“አምላካዊ ፍርሃት” በተባለው የወረዳ ስብሰባ ላይ ተገኝ!
“አምላካዊ ፍርሃት” በተባለው የ1994 የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከአሁኑ ዕቅድ አውጥተሃልን? ሦስቱንም ቀን በስብሰባው ላይ ብትገኝ በርግጥ ትጠቀማለህ! በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ እንኳን 165 ስብሰባዎች ለማድረግ ታቅዷል። አንተ በምትኖርበት አቅራቢያም አንድ ስብሰባ ይደረጋል።
አንዳንዱ ፍርሃት ወኔን የሚሰልብና ተስፋን የሚያጨልም ሊሆን ይችላል። ዓርብ ጠዋት የሚቀርበው የስብሰባውን መልእክት የሚገልጸው ንግግር አምላካዊ ፍርሃት ትርጉሙ ምን እንደሆነ ያብራራል፤ እንዲሁም የሚያስገኛቸውን በርካታ ጥቅሞች ይዘረዝራል። የስብሰባው ጠቅላላ ፕሮግራም እነዚህን ጥቅሞች የሚያጎላ ነው።
ዓርብ ከሰዓት በኋላ አምላካዊ ፍርሃት ትዳርንና የቤተሰብን ኑሮ እንዴት ሊያጠናክር እንደሚችል፣ እንዲሁም ወጣቶች ከአምላክ ጎን እንዴት በታማኝነት ጸንተው መቆማቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ሲብራራ ትሰማለህ። የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም “ለሟች ቤተሰቦች የሚሆን ማጽናኛ” የሚል ርዕስ ባለው አስደሳች ንግግር ይደመደማል። የሚወዱትን ሰው በሞት የተነጠቁ ሰዎችን ለመርዳት በንግግሩ ላይ የሚቀርቡትን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች ስትሰማ ትደሰታለህ።
የቅዳሜው ፕሮግራም አምላካዊ ፍርሃት ይሖዋ ጉባኤንና አገልግሎታችንን አስመልክቶ የሚሰጠንን መመሪያዎች ተከትለን እንድንኖር እንዴት እንደሚያጠነክረን ይገልጻል። በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ “የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብቡ” ከተሰኘው ንግግር መጽሐፍ ቅዱስን ስለ ማንበብና ስለ ማጥናት ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች ያገኛሉ። የቅዳሜው ፕሮግራም “አስፈሪው የይሖዋ ቀን ቀርቧል” በሚል ስሜት ቀስቃሽ ንግግር ያበቃል።
በእሁዱ ፕሮግራም ላይ ጎላ ብለው ከሚታዩት ክፍሎች አንዱ “የጻድቃን ትንሣኤ ይኖራል” የሚለው ንግግር ነው። ከርሱ በማስከተል በሚቀርበው “ታላቁን መከራ በሕይወት ማለፍ” የተባለ ንግግር ኢየሱስ ለዘላለም አይሞቱም የሚል አስደናቂ ተስፋ የሰጣቸውን ሰዎች አስመልክቶ ማብራሪያ ይቀርባል።—ዮሐንስ 11:26
የእሁድ ጠዋቱ ፕሮግራም በፊታችሁ የተደቀኑ አማራጮች የሚል ርዕስ ባለው 40 ደቂቃ በሚፈጅ አእምሮን የሚያመራምር ድራማ ይደመደማል። ድራማው አድማጮችን ወደ ኢያሱ ዘመን ይመልሳቸውና ኢያሱ ይሖዋን ለማገልገል የነበረውን ቁርጥ አቋም ያሳያቸዋል። በኤልያስ ዘመን የነበረውን ከባድ ፈተና በድራማው ውስጥ ይቀርባል። ተሰብሳቢዎቹ በዛሬው ጊዜ አምላካዊ ፍርሃትን እንዲያሳዩ ከሚረዷቸው ከሁለቱም ሁኔታዎች ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ። “በአሁኑ ጊዜ እውነተኛውን አምላክ መፍራት ለምን ያስፈልጋል?” የሚል ርዕስ ያለው ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የሕዝብ ንግግር የስብሰባው የጐላ ክፍል ይሆናል።
በስብሰባው ላይ ለመገኘት ከአሁኑ እቅድ አውጣ። አንተ በምትኖርበት አካባቢ ስብሰባው የሚደረግበትን ቦታ ለማወቅ በአካባቢህ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ጠይቅ፤ አለዚያም ለዚህ መጽሔት አሳታሚዎች ደብዳቤ ጻፍ። የሰኔ 8 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳ፣ በብሪታንያና በአየርላንድ ስብሰባው የሚደረግባቸውን ቦታዎች በሙሉ ይዘረዝራል።
[ምንጭ]
T. Rosenthal/SUPERSTOCK