ስለ ሃይማኖት ከመወያየት ምን ጥቅም ሊገኝ ይችላል?
ወላጆች ልጃቸው የሚናገራቸውን የመጀመሪያ ቃላት ለመስማት በጉጉት ይጠባበቃሉ። እየተንተባተበ “ማማ” ወይም “ባባ” እያለ በተደጋጋሚ ሲጣራ ሲሰሙ ልባቸው በደስታ ይሞላል። በፍጥነት ይህንን ዜና ለወዳጆቻቸውና ለጎረቤቶቻቸው ይናገራሉ። በእርግጥም የሕፃን የመጀመሪያ ንግግር የሚያስደስት ምሥራች ነው።
ሕፃኑ ልጅ ለሚሰማቸው ድምፆች፣ ለሚ መለከታቸው ነገሮችና ፈገግታዎች ምላሽ ይሰጣል። እርግጥ የሚያሳያቸው ስሜቶች ይለያያሉ። ይሁን እንጂ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ልጁ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ካላሳየ ወላጆች የልጁ እድገት ተገትቷል ብለው መጨነቃቸው ተገቢ ነው።
ሕፃናት ስሜታቸውን ይበልጥ የሚገልጹት በደንብ ለሚያውቋቸው ሰዎች ነው። እናትየዋ ሕፃኑን እቅፍ ስታደርገው ብዙውን ጊዜ ሕፃኑ ፈገግታ ያሳያል። ሆኖም የማያውቀው ዘመድ ልቀፍህ ቢለው ሊያለቅስ እንዲያውም በእልህ አትንካኝ ሊል ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥማቸው አብዛኞቹ ዘመዶች ተስፋ አይቆርጡም። ልጁ ይበልጥ ባወቃቸው መጠን እነሱንና ሕፃኑን እንደ አጥር ይለያያቸው የነበረው አለመተዋዋቅ ሲወገድ ይደሰታሉ፤ ቀስ በቀስ የልጁ ፈገግታ ይታያል።
በተመሳሳይም ብዙ ሰዎች በደንብ ከማ ይተዋወቁት ሰው ጋር ስለ ሃይማኖት ለመወያየት ያመነታሉ። ይህ የማያውቁት ሰው የግል ጉዳይ ስለ ሆነው ስለ ሃይማኖት ለመነጋገር ለምን እንደፈለገ አይረዱ ይሆናል። በዚህ ምክንያት በእነሱና ስለ ፈጣሪ ሊነግሯቸው በመጡ ሰዎች መካከል አንድ የሚለያይ አጥር እንዲኖር ይፈቅዳሉ። ሰዎች በተፈጥሯቸው ስላላቸው የአምልኮ ፍላጎት እንኳ ለመወያየት ፈቃደኛ አይሆኑም።
በእርግጥ ስለ ፈጣሪያችን ለመማር ፍላጎት ሊኖረን ይገባል፤ ከሌሎች ሰዎች ጋር መነጋገራችን ይህን ትምህርት እንድናገኝ መንገድ ሊከፍትልን ይችላል። አምላክ ከረጅም ጊዜ በፊት ከሰዎች ጋር ያለውን የሐሳብ ግንኙነት ክፍት ስላደረገ ስለ እሱ መማር እንችላለን። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
‘አዳምጥና ተማር’
አምላክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሐሳብ ግንኙነት ያደረገው ከአዳም ጋር ሲሆን ቦታውም ዔደን ገነት ነበር። ሆኖም አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ አምላክ እንደገና ሊያነጋግራቸው ፈልጎ ሲጠራቸው መሸሸግን መረጡ። (ዘፍጥረት 3:8–13) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ ፈቃደኛ የነበሩ የብዙ ወንዶችና ሴቶችን ዝርዝር ታሪክ ይዟል።
አምላክ በዘመኑ በነበረው ክፉ ዓለም ላይ ስለሚመጣው ጥፋት ለኖኅ ነግሮታል፤ በዚህ ምክንያት ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ሆነ። (2 ጴጥሮስ 2:5 አዓት) ኖኅ በዘመኑ ለነበረው ትውልድ የአምላክ ቃል አቀባይ እንደ መሆኑ መጠን አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በሚያደርጋቸው ግንኙነቶች ማመኑን በተግባር ከማሳየቱም በላይ ከአምላክ ጎን የቆመ መሆኑን በይፋ አሳውቋል። ሰዎች ለኖኅ ስብከት የሰጡት ምላሽ ምን ነበር? በዘመኑ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ‘የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን ጠራርጎ እስከ ወሰደ ድረስ አለማስተዋላቸው’ ያሳዝናል። (ማቴዎስ 24:37–39) ይሁን እንጂ የኖኅ ቤተሰብ የሆኑት ሰባት ሰዎች በማዳመጣቸው፣ የአምላክን መመሪያዎች በመከተላቸውና ከዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ በመትረፋቸው ደስ ይለናል። አሁን ያሉት ሰዎች ሁሉ የእነሱ ዘሮች ናቸው።
ከዚያ በኋላ አምላክ ከጥንት እስራኤል ጋር በብሔር ደረጃ የሐሳብ ግንኙነት አደረገ። አምላክ በሙሴ አማካኝነት አሥሩን ትእዛዛትና ሌሎች እኩል ተፈጻሚነት ያላቸው 600 ሕጎችን ሰጣቸው። ይሖዋ ሁሉንም ሕጎች እንዲያከብሩ እስራኤላውያንን ይጠብቅባቸው ነበር። ሙሴ በየሰባት ዓመቱ በዓመታዊው የዳስ በዓል ወቅት የአምላክ ሕግ እንዲነበብ መመሪያ አስተላልፎ ነበር። “ሕዝቡን ወንዶችና ሴቶችን ሕፃናቶችንም በአገራችሁ ደጅ ያለውን መጻተኛ ሰብስብ” ሲል አዘዘ። ለምን? “ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፣ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፣ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ።” ሁሉም ማዳመጥ እና መማር ነበረባቸው። የሰሙትን ሲወያዩ ያገኙት የነበረውን ደስታ እስቲ ገምት!—ዘዳግም 31:10–12
ከአምስት መቶ ዘመናት በላይ ካለፈ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ መሳፍንትንና ሌዋውያንን የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ እንደገና ለማቋቋም ለሚደረገው ዘመቻ አደራጃቸው። እነዚህ ሰዎች ሕዝቡን የይሖዋን ሕጎች እያስተማሩ በይሁዳ ከተማዎች ሁሉ ዞሩ። ንጉሡ እነዚህን ሕጎች ሕዝቡ እንዲወያይባቸው በማድረጉ ለንጹሕ አምልኮ ያለውን ቆራጥ አቋም አሳይቷል። የእሱ ተገዢዎች እንደመሆናቸው መጠን መማርና ማዳመጥ ነበረባቸው።—2 ዜና መዋዕል 17:1–6, 9
በውይይት መመሥከር
አምላክ የራሱ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን ቃል አቀባዩ አድርጎ ወደ ምድር ልኮት ነበር። (ዮሐንስ 1:14) ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በፊታቸው በተአምር ሲለወጥ ስለ ተመለከቱ አምላክ ራሱ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል ሰምተዋል። (ማቴዎስ 17:5) እነሱም በፈቃደኝነት ይህን ትእዛዝ ፈጽመዋል።
በተመሳሳይም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስለ አምላክ ዓላማዎች ለሌሎች እንዲናገሩ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሊፈጽም ስድስት ወራት ገደማ ሲቀረው መንግሥተ ሰማያትን የመስበኩ ሥራ በጣም ሰፊ ስለሆነ ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት እንደሚያስፈልጉ ገልጿል። 70ዎቹን ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ስለ አምላክ መንግሥት እንዴት መወያየት እንደሚችሉ ካስተማራቸው በኋላ መልእክቱን ለሕዝብ እንዲነግሩ ላካቸው። (ሉቃስ 10:1, 2, 9) ኢየሱስ በሰማይ ወዳለው አባቱ ከመመለሱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ይህን መልእክት ለሌሎች እንዲናገሩ አበረታታቸውና “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድረጓቸው” ሲል አዘዛቸው። (ማቴዎስ 28:19, 20) በአሁኑ ወቅት እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም በሙሉ ከሰዎች ጋር ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በመወያየት ይህን ተልእኮ እየፈጸሙ ነው። እነዚህ ውይይቶች ፈጣሪ ስለ ሆነው ይሖዋ የሚናገረውን እውነት ለሰዎች ለመመሥከር ያስችሏቸዋል።—ማቴዎስ 24:14
ሰላማዊና የሚያንጹ ውይይቶች
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ እምነታቸው ከሰዎች ጋር የሚወያዩት እንዴት ነበር? ተቃዋሚዎችን አያስቆጡም፤ ከእነሱም ጋር አይከራከሩም። ከዚህ ይልቅ ምሥራቹን የሚቀበሉትን ለማግኘት ይጥራሉ፤ ከዚያም መልእክታቸውን የሚደግፍ ቅዱስ ጽሑፋዊ መረጃ ያቀርባሉ። እርግጥ አምላክ ከልጁ ደቀ መዛሙርት ጋር የሚገናኙ ሰዎች የሚያሳዩትን ስሜት ይመለከት ነበር፤ እንዲያውም ኢየሱስ “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፣ እኔን የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” ብሏል። (ማቴዎስ 10:40) በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች መልእክቱን አለመቀበላቸው አምላክን ምንኛ እንዳቃለሉት ያሳይ ነበር!
ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “የጌታም ባሪያ . . . ሊጣላ አይገባውም” ሲል ምክር ሰጥቷል። ከዚህ ይልቅ “ለሰው ሁሉ ገር ለማስተማርም የሚበቃ ለትዕግሥትም የሚጸና [ይሁን።] . . . ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና . . . የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ” አለ። (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25) ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን በግሪክ ለሚገኙ የአቴና ሰዎች ያቀረበበት ዘዴ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ከአይሁዶች ጋር በምኩራባቸው ውስጥ ተወያይቷል። በገበያ “ከሚያገኛቸው ጋር” በየቀኑ ይነጋገር ነበር። አንዳንዶች አዲስ ነገር ብቻ መስማት ይወዱ የነበረ ቢሆንም ጳውሎስ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ በደግነት አነጋግሯቸዋል። ንስሐ እንዲገቡ የሚጠይቅባቸውን የአምላክን መልእክት ከአድማጮቹ ጋር ተወያይቷል። የሰጡት ምላሽ በዘመናችን ያሉ ሰዎች ከሚያሳዩት ምላሽ ጋር በብዙ መንገድ ይመሳሰላል። “እኩሌቶቹ አፌዙበት፣ እኩሌቶቹ ግን፦ ስለዚህ ነገር ሁለተኛ እንሰማሃለን አሉት።” ጳውሎስ ውይይቱን ለማራዘም አልሞከረም። መልእክቱን ከሰበከላቸው በኋላ “ከመካከላቸው ወጣ።”—ሥራ 17:16–34
ጳውሎስ ቆየት ብሎ በኤፌሶን ለሚገኙት የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ‘የሚጠቅማችሁን ነገር ሁሉ ከመንገር ወይም ሕዝብ ባለበትና ከቤት ወደ ቤት እየሄድሁ እናንተን ከማስተማር ወደኋላ አላልሁም’ ብሏቸው ነበር። ከዚህም በላይ ‘ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች መሥክሯል።’—ሥራ 20:20, 21 አዓት
እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ይኖሩ የነበሩ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከሰዎች ጋር ስለ ሃይማኖት እንዴት ይወያዩ እንደነበር ያሳያሉ። ስለዚህ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች በታዛዥነት ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስለ ሃይማኖት ይወያያሉ።
ብዙ ጥቅም የሚያስገኙ ውይይቶች
‘የእግዚአብሔርን ቃል ስማ።’ ‘ትእዛዛቱን ጠብቅ።’ እንደነዚህ ያሉ ምክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንኛ በተደጋጋሚ ተጠቅሰዋል! የይሖዋ ምሥክሮች በሚቀጥለው ጊዜ ሲያነጋግሩህ ለእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎች ምላሽ ለመስጠት ትችላለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን መልእክታቸውን አድምጥ። ይህ መልእክት ፖለቲካዊ መልእክት ሳይሆን የአምላክ ሰማያዊ መስተዳድር ለሆነው ለመንግሥቱ ድጋፍ የሚሰጥ መልእክት ነው። አምላክ በዘመናችን ያሉትን ግጭቶች የሚያስወግድበት መሣሪያ ይህ መንግሥት ነው። (ዳንኤል 2:44) ከዚያ በኋላ ይህ በሰማይ ሆኖ የሚገዛው የአምላክ መንግሥት ጠቅላላዋ ምድር የዔደንን የአትክልት ቦታ ወደምትመስል ገነት እንድትለወጥ ዝግጅት ያደርጋል።
ቀደም ሲል መርማሪ ፖሊስ የነበረ አንድ ግለሰብ ብዙውን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነጋግሩት አይቀበላቸውም ነበር። ይሁን እንጂ የሚመረምራቸው ወንጀሎች እየጨመሩ ሲመጡ ሕይወት ግራ እያጋባው መጣ። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መመርመር እንደሚፈልግ ቀጥሎ ለመጣው ምሥክር ነገረው። ቋሚ ውይይት ተጀመረ። ፖሊሱ ብዙውን ጊዜ መኖሪያውን ቢቀያይርም ምሥክሮቹ ውይይቱን ለመቀጠል ሲሉ በሄደባቸው አዲስ ቦታዎች ሁሉ እሱን በደስታ መፈለጋቸውን አላቋረጡም ነበር። መጨረሻ ላይ ይህ ባለ ሥልጣን እንዲህ አለ፦ “እፈልገው የነበረው መረጃ ሁሉ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይገኝ ነበር። እነዚያ ምሥክሮች ከእኔ ጋር በትዕግሥት መነጋገራቸውን ባይቀጥሉ ኖሮ አሁንም ቢሆን በዓለም ውስጥ እየተቅበዘበዝኩ የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት እጥር ነበር። እውነትን ስላወቅሁ ቀሪ ሕይወቴን በሙሉ እንደ እኔ አምላክን የሚፈልጉትን ለማግኘት እጥራለሁ።”
ፍላጎት ያላቸው አድማጮች ይበልጥ ለማወቅ ይሻሉ። ለሚቀርቡላቸው እምነቶች ማስረጃ እንዲቀርብላቸው መጠበቃቸው ተገቢ ነው። (1 ጴጥሮስ 3:15) አንድ ትንሽ ልጅ ወላጆቹን ብዙ ጥያቄዎችን ጠይቆ መልስ እንዲሰጡት እንደሚጠብቅባቸው ሁሉ ምሥክሮቹ አጥጋቢ መልሶችን እንዲሰጡህ መጠበቅህ ትክክል ነው። እንደገና መጥተው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክታቸውን ቢያወያዩህ እንደሚደሰቱ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ።
ምናልባት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመጠኑ ታውቅ ይሆናል። አምላክ ከአንተ የሚጠብቀው በአኗኗርህ ላይ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግን እንደሚጨምር ተገንዝበህ ይሆናል። የአምላክ ብቃቶች ከመጠን በላይ የሆኑ ብዙ መሥዋዕትነቶችን ይጠይቁብኛል ብለህ በመፍራት የጀመርከውን ለመቀጠል አታመንታ። ትእዛዞቹ እውነተኛ ደስታ ያስገኙልሃል። በየጊዜው አንድ እርምጃ ወደፊት በገፋህ መጠን ይህ እውነት መሆኑን ትገነዘባለህ።
በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ ማን እንደሆነ፣ ከአንተ ምን እንደሚፈልግብህና ለአንተ ምን እንደሚያደርግልህ መርምር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እንዲያሳዩህ ምሥክሮቹን ጠይቃቸው። የሚሉት እውነት መሆኑን በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቃቄ በመመርመር አረጋግጥ። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ሃይማኖት የሚያቀርቡልህ እውነት ምክንያታዊ እንደሆነ ስትረዳ ከቅዱሳን ጽሑፎች ሊያካፍሉህ የሚችሉትን ብዙ መልካም ነገሮች በጥንቃቄ ለመመርመር እንደምትጓጓ አያጠራጥርም።—ምሳሌ 27:17
በአካባቢያቸው በሚገኘው የስብሰባ ቦታቸው ማለትም በመንግሥት አዳራሻቸው ተገኝተህ የይሖዋ ምሥክሮችን እንድትመለከታቸው ተጋብዘሃል። እዚያም ስለ አምላክ ቃል የሚያደርጓቸውን ጠቃሚ ውይይቶች ታዳምጣለህ። በስብሰባው ላይ የተገኙት እርስ በርሳቸው ስለ አምላክ ዓላማዎች የሚያደርጉትን ውይይት ትመለከታለህ። የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ በአሁኑ ጊዜ ለእኛ ያለውን ፈቃድ እንድትማር እንዲረዱህ ፈቃደኛ ሁን። አምላክ ስለ እውነተኛው አምልኮ እንድትወያይ የሚያቀርብልህን ጥሪ ተቀብለህ ሞገሱን ብሎም በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ትችላለህ።—ሚልክያስ 3:16፤ ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኖኅ ስለ አምላክ ዓላማ በግልጽ ተናግሯል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጳውሎስ በጥንቷ አቴና ውስጥ እንዳደረገው ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች ያስተምራሉ