ወደ መቄዶንያ መሻገር ትችላለህ?
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የትንሿ እስያ የወደብ ከተማ በሆነችው በጥሮአስ ሳለ ራእይ ተመለከተ። በዚህ ራእይ ላይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ “ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን” ብሎ ሲለምነው ተመለከተ። ጳውሎስ ይህን ራእይ ከተመለከተ በኋላ እሱና የጉዞ ጓደኞቹ “አምላክ ምሥራቹን እንድንሰብክላቸው [ወደ መቄዶንያ] ጠርቶናል የሚል መደምደሚያ ላይ” ደረሱ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የመቄዶንያ አውራጃ ቁልፍ ከተማ በሆነችው በፊልጵስዩስ የሚኖሩ ሊዲያና ቤተሰቦቿ ክርስቲያኖች ሆኑ። የሮም ግዛት በሆነችው በመቄዶንያ የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችም ከዚያ በኋላ ክርስትናን ተቀብለዋል።—ሥራ 16:9-15
በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አንዳንድ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ መንፈስ አሳይተዋል። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው ወጪ ለማገልገል የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ተዛውረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በካናዳ ትኖር የነበረችው ሊሳ ለአገልግሎቷ የበለጠ ትኩረት መስጠት ትፈልግ ነበር። በመሆኑም ወደ ኬንያ ሄዳ በዚያ መኖር ጀመረች። ትሬቨር እና ኤመሊ የተባሉ ካናዳውያን ባልና ሚስትም አገልግሎታቸውን ለማስፋት በማሰብ ማላዊ ሄደው መኖር ጀመሩ። ፖልና ማጊ የተባሉ እንግሊዛውያንም ጡረታ መውጣታቸው በይሖዋ አገልግሎት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ከፍ ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ስለከፈተላቸው ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አቀኑ። አንተስ እንዲህ ያለው የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ አለህ? ወደ ሌላ አካባቢ ሄደህ ለማገልገል ታስባለህ? ከሆነ ስኬታማ እንድትሆን ሊረዱህ የሚችሉ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ጠቃሚ ሐሳቦች አሉ?
ራስህን ገምግም
በመጀመሪያ ደረጃ ‘ወደ ሌላ አካባቢ እንድሄድ የሚገፋፋኝ ነገር ምንድን ነው?’ የሚለውን ጉዳይ ልታስብበት ይገባል። ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” የሚለው እንደሆነ ተናግሯል። በመሆኑም ወደ ሌላ አገር ሄደን እንድናገለግል የሚገፋፉን ምክንያቶች ለአምላክ ያለን ፍቅርና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ተልዕኮ ለመፈጸም ያለን ፍላጎት ናቸው። ኢየሱስ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።” ሰዎችን ከልብ ለመርዳት ያለን ፍላጎት ለእነሱ ፍቅር እንዳለን ያሳያል። (ማቴ. 22:36-39፤ 28:19, 20) ወደ ሌላ አገር ሄዶ ማገልገል አብዛኛውን ጊዜ ተግቶ መሥራትና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ይጠይቃል። ይህ ጀብድ ለመሥራት ሲባል የሚደረግ ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሚገፋፋህ ኃይል ፍቅር መሆን አለበት። ከኔዘርላንድ ወደ ናሚቢያ ሄደው በማገልገል ላይ የሚገኙት ሬምኮና ሱዛን “እዚሁ እንድንቆይ ያደረገን ፍቅር ነው” በማለት ሁኔታውን ጠቅለል አድርገው ገልጸውታል።
በናሚቢያ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግለው ዊሊ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ሌላ አገር ሄደው እዚያው የቆዩ ወንድሞችና እህቶች ወደዚያ የሄዱት ‘የአካባቢው ወንድሞች ይንከባከቡናል’ በሚል ስሜት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከአካባቢው ወንድሞች ጋር ለማገልገልና በስብከቱ ሥራ እነሱን ለመርዳት አስበው ነው።”
ወደ ሌላ አገር እንድትሄድ የሚገፋፋህ ዝንባሌ ምን እንደሆነ ከገመገምክ በኋላ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በሌላ አገር ሄጄ ሳገለግል ልጠቀምበት የምችል ምን ተሞክሮ አለኝ? ውጤታማ አገልጋይ ነኝ? የትኞቹን ቋንቋዎች መናገር እችላለሁ? ሌላ ቋንቋ ለመማር ፈቃደኛ ነኝ?’ ጉዳዩን አንስተህ ከቤተሰብህ ጋር በቁም ነገር ተነጋገርበት። የጉባኤህን ሽማግሌዎች አማክር። በተጨማሪም ወደ ይሖዋ ጸልይ። በዚህ መንገድ ራስህን በሐቀኝነት መመርመርህ ሌላ አገር ሄደህ የማገልገል ችሎታውም ሆነ ቁርጠኝነቱ እንዳለህ ለማወቅ ይረዳሃል።—“ራስህን እወቅ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ማገልገል የምትችለው የት ነው?
ጳውሎስ ወደ መቄዶንያ እንዲሄድ የተነገረው በራእይ ነበር። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የት ማገልገል እንደምንችል በራእይ አይነግረንም። ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች ተጨማሪ ሰባኪዎች የሚያስፈልጉባቸው ብዙ ቦታዎች እንዳሉ በመጠበቂያ ግንብና በሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት መገንዘብ ችለዋል። ስለሆነም በመጀመሪያ እነዚህን ቦታዎች በዝርዝር ጻፋቸው። ሌላ ቋንቋ ለመማር ዝግጁ ካልሆንክ አሊያም በምትሄድበት አገር ለዘለቄታው የመኖር ሐሳብ ከሌለህ የራስህ ቋንቋ በሰፊው ወደሚነገርበት አገር ሄደህ ማገልገል ትችላለህ። ከዚያ በኋላ ትራንስፖርትን፣ ቪዛን፣ ደኅንነትን፣ ለኑሮ የሚያስፈልግህን ወጪ እንዲሁም የአየሩን ሁኔታ በተመለከተ መረጃዎችን አሰባስብ። ከዚህ በፊት ወደዚያ አካባቢ የሄዱትን ሰዎች መጠየቅም ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። እነዚህን መረጃዎች ተጠቅመህ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንድትችል እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው። ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ‘ቃሉን በእስያ አውራጃ እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ከልክሏቸው’ እንደነበር አስታውስ። ወደ ቢቲኒያ ለመግባት በሞከሩ ጊዜም “የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም።” አንተም ይበልጥ መርዳት የምትችለው የት ብትሄድ እንደሆነ ለመወሰን ጊዜ ሊወስድብህ ይችላል።—ሥራ 16:6-10
ይህንን ሁሉ ካደረግክ በኋላ ለአንተ ተስማሚ የሆኑ አማራጮችን ማግኘትህ አይቀርም። በሌላ አገር ለማገልገል ከወሰንክ እንደ አማራጭ በያዝካቸው አገሮች ውስጥ ወደሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ደብዳቤ ጻፍ። በደብዳቤህ ላይ ከዚህ ቀደም የነበረህንም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ያለህን የአገልግሎት መብት መጥቀስ ትችላለህ። በተጨማሪም ለኑሮና ለማረፊያ ቤት ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅብህ እንዲሁም በአካባቢው ምን ዓይነት የጤና ተቋማትና የሥራ መስኮች እንዳሉ መጠየቅ ትችላለህ። ከዚያም ለተለያዩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የጻፍካቸውን ደብዳቤዎች ለጉባኤህ የአገልግሎት ኮሚቴ ስጥ። እነሱ ደግሞ የራሳቸውን የድጋፍ ደብዳቤ አያይዘው ወደምትፈልጋቸው ቅርንጫፍ ቢሮዎች በቀጥታ ይልኩልሃል። ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ የሚሰጡህ መልስ ይበልጥ ውጤታማ አገልግሎት ልታከናውን የምትችለው የት እንደሆነ ለመወሰን ሊረዳህ ይችላል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዊሊ እንዲህ ብሏል፦ “ጠቅልለው ከመግባታቸው በፊት አገሩን ሄደው በማየት ደስ ብሏቸው ሊኖሩባቸው የሚችሉባቸውን ቦታዎች የመረጡ ወንድሞችና እህቶች እዚያው የመቆየታቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው። አንድ ባልና ሚስት ገጠራማ በሆነ አካባቢ መኖር በጣም እንደሚያስቸግራቸው ተገነዘቡ። በመሆኑም ደስ ብሏቸው እንዲኖሩ የሚያስችላቸው የኑሮ ደረጃ ባለው ትንሽ ከተማ ውስጥ መኖር ጀመሩ፤ እርግጥ እዚህም ተጨማሪ ሰባኪዎች ያስፈልጉ ነበር።”
ተፈታታኝ የሆኑ አዳዲስ ችግሮችን መቋቋም
ከትውልድ አካባቢህ ርቀህ በመሄድ ሙሉ በሙሉ አዲስ በሆነ አካባቢ መኖር ስትጀምር አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙህ እሙን ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሊሳ “የብቸኝነት ስሜት በጣም አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ይችላል” በማለት ተናግራለች። ታዲያ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳት ምንድን ነው? በአዲሱ መኖሪያዋ አካባቢ ካለው ጉባኤ አባላት ጋር በጣም መቀራረቧ ነው። የሁሉንም የጉባኤ አባላት ስም በቃሏ ለመያዝ ትጥር ነበር። ይህን ጥረቷን ከግብ ለማድረስ ቀደም ብላ ወደ ስብሰባዎች የምትሄድ ሲሆን ስብሰባው ካለቀ በኋላ ደግሞ ከወንድሞችና እህቶች ጋር ትጫወታለች። ሊሳ ከሌሎች ጋር አብራ በማገልገልና ብዙዎችን ቤቷ በመጋበዝ አዳዲስ ወዳጆችን አፍርታለች። “የከፈልኩት መሥዋዕትነት ምንም አይቆጨኝም። ደግሞም ይሖዋ ባርኮኛል” ብላለች።
ፖልና ማጊ፣ ልጆቻቸው ራሳቸውን ሲችሉ ለ30 ዓመት የኖሩበትን ቤት ትተው ወደ ሌላ አገር ሄዱ። ፖል እንዲህ ብሏል፦ “ንብረታችንን ትተን መምጣት እንደጠበቅነው ቀላል አልነበረም። ይበልጥ ከባድ የነበረው ደግሞ ከቤተሰቦቻችን መለየታችን ነበር። አውሮፕላን ውስጥ እያለን ስቅስቅ ብለን አለቀስን። በዚህ ዓይነት ሁኔታ መሄድ እንደማንችል ተሰምቶን ነበር። ይሁንና በይሖዋ ተማምነን ጉዟችንን ቀጠልን። አዳዲስ ወዳጆችን ማፍራታችን በውሳኔያችን እንድንጸና ረድቶናል።”
ግሬግና ክሪስተል ከካናዳ ወደ ናሚቢያ ለመሄድ የመረጡት የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ እንግሊዝኛ ስለነበር ነው። ያም ሆኖ ከጊዜ በኋላ የአገሬውን ቋንቋ መማራቸው ጠቃሚ እንደሆነ ተገነዘቡ። እንዲህ ብለዋል፦ “ተስፋ የቆረጥንባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁን እንጂ የአገሬውን ቋንቋ ስንማር ባሕሉን ማወቅ ችለናል። እዚያ ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረባችንም አዲሱን መኖሪያችንን እንድንለምድ ረድቶናል።”
እንዲህ ያለው የትሕትና መንፈስና የፈቃደኝነት ዝንባሌ በአካባቢው ወንድሞች ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ጄኒ፣ እሷ ባደገችበት በአየርላንድ ለማገልገል ከሌላ አገር ስለመጡ ቤተሰቦች ጥሩ ትዝታ አላት። እንዲህ ብላለች፦ “የሚቀረቡ ሰዎች ነበሩ። የመጡት ለማገልገል እንጂ ሌሎች እንዲያገለግሏቸው አልነበረም። በአገልግሎታቸው ቀናተኞችና ደስተኞች ስለነበሩ እኔም እንደ እነሱ ሌላ አገር ሄጄ ለማገልገል ተነሳሳሁ።” በአሁኑ ጊዜ ጄኒ ከባለቤቷ ጋር ሆና ጋምቢያ ውስጥ በሚስዮናዊነት በማገልገል ላይ ትገኛለች።
የይሖዋ በረከት “ብልጽግናን ታመጣለች”
ጳውሎስ በመቄዶንያ ማገልገሉ ብዙ በረከት አስገኝቶለታል! ወደ አሥር ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ወንድሞች “እናንተን ባስታወስሁ ቁጥር አምላኬን አመሰግናለሁ” በማለት ጽፎላቸው ነበር።—ፊልጵ. 1:3
ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊት በማላዊ ያገለገሉት ትሬቨርና ኤመሊ ልክ እንደ ጳውሎስ ተሰምቷቸው ነበር። እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “ትክክለኛ እርምጃ መውሰዳችንን የተጠራጠርንባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ሆኖም ደስተኞች ነበርን። እርስ በርሳችን በጣም የተቀራረብን ከመሆኑም በላይ የይሖዋ በረከት እንዳልተለየን ይሰማናል።” ቀደም ሲል የተጠቀሱት ግሬግና ክሪስተል ደግሞ “ከዚህ የተሻለ ሊያስደስተን የሚችል ሥራ የለም” ብለዋል።
እርግጥ ነው፣ ሁሉም ሰው ሌላ አገር ሄዶ ማገልገል ይችላል ማለት አይደለም። አንዳንዶች አገራቸው ውስጥ እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደው ቢያገለግሉ የተሻለ ውጤት ሊያገኙ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ትንሽ ራቅ ብሎ ወደሚገኝ አንድ ጉባኤ ሄደው የማገልገል ግብ ሊያወጡ ይችላሉ። ዋናው ነገር ይሖዋን ለማገልገል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግህ ነው። (ቆላ. 3:23) እንዲህ ካደረግህ ‘የይሖዋ በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም’ የሚለው በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ሐሳብ እውነት መሆኑን በራስህ ተሞክሮ ማረጋገጥ ትችላለህ።—ምሳሌ 10:22
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ራስህን እወቅ
ሌላ አገር ሄደህ ማገልገል ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ በሚከተሉት ጥያቄዎች አማካኝነት ራስህን በሐቀኝነት መርምር፤ እንዲሁም ጉዳዩን በጸሎት አስብበት። ከዚህ ቀደም የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ይችላሉ።
• መንፈሳዊ ሰው ነኝ?—“ደስታ ለማግኘት ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች” (ጥቅምት 15, 1997 ገጽ 6)
• ውጤታማ አገልጋይ ነኝ?—“በአቅኚነት አገልግሎት ስኬታማ መሆን የሚቻልበት መንገድ” (ግንቦት 15, 1989 ገጽ 21 [እንግሊዝኛ])
• ከቤተሰቤና ከጓደኞቼ ርቄ መኖር እችላለሁ?—“አምላክን ስታገለግል የሚያጋጥምህን ናፍቆት ታግሎ ማሸነፍ” (ግንቦት 15, 1994 ገጽ 28)
• ሌላ ቋንቋ መማር እችላለሁ?—“በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል” (መጋቢት 15, 2006 ገጽ 17)
• ወደ ሌላ አገር ሄዶ ለማገልገል የሚያስችል የገንዘብ አቅም አለኝ?—“በባዕድ አገር ማገልገል ትችላለህን?” (ጥቅምት 15, 1999 ገጽ 23)
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የትሕትና መንፈስና የፈቃደኝነት ዝንባሌ በአካባቢው ወንድሞች ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውጤታማ የሚሆኑት ሌሎች እንዲያገለግሏቸው ሳይሆን ለማገልገል የሚመጡ ወንድሞች ናቸው