የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በትምህርት ቤት የጸና አቋም መያዝ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል
መጽሐፍ ቅዱስ “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 54:13) “ልጆችሽም ሁሉ” የሚለውን አነጋገር ሰፋ አድርገን ስናየው ትናንሽ የሆኑትን ልጆች ጨምሮ በምድር ላይ የሚገኘውን መላውን የአምላክ አገልጋዮች ጉባኤ በጠቅላላ ሊያመለክት ይችላል። ዛሬ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው በቤትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ‘ከይሖዋ የተማሩ’ እንዲሆኑ ለማድረግ ይጥራሉ።
ይሁን እንጂ ወጣት ክርስቲያኖች በትምህርት ቤት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል። ብዙውን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኙት ትምህርት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አቋም መውሰዱን አስፈላጊ ሆኖ ያገኙታል። ይህንንም በማድረጋቸው የሚገኘው ውጤት ለተማሪዎችም ሆነ ለአስተማሪዎች ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ከማይክሮኔዥያ የተገኘው የሚከተለው ተሞክሮ ያሳያል።
ከቹክ ደሴቶች አንዷ በሆነችውና በምዕራባዊው ሰላማዊ ውቅያኖስ ላይ በምትገኘው በትንሿ ደሴት በቶል ውስጥ የሚገኝ የአንድ ትምህርት ቤት አስተማሪዎች ሃሎዊን የተባለውን በዓል ትምህርት ቤቱ ስለሚያከበር ሁሉም ልጆች እንዲዘጋጁና በበዓሉ አከባበር ላይ እንዲሳተፉ ይነግሯቸዋል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ተማሪዎች የበዓሉ አከባበር ጣረሞት፣ ጭራቅና ጠንቋይ የሚያስመስሉ መኳኳያዎችንና ልብሶች መጠቀምን እንደሚጨምር አውቀዋል፤ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደግሞ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዙ ናቸው። እነዚህ ልጆች በዚህ ጉዳይ ለመሳተፍ ሕሊናቸው አልፈቀደላቸውም።a
በቤት ውስጥና በክርስቲያን ጉባኤ ባገኙት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሥልጠና የተነሣ እንደነዚህ ያሉት ነገሮች ለመዝናኛም እንኳን ተብለው ቢደረጉ አምላክን እንደማያስደስቱት አውቀዋል። ልጆቹ አቋማቸውን ይበልጥ ግልጽ አድርጎ ለአስተማሪዎቻቸው እንዲያስረዳላቸው በደሴቲቱ በሚስዮናዊነት የሚያገለግለውን ባራክ የተባለ የይሖዋ ምሥክር ጋበዙት።
አስተማሪዎቹ ማብራሪያውን ከሰሙ በኋላ ባራክ ለትምህርት ቤቱ ሠራተኞች በጠቅላላ ገለጻ መስጠት ይችል ዘንድ ሁለተኛ ስብሰባ እንዲካሄድ ዝግጅት አደረጉ። ባራክ በዚህ ስብሰባ ላይ የሃሎዊንን በዓል ትክክለኛ ገጽታ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን አቀረበ። ሐሳቡን ያገኘው ከበርካታ መጠበቂያ ግንቦች እና ከሌሎችም ጽሑፎች ላይ ነበር። አስተማሪዎቹና አስተዳዳሪዎቹ የበዓሉ አከባበር ከየት እንደጀመረ፣ ታሪኩ ምን እንደሆነና ከሃይማኖት ጋር ምን ዝምድና እንዳለው ሲያውቁ ተገረሙ። ስለዚህ ጉዳይ አንድ እልባት ላይ ለመድረስ የሠራተኞች ስብሰባ እንዲጠራ ወሰኑ።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ያልተጠበቀ ውሳኔ ይፋ ሆነ። ለሃሎዊን በዓል ይደረጉ የነበሩት ዝግጅቶች በሙሉ ተሰረዙ። በዚያ ዓመት ትምህርት ቤቱ የሃሎዊንን በዓል እንደማያከብር ተነገረ። እነዚህ ወጣቶች በትምህርት ቤት ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለማድረግ በወሰዱት ቆራጥ አቋም ምክንያት የተገኘ እንዴት ያለ አስደሳች ውጤት ነው! ወጣቶች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ቁርጥ ያለ አቋም ለመውሰድ ፈጽሞ ሊፈሩ ወይም ሊያፍሩ አይገባም።
በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው ተግተው እንዲማሩ ይረዷቸዋል። በተጨማሪም ወጣት ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩና አጋጣሚውን ሲያገኙ ተስፋቸውንና እምነታቸውን ለሌሎች ተማሪዎች እንዲያካፍሉ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። የሚያገኙት ውጤት ከላይ የተጠቀሰውን ታሪክ ያህል አስደሳች ወይም ፈጣን ባይሆንም እንኳ ወጣቶች ትክክለኛ የሆነውን ነገር ማድረግ የሚያመጣውን የመተማመን መንፈስና እርካታ ሊያገኙ ይችላሉ። ከዚህ በላይ ደግሞ ሰማያዊ አባታቸው እንደሚደሰትና የታመኑ በመሆን ላሳዩት ታዛዥነት እንደሚባርካቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ ሃሎዊን በዓልና ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር የተያያዘ አመጣጥ ያለው ስለመሆኑ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የኅዳር 22, 1993 የእንግሊዝኛ ንቁ! ተመልከት።