ነፍስ ለዘላለም ሕያው ሆና ትኖራለች?
የሟቹ ቤተሰቦችና ጓደኞች ክፍት በሆነው የሬሳ ሣጥን አጠገብ ጸጥ ብለው ያልፋሉ። የ17 ዓመቱን ልጅ አስከሬን ትኩር ብለው ይመለከታሉ። የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ማንነቱን መለየት አልቻሉም። ይወስደው ከነበረው መድኃኒት የተነሳ ጸጉሩ ከማለቁም በተጨማሪ ይዞት የነበረው የካንሰር በሽታ ሰውነቱን አመንምኖታል። ይህ በእርግጥ የእነሱ ጓደኛ ሊሆን ይችላልን? ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሚያስብ፣ በአእምሮው ጥያቄዎች የሚመላለሱና ኃይል ያለው በሌላ አባባል ሕያው ልጅ ነበር! የልጁ እናት እያለቀሰች “ይህን ጊዜ ቶሚ ደስ ብሎታል። አምላክ ቶሚን ከእርሱ ጋር በሰማይ እንዲሆን ስለፈለገ ወስዶታል” በማለት ደጋግማ ትናገራለች።
ይህች በሐዘን የተዋጠች እናት ልጅዋ አሁንም በሆነ መንገድ በሕይወት እንደሚኖር ማሰብዋ መጠነኛ ተስፋና ማጽናኛ አስገኝቶላታል። ነፍስ የማትሞትና የአንድ ሰው ባሕርይ፣ ሐሳብ፣ ትዝታ መቀመጫ ወይም በሌላ አነጋገር የአንድ ሰው “ማንነት” መሆኗን በቤተ ክርስቲያን ተምራለች። ይህች እናት ነፍስ ማለት አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ከአምላክና ከመላእክት ጋር በሰማይ ለመኖር ከሰውዬው ወጥታ የምትሄድ ሕያው መንፈሳዊ አካል እንደሆነች አድርጋ ስለምታስብ ልጅዋ ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጪ እንዳልሆነ እምነት ነበራት።
አሳዛኝ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሰው ልብ ባገኘው ነገር ላይ ተስፋ ስለሚያደርግ ይህ እምነት ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ለምን እንደሆነ ማወቅ አያስቸግርም። ለምሳሌ የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ጄ ፓተርሰን ስሚዝ ዘ ጎስፕል ኦቭ ዘ ሂርአፍተር በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደተናገሩ ተመልከት፦ “ሞት ከበስተኋላው ከሚኖረው ሁኔታ ማለትም በእርሱ ተሸጋግረን ከምናገኘው እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነ ዓለም ጋር ሲወዳደር ኢምንት ነገር ነው።”
በዓለም ዙሪያ የተለያየ ሃይማኖትና ባህል ያላቸው ሰዎች ሰው የማትሞት ነፍስ ይኸውም አካሉ ከሞተ በኋላ ሕያው ሆኖ የሚቀጥል መንፈስ አለው ብለው ያምናሉ። በሺህ የሚቆጠሩት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶችና ኑፋቄዎች በሙሉ በዚህ ያምናሉ ለማለት ይቻላል። በአይሁድ እምነትም ቢሆን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትምህርት ነው። ሂንዱዎች ነፍስ ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበረች ነገር ስትሆን አንድ ሰው ሲወለድ በአካሉ ውስጥ ትታሰርና ሲሞት በማያቋርጠው የሪኢንካርኔሽን ዑደት አማካኝነት ወደ ሌላ አካል ትዘዋወራለች በማለት ያምናሉ። ሙስሊሞች ደግሞ ነፍስ ሕልውና የምታገኘው አንድ ሰው ሲወለድ እንደሆነና አካሉ ሲሞት ነፍሱ በሕይወት እንደምትቀጥል ያምናሉ። በሙታን መናፍስት እንደሚያምኑት አፍሪካውያን፣ እንደ ሺንቶም ሆነ ቡድሂስት የመሳሰሉ ሌሎች እምነቶች ዓይነቱ ይለያይ እንጂ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል መሠረታዊ ሐሳብ ያለው ትምህርት ያስተምራሉ።
አንዳንድ አሳሳቢ ጥያቄዎች
ነፍስ አትሞትም የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ተቀባይነት ያገኘና በዓለም ዙሪያ የተስፋፋ ቢሆንም አንዳንድ አሳሳቢ ጥያቄዎች ያስነሳል። ለምሳሌ ያህል ሰዎች በሞት የተለያቸው ግለሰብ በሕይወት ሳለ ጥሩ ሰው ካልነበረ ነፍሱ የት ገብታ ይሆን እያሉ ያስባሉ። ዝቅተኛ ፍጡር ሆኖ እንደገና ይወለድ ይሆን? ወይስ ወደ ሰማይ ለመሄድ ብቁ መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ በእሳት ወደሚነጻበት መንጽሔ ተልኮ ይሆን? ከዚህ የባሰ ደግሞ በሲኦል እሳት ውስጥ ለዘላለም እየተቀጣ ይሆን? ወይስ ብዙዎቹ በሙታን መናፍስት የሚያምኑ ሰዎች እንደሚያስተምሩት ፍላጎቱ ካልተሟላለት የሚተናኮል መንፈስ ሆኗል?
እንደዚህ ያሉት አመለካከቶች በሕይወት ያሉትን ሰዎች በጣም የሚያስጨንቁ ናቸው። በሞት የተለዩን ወዳጅ ዘመዶቻችን ለምን ይህ አልተደረገልንም ብለው መጥፎ ነገር እንዳያደርሱብን የእነሱን መንፈስ መለማመን አለብንን? በጣም አሠቃቂ ከሆነው መንጽሔ እንዲወጡ መርዳት ይጠበቅብናል? ወይስ ሲኦል ውስጥ እየተሠቃዩ እንደሆነ በማሰብ እርባና በሌለው ፍርሃት መንቀጥቀጥ አለብንን? ወይስ አንዳንድ ሕያዋን እንስሳት የሞቱ ሰዎችን ነፍሳት ይዘዋል ብለን በማሰብ ልዩ ጥንቃቄ ልናደርግላቸው ይገባል?
ራሱን አምላክን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችም ቢሆኑ እረፍት የሚነሱ ናቸው። ለምሳሌ በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችውን እናት የመሰሉ ብዙ ወላጆች አምላክ በሰማይ ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ የልጆቻችንን የማይሞት ነፍስ “ወስዷል” የሚለው አመለካከት መጀመሪያ ላይ ያጽናናቸዋል። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች ብዙም ሳይቆዩ አምላክ ልጁን ወደ ሰማይ ለመውሰድ ስለፈለገ ብቻ ያለ ጥፋቱ በመጥፎ በሽታ እንዲሠቃይ አድርጎ እንደ ብርቅ የሚታየውን ልጅ ባሰኘው ጊዜ በሞት በመቅጠፍ ወላጆቹን ሐዘን ውስጥ የሚከታቸው ምን ዓይነት አምላክ ቢሆን ነው እያሉ ማሰብ ይጀምራሉ። ታዲያ አምላክ እንዲህ ከሆነ ፍትሑ፣ ፍቅሩና ምሕረቱ ምኑ ላይ ነው? እንዲያውም አንዳንዶች እንደዚህ ዓይነቱ አምላክ ጥበበኛ መሆኑ አጠያያቂ ሆኖባቸዋል። አምላክ ጥበበኛ ቢሆን ኖሮ ሁሉም ነፍሳት ወደ ሰማይ መሄዳቸው የማይቀር ሆኖ ሳለ እነዚህን ሁሉ ነፍሳት መጀመሪያውኑ ምድር ላይ እንዲኖሩ ያደርግ ነበርን? ሁሉም ነፍሳት ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ማለት ምድር የተፈጠረችው በከንቱ ነው ማለት አይሆንምን? በማለት ይጠይቃሉ።—ከዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 103:8፤ ኢሳይያስ 45:18፤ 1 ዮሐንስ 4:8 ጋር አወዳድር።
ስለዚህ የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በማንኛውም ዓይነት መልኩ ቢቀርብ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች ከማስከተሉም በላይ አንድ ወጥ አይደለም። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው? ይህ ትምህርት ያሉበት አብዛኞቹ ችግሮች ከትምህርቱ ምንጭ ጋር የተያያዙ ናቸው። በእነዚህ የትምህርቱ ምንጮች ላይ አጠር ያለ ጥናት ስታደርግ እውቀት የሚጨምር ሆኖ ታገኘዋለህ፤ በተጨማሪ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ የሚናገረውን ማወቅህ ያስደንቅህ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት በኋላ ስለሚኖረው ሕይወት የዓለም ሃይማኖቶች ከሚያስተምሩት እጅግ የተሻለ ተስፋ ይሰጣል።