“አምላካዊ ፍርሃት” በተባለው የወረዳ ስብሰባ ላይ እንድትገኙ ተጋብዛችኋል!
አዎን፣ በ1994 የሚደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ በጣም ቀርቧል። ከሰኔ 1994 ጀምሮ እስከ ጥር 1995 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከናወነው የሦስት ቀን ስብሰባ ፕሮግራም በዓለም ዙሪያ በመጀመሪያ በሰሜን አሜሪካ ከዚያ በምሥራቅና በምዕራብ አውሮፓ፣ በእስያ፣ በመካከለኛውና በደቡብ አሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያና በባሕር በሚገኙ ደሴቶች በመቶዎች በሚቆጠሩ ከተሞች ውስጥ ይደመጣል።
“አምላካዊ ፍርሃት”፤ እንዴት ያለ ስሜት ቀስቃሽ መልእክት ነው! ይህ አንድ ሰው ሕይወቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ የሚሰማው ዓይነት የመርበድበድ ፍርሃት ሳይሆን የአእምሮ ሰላምና ደስታ የሚያመጣ አምላካዊ ፍርሃት ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዲህ ይላል፦ “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው።” (ምሳሌ 22:4) አምላክን መፍራት “ባለጠግነት ክብር ሕይወትም” ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ንግግሮች፣ ቃለ ምልልሶች፣ ትዕይንቶችና ድራማ በሚቀርቡባቸው ሦስት የስብሰባ ቀናት የስብሰባው ዋና መልእክት ሲብራራ ይህ ጥያቄ መልስ ያገኛል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በአንድ ላይ መሰብሰባችንን መተው’ እንደሌለብን ጽፏል። (ዕብራውያን 10:25) የይሖዋ ምሥክሮች ለጉባኤ ጥናትና ለአምልኮ በሳምንት ሦስት ጊዜ መሰብሰባቸውን በጣም አስፈላጊ ነገር አድርገው ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ ዓመታዊው የወረዳ ስብሰባ ልዩ ነው። ይህ ስብሰባ በትልቅ ጉጉት የሚጠበቅና ካለፈም በኋላ ቢሆን ለወራት የሚወራለት ነው። በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ቢሆኑ በስብሰባው ተገኝተው እዚያ ባለው የሞቀ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነትና በጣም አስፈላጊ በሆነ መንፈሳዊ እውቀት እንዲደሰቱ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልዎታለን። በአካባቢዎ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አባላት አንዱን ቢጠይቁ ስብሰባው በአቅራቢያዎ የሚደረግበትን ቦታና ጊዜ ሊነግርዎት ደስተኛ ነው።