የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የመንግሥቱን ዘር ማሰራጨት
የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ታታሪ መሆንን ያበረታታል። ንጉሥ ሰሎሞን “ወይም ይህ ወይም ያ ማናቸው እንዲበቅል ወይም ሁለቱ መልካም እንዲሆኑ አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታማ እጅህን አትተው” በማለት ተናግሯል።—መክብብ 11:6
የይሖዋ ምሥክሮች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ “ዘር” ይዘራሉ። ከ230 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች ‘ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከማስተማርና ከመስበክ ወደ ኋላ አላሉም።’ (ሥራ 5:42) የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራ ‘እጃቸውን እንዳልተዉ’ የሚከተሉት ተሞክሮዎች ያሳያሉ።
◻ በኬፕ ቨርዴ ሪፑብሊክ የምትገኝ አንዲት የይሖዋ ምሥክር በአንድ እስር ቤት አካባቢ በመስክ አገልግሎት ተሰማርታ ታገለግል ነበር። በእስር ቤቱ አጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው አንድ ዛፍ ላይ የተወሰኑ እስረኞች ተቀምጠው ነበር። ምሥክሯን ከታች ባዩዋት ጊዜ መጽሔቶች እንድትሰጣቸው ጠየቋት። ምሥክሯም በዛ ያሉ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን በአንድ ድንጋይ ላይ አሰረችና የእስር ቤቱን አጥር አሳልፋ ወረወረችላቸው። በዚህ ጊዜ ያሳዩት ፍላጎት ለ12 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርላቸው በር ከፈተ። ከእስረኞቹ መካከል ሦስቱ ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ተጠመቁ። አንዱ እስረኛ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ወይም አቅኚ ሆኖ ማገልገል ከጀመረ አሁን አንድ ዓመት አልፎታል። ታዲያ በእስር ቤቱ ውስጥ የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን የሚያከናውኑት እንዴት ነው? በመጀመሪያ እስር ቤቱ በአገልግሎት ክልሎች ተከፋፈለ። ከዚያም የአገልግሎት ክልሉ ለሦስቱ ምሥክሮች ተከፋፈለና ከአንዱ የእስረኞች ክፍል ወደ ሌላው ክፍል እየሄዱ ማገልገል ጀመሩ። እነዚህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ተመላልሶ መጠየቅ በሚያደርጉበት መንገድ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ተከታትለው ይረዳሉ። ይሁን እንጂ በእነርሱ ዘንድ ያለው አንዱ ለየት ያለ ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የሚመሩበት ብዛት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ለአንድ ሰዓት ያህል ከማጥናት ይልቅ አንዳንድ እስረኞች በየቀኑ ያጠናሉ! በተጨማሪም ምሥክሮቹ ሁሉንም የጉባኤ ስብሰባዎች በእስር ቤቱ ውስጥ ለማድረግ ከእስር ቤቱ የአስተዳደር ሹም ፈቃድ አግኝተዋል።
◻ በፖርቱጋል የምትኖር አንዲት ሴት በዛ ያሉ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ሴት አያቷ ሲሞቱ በውርስ አገኘች። እርሷ ግን የይሖዋ ምሥክር ስላልነበረች ጽሑፎቹን የማስቀመጥ ፍላጎት አልነበራትም። ሆኖም መጽሐፎቹን ለመጣልም አልፈለገችም። አንድ ቀን ከቤት ወደ ቤት እያገለገለች እቤቷ ለመጣችው የይሖዋ ምሥክር ስለ ጽሑፎቹ አነጋገረቻት። ምሥክሯም ጽሑፎቹ ያላቸውን ትክክለኛ ጠቀሜታ ታውቅ እንደሆነ ጠየቀቻት። ሴትዮዋም “እውነቱን ለመናገር ጽሑፎቹ የሚሰጡትን ትክክለኛ ጠቀሜታ አላውቅም። ግን እንዴት ላውቅ እችላለሁ?” በማለት መለሰች። ሴትዮዋም መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። ብዙም ሳይቆይ የአያቷን ጽሑፎች እንደ ውድ ሀብት አድርጋ መመልከት ጀመረች። አሁን እርሷም የተጠመቀች የይሖዋ ምሥክር ናት። ከዚህም በላይ ሴት ልጅዋና አንድ የቤተሰቧ የቅርብ ወዳጅ መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑ ናቸው። ይህ የመጻሕፍት ስብስብ እንዴት ያለ ውድ ውርሻ ሆነላት!