ክልል የተዛወረች አንዲት ነጠላ እህት ያጋጠማትን ተሞክሮ ተናገር።
6 ነጠላ እህቶች፦ ይሖዋ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ክልል ምሥራቹን ለማዳረስ በእህቶች እየተጠቀመ ነው። (መዝ. 68:11) አንዲት ወጣት እህት እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ክልል ሄዳ አገልግሎቷን ለማስፋት ግብ ነበራት፤ ሆኖም ወላጆቿ የደኅንነቷ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ተገነዘበች። በመሆኑም ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ጽፋ ዝርዝር መመሪያ በመጠየቅ ጠቃሚ መረጃ አገኘች። በአዲሱ ክልሏ ውስጥ ባገለገለችባቸው ስድስት ዓመታት ውስጥ ስላገኘቻቸው የተትረፈረፉ በረከቶች ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በትውልድ ቦታዬ ሳለሁ ጥናቶች ለማግኘት ያለኝ አጋጣሚ ውስን ነበር። ሆኖም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውሬ ማገልገሌ ብዙ ጥናቶችን እንድመራ እንዲሁም የማስተማር ችሎታዬን እንዳሻሽል ረድቶኛል።”
7. የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ክልል ስለተዛወረ አንድ ቤተሰብ ተሞክሮ ተናገር።
7 ቤተሰቦች፦ ወላጅ ከሆንክ፣ ትንንሽ ልጆች ያሉህ መሆኑ ምሥራቹን ለማስፋፋት ‘ወደ መቄዶንያ’ እንዳትዛወር ሊያግድህ ይችላል? የስምንትና የአሥር ዓመት ልጆች ያሉት አንድ ቤተሰብ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ለመዛወር አሰበ። እናትየው ቤተሰቡ ያጋጠመውን ተሞክሮ አስመልክታ ስትጽፍ እንዲህ ብላለች፦ “ልጆቻችንን እዚህ ማሳደግ በመቻላችን አመስጋኞች ነን፤ ምክንያቱም ልጆቻችን ከልዩ አቅኚዎችና ከሚስዮናውያን ጋር መቀራረብ ችለዋል። እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ተዛውረን ማገልገላችን በሕይወታችን ይበልጥ ደስተኞች እንድንሆን አድርጎናል።”
8. ቋንቋ ሳይማሩ ወደ ሌላ ክልል ሄዶ ማገልገል ይቻላል? አብራራ።
8 የቋንቋ ጉዳይ ሊያሳስብህ ይገባል? ወደ ሌላ ክልል ተዛውረህ ከማገልገል ወደኋላ ያልከው አዲስ ቋንቋ መማር እንደማትችል ስለተሰማህ ይሆን? ምናልባት አንተ የምትናገረው ቋንቋ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ሌሎች ክልሎችም ይነገር ይሆናል። አንድ ባልና ሚስት እርዳታ ወደሚያስፈልገው ጉባኤ ከመዛወራቸው በፊት ሁለት ጊዜ ወደዚያ ጉባኤ ሄደው ነበር፤ በኋላም ወደ ጉባኤያቸው በመመለስ ወርኃዊ ወጪዎቻቸውን ቀንሰው ለአንድ ዓመት ገንዘብ አጠራቀሙ። ሙሉ በሙሉ ወደዚያ ጉባኤ ለመዛወር ሲወስኑ የአካባቢው ወንድሞች በጥሩ ዋጋ ቤት ማግኘት እንዲችሉ ረዷቸው።
9, 10. ከትውልድ አገራቸው ተሰደው በሌላ አገር የሚኖሩ ወንድሞች ስለ ምን ነገር ሊያስቡ ይችላሉ? ለምንስ?
9 ስደተኞች፦ አሁን የምትኖረው በባዕድ አገር ነው? ምናልባትም አሁን ወደምትኖርበት አገር የመጣኸው እውነትን ከመስማትህ በፊት ሊሆን ይችላል። በትውልድ አገርህ ተጨማሪ የመከሩ ሠራተኞች ያስፈልጉ ይሆን? አንተስ ተመልሰህ እዚያ ማገልገል ትችላለህ? ሥራና መኖሪያ ማግኘት ከሌላ አገር ሰው ይልቅ ለአንተ ሊቀል ይችላል። የክልሉን ቋንቋ እንደምትችልም እሙን ነው። በተጨማሪም ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ከውጪ የመጣ ሰው ከሚነግራቸው ይልቅ አንተ ብትነግራቸው ይቀበሉ ይሆናል።
10 አንድ ሰው በስደት ከአልባንያ ወደ ጣሊያን ይሄዳል፤ ይህ ሰው በጣሊያን ጥሩ ሥራ ከያዘ በኋላ አልባንያ ለሚገኙት ቤተሰቦቹ ገንዘብ መላክ ጀመረ። ወደ እውነት ከመጣ በኋላ፣ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ላሉ ጣሊያናውያን ልዩ አቅኚዎች የአልባንያን ቋንቋ ማስተማር ጀመረ። ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እነዚህ ሰዎች እኔ ትቼው ወደመጣሁት አገር እየሄዱ ነው። ቋንቋውን መናገር ባይችሉም እንኳ ወደ እዚያ ለመሄድ በጣም ጓጉተዋል። እኔ ቋንቋውን መናገር የምችል ከመሆኑም በላይ ባሕሉን አውቃለሁ። ታዲያ እዚህ ጣሊያን ተቀምጬ ምን እሠራለሁ?” ይህ ወንድም ወደ አልባንያ ተመልሶ ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ለመካፈል ወሰነ። እንዲህ ብሏል፦ “በጣሊያን የነበረኝን ሥራና የማገኘውን ገንዘብ ትቼ በመሄዴ ይጸጽተኝ ይሆን? ለደቂቃ እንኳ አስቤው አላውቅም! በአልባንያ እውነተኛ ሥራ አግኝቻለሁ። እኔ እንደሚሰማኝ ከሆነ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ዘላቂ ደስታ የሚያስገኘው ሥራ ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገል ነው!”
11, 12. የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመዛወር የሚያስቡ ወንድሞች ምን ማድረግ አለባቸው?
11 ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ወደ መቄዶንያ ከመሄዳቸው በፊት እየተጓዙ የነበረው ወደ ምዕራብ ነበር፤ ሆኖም ‘መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው’ ወደ ሰሜን አቀኑ። (ሥራ 16:6) ቢቲኒያ አቅራቢያ ሲደርሱ ኢየሱስ እዚያ እንዳይገቡ ከለከላቸው። (ሥራ 16:7) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት የስብከቱን ሥራ እየተቆጣጠረው ነው። (ማቴ. 28:20) ስለዚህ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረህ የማገልገል ሐሳብ ካለህ በጸሎት አማካኝነት የይሖዋን አመራር ጠይቅ።—ሉቃስ 14:28-30፤ ያዕ. 1:5
12 ወደ ሌላ ቦታ ብትዛወር ውጤታማ መሆን ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንዲሁም ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖችን አማክር። (ምሳሌ 11:14፤ 15:22) ልትዛወር ወዳሰብክበት ቦታ አስቀድመህ በመሄድ ምናልባትም ትንሽ ረዘም ያለ ጊዜ እዚያ በመቆየት ሁኔታውን ማጥናት ትችላለህ? ለመዛወር ከወሰንክ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ መጻፍ ትችላለህ። ሆኖም ደብዳቤውን በቀጥታ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ከመላክ ይልቅ ለጉባኤህ ሽማግሌዎች ስጣቸው፤ እነሱም አስተያየታቸውን አክለው ደብዳቤውን ወደ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልኩታል።—የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ ከገጽ 111-112 ተመልከት።
13. ቅርንጫፍ ቢሮው በምን ረገድ ሊረዳህ ይችላል? የአንተስ ኃላፊነት ምንድን ነው?
13 ቅርንጫፍ ቢሮው ውሳኔ በማድረግ ረገድ አንተን ለመርዳት ስለ ክልሉ ጠቃሚ መረጃዎችን ይልክልሃል፤ ይህ ሲባል ግን ስፖንሰር ይሆንሃል ወይም መኖሪያ ቤት ያፈላልግልሃል ማለት አይደለም። እነዚህ ነገሮች ከመዛወርህ በፊት አንተው ራስህ አጣርተህ ልትፈጽማቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። ወደ ሌላ ቦታ የሚዛወሩ ሁሉ የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት መቻል ይኖርባቸዋል።—ገላ. 6:5
14. ወደ ሌላ ቦታ መዛወር የማይችሉ ወንድሞች አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚችሉት እንዴት ነው?
14 ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ባትችልስ? ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ካልቻልክ ተስፋ አትቁረጥ። ምናልባት ሌላ “ትልቅ የሥራ በር” ይከፈትልህ ይሆናል። (1 ቆሮ. 16:8, 9) የወረዳ የበላይ ተመልካችህ ካለህበት ቦታ እየተመላለስክ ልትረዳው የምትችል ጉባኤ ያውቅ ይሆናል። ምናልባትም በአቅራቢያህ የሚገኝ አንድ ጉባኤ ወይም ቡድን መርዳት ትችል ይሆናል። አሊያም ደግሞ ባለህበት ጉባኤ አገልግሎትህን ማስፋት ትችላለህ። ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ዋናው ነገር አገልግሎትህን በሙሉ ነፍስህ ማከናወንህ ነው።—ቆላ. 3:23
15. ወንድሞች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ተዛውረው ማገልገል እንደሚፈልጉ ቢነግሩን ምላሻችን ምን መሆን ይኖርበታል?
15 የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ የማገልገል ግብ ያለው በመንፈሳዊ የጎለመሰ ክርስቲያን ታውቃለህ? ከሆነ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርግለት፤ እንዲሁም አበረታታው! ጳውሎስ የነበረባት የሶርያዋ አንጾኪያ በሮም ግዛት ውስጥ ካሉ ከተሞች መካከል በስፋቷ ከሮምና ከእስክንድሪያ ቀጥሎ ሦስተኛ ነበረች። የአንጾኪያ ጉባኤ ሰፊ የአገልግሎት ክልል ስለነበረው የጳውሎስ በዚያ መቆየት ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው፤ በመሆኑም እሱ ወደ ሌላ ቦታ መሄዱ ጉባኤውን ያጎድል ነበር። ሆኖም በዚያ ጉባኤ የነበሩት ወንድሞች ጳውሎስ እንዳይሄድ ሊያከላክሉት እንደሞከሩ መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። እነዚህ ክርስቲያኖች ስለራሳቸው ጉባኤ ብቻ ከማሰብ ይልቅ “እርሻው ዓለም” እንደሆነ ያስታወሱ ይመስላል።—ማቴ. 13:38
16. ‘ወደ መቄዶንያ ተሻግረን እንድንረዳ’ የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ?
16 ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ወደ መቄዶንያ ተሻግረው እንዲረዱ ለቀረበላቸው ግብዣ ምላሽ በመስጠታቸው በእጅጉ ተባርከዋል። በመቄዶንያ ወደምትገኘው ወደ ፊልጵስዩስ በሄዱበት ጊዜ ሊድያን ያገኙ ሲሆን “ይሖዋም ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል እንድትሰማ ልቧን በደንብ ከፈተላት።” (ሥራ 16:14) ጳውሎስና ሚስዮናዊ ጓደኞቹ ሊድያና መላው ቤተሰቧ በተጠመቁ ጊዜ ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ማየት ትችላለህ! በብዙ አካባቢዎች እንደ ሊድያ ያሉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመንግሥቱ መልእክት ገና አልደረሳቸውም። አንተም ‘ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ’ ሰዎችን መርዳት የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም ትችላለህ።