“ደስተኛ አወዳሾች” የአውራጃ ስብሰባ እርስዎ በዚያ ይገኛሉን?
ደስታ! በዚህ በመከራ በተሞላ ጊዜ ውስጥ ይህ ቃል እንግዳ፣ እንዲያውም ባዕድ አይመስልምን? ጋዜጦች የሚያስደስቱ ብዙ ነገሮችን እንደማያቀርቡልን እሙን ነው። የጎሣ ግጭት፣ በየቦታው ተስፋፍቶ ያለ ረሃብ፣ ሥራ አጥነት፣ አደገኛ የሆነ የአካባቢ ብክለት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ወንጀል የመሳሰሉ ነገሮች ልብን በደስታ የሚያሞቁ ነገሮች አይደሉም፤ ናቸው እንዴ?
ዛሬ አብዛኞቹ ሰዎች ከሕይወት ማግኘት የሚችሉትን ማንኛውንም ዓይነት ተድላ ለማግኘት ይፍጨረጨራሉ። ነገር ግን ደስታ አግኝተዋልን? ደስታ ማለት “ሐሴት ማድረግ፤ ፈንጠዝያ” እንደሆነ ተገልጿል። ብዙዎች እንዲህ ዓይነቱን ደስታ አላገኙም፤ ቢያገኙም ሁሌ ጊዜያዊ ነው።
ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ወዳለንበት ጊዜ አሻግሮ በመመልከት ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል። እነሆ፣ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ’ በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 65:13, 14) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
መልሱን ለማግኘት በ1995 ከሚደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባዎች መካከል በአንዱ ላይ እንዲገኙ እንጋብዝዎታለን። የስብሰባው ርዕስ “ደስተኛ አወዳሾች” የሚል ሲሆን በስብሰባው ላይ ለመገኘት ምንም ክፍያ አይጠየቅም። የሦስት ቀኑ የአውራጃ ስብሰባ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችን፣ ትዕይንቶችን፣ በውይይት መልክ የሚቀርቡ ትምህርቶችንና ሌሎች ዝግጅቶችን ያካትታል። ፕሮግራሙ ተጀምሮ እስኪያበቃ ድረስ የስብሰባው ዋና መልእክት የሆነው ደስታ አጽንኦት ይሰጥበታል።
ስብሰባዎቹ ሰኔ ወር ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ይጀምሩና እስከ 1996 መባቻ ድረስ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ከተሞች ይቀጥላሉ። ከእነዚህ ስብሰባዎች መካከል አንዱ እርስዎ በሚኖሩበት አቅራቢያ እንደሚደረግ የታወቀ ነው። ለምን በአካባቢዎ የሚኖሩትን የይሖዋ ምሥክሮች አይጠይቁም? በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልዎታለን።