ኃጢአትን የምትመለከተው እንዴት ነው?
“ኃጢአት የለብህም፣ ሥቃይና ችግር የለብህም፤ ሁሉን ማድረግ የሚችል ኃይል ጎተራ ነህ።” ይህን የተናገረው ታዋቂው የሂንዱ ፈላስፋ ቪቬክናንዳ ሲሆን ይህንንም የተናገረው የሂንዱ ቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ከሆነው ባጋቫድ ጊታ ከተባለው መጽሐፍ አንድ ምንባብ በሚያብራራበት ጊዜ ነው። ከቬዳንታ በመጥቀስ “ከሁሉም የበለጠው ስህተት አንተ ደካማ ነህ፤ አንተ ኃጢአተኛ ነህ ብሎ መናገር ነው” ብሏል።a
ይሁን እንጂ ሰው ኃጢአት የለበትም የሚለው አነጋገር በእርግጥ ትክክል ነውን? ታዲያ አንድ ሰው ሲወለድ የሚወርሰው ነገር ምንድን ነው? ኒክሂላናንዳ የተባለ የሂንዱ ሃይማኖታዊ አስተማሪ “በውርስ የሚተላለፈው አካላዊ ባሕርይ ብቻ ነው” ይላል። ሌሎች ጠባዮች አንድ ሰው “ከዚህ በፊት በሕይወት በነበረበት ጊዜ በሠራቸው ሥራዎቹ” ይወሰናሉ። እንደ ቪቬካናንዳ አባባል “ዕድልህን የምትወስነው አንተው ራስህ ነህ።” ሂንዱኢዝም ኃጢአት መውረስን በሚመለከት የሚያስተምረው ምንም ነገር የለም።
በተጨማሪም ኃጢአትን የመውረስ ጽንሰ ሐሳብ በዞሮአስትርያውያን፣ በሺንቶ፣ በኮንፍዩሼስ እና በቡዲሂስት ሃይማኖተኞች ዘንድ ፈጽሞ አይታወቅም። ሌላው ቀርቶ በአይሁድና በክርስትና እምነቶች ላይ የተመሠረቱት ሃይማኖቶች እንኳ በባሕላቸው ኃጢአት የመውረስን መሠረተ ትምህርት የሚያስተምሩ ቢሆንም እነዚህን ሃይማኖቶች የሚከተሉ ሰዎች ለኃጢአት ያላቸው ዝንባሌ በመለወጥ ላይ ነው። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ኃጢአተኞች እንደሆኑ አድርገው አይቆጥሩም።
“ዘመናዊው አስተሳሰብ በሥነ ምግባር መኮነንን አያበረታታም፤ በተለይ ደግሞ ራስን በራስ መኮነንን አያበረታታም” በማለት ኮርኔልየስ ፕላንቲንግ ጁኒየር የተባሉ የሃይማኖት ምሁር ይናገራሉ። ኃጢአትን አቅልሎ በመመልከት በኩል የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትም በከፊል ተጠያቂ ናቸው። አንድ የዱክ ዩኒቨርሲቲ ቄስ “ስለ ኃጢአት መስማት የምትፈልግ ከሆነ ወደ ቤተ ክርስቲያን አትሂድ” በማለት ይናገራሉ። እንዲሁም ፕላንቲንጋ እንዳሉት ከሆነ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በአጠቃላይ ስለ ኃጢአት የሚናገሩት ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር በማገናኘት ነው።
እርግጥ ነው በአሁኑ ጊዜ በኅብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለው ወዮታ በርካታ መሆኑ አይካድም። ወንጀል፣ ጦርነት፣ የጎሳ ግጭት፣ በአደንዛዥ ዕፅ መጠቀም፣ እምነት አጉዳይነት፣ ጭቆናና በልጆች ላይ ጥቃት መፈጸም በሰፊው እየተዛመተ ነው። እንዲያውም 20ኛው መቶ ዘመን እስከ ዛሬ ድረስ የሰው ልጅ ከኖረባቸው ዘመናት ሁሉ የከፋ ደም መፋሰስ የታየበት ዘመን ተብሎ ሲጠራ ቆይቷል። በዚህም ላይ በሽታ፣ እርጅናና ሞት የሚያስከትሉትን ሕመምና ሥቃይ አክልበት። በአሁኑ ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ ካሉት ትልልቅ ችግሮች ነፃ ለመሆን የማይናፍቅ ማን አለ?
ታዲያ አንተ ለኃጢአት ያለህ አመለካከት ምንድን ነው? ኃጢአት የሚወረስ ነገር ነው? ከሕመምና ከሥቃይ የምንገላገልበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የቬዳንታ ፍልስፍና የተመሠረተው ቬዳ የተባሉት የሂንዱ ቅዱሳን መጻሕፍት የመጨረሻ ክፍል በሆኑት ዩፓኒሻድ በተባሉት መጻሕፍት ነው።