የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w05 4/1 ገጽ 4-7
  • ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ይጋጫሉ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ይጋጫሉ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቤተ ክርስቲያን የአርስቶትልን አስተሳሰብ ተቀበለች
  • ምን ትምህርት እናገኛለን?
  • እውነተኛ ሳይንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል
  • “ቢሆንም ትንቀሳቀሳለች!”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • አርስቶትል
    ንቁ!—2016
  • የጋሊልዮና የቤተ ክርስቲያን ግጭት
    ንቁ!—2003
  • ጋሊልዮ
    ንቁ!—2015
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
w05 4/1 ገጽ 4-7

ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ይጋጫሉ?

በጋሊሊዮና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል ውዝግብ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው ነገር የተጸነሰው ኮፐርኒከስና ጋሊሊዮ ከመወለዳቸው ብዙ መቶ ዘመናት አስቀድሞ ነበር። የጥንት ግሪኮች የጽንፈ ዓለም እምብርት ምድር ናት በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ያምኑ የነበረ ሲሆን ይህ ጽንሰ ሐሳብ ይበልጥ እውቅና እንዲያገኝ ያስቻሉት ደግሞ አርስቶትል የተባለ ፈላስፋ (384-322 ከክርስቶስ ልደት በፊት) እንዲሁም የስነ ፈለክ ተመራማሪና ኮከብ ቆጣሪ የነበረው ቶለሚ (በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ናቸው።a

የሒሳብ ሊቅና ፈላስፋ የነበረው የግሪካዊው ፓይታጎረስ (ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው መቶ ዘመን) አስተሳሰብ አርስቶትል ስለ ጽንፈ ዓለም በነበረው እምነት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። አርስቶትል፣ ፓይታጎረስ ስለ ክብና ሉል ያለውን አመለካከት መሠረት በማድረግ ሰማያት ልክ እንደ ቀይ ሽንኩርት አንዱ በአንዱ ላይ በተነባበሩ ሉሎች እንደተሠሩ፣ እያንዳንዱ ድርብርብ እንደ መስተዋት ባለ ነገር መሠራቱንና ምድር የንብርብሩ እምብርት እንደሆነች አድርጎ ያምን ነበር። በተጨማሪም ከዋክብት በጣም ርቆ በሚገኘው ሉል ላይ የሚቀመጠው መለኮታዊ ኃይል በሚሰጣቸው መመሪያ መሠረት ክብ ሠርተው እንደሚዞሩ እንዲሁም ፀሐይና ሌሎች የሰማይ አካላት ፍጹም እንደሆኑ፣ ምንም እንከን እንደሌለባቸውና እንደማይለወጡ እምነት ነበረው።

የአርስቶትል ንድፈ ሐሳብ የፍልስፍና ውጤት እንጂ በሳይንስ ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ምድር ትንቀሳቀሳለች የሚለው እምነት ምክንያታዊ እንዳልሆነ ይሰማው ነበር። በተጨማሪም ምድር ብትንቀሳቀስ ሰበቃ ስለሚፈጠር በቋሚነት እንድትንቀሳቀስ የሚያግዛት ኃይል ስለማይኖር መዞሯን ታቆማለች የሚል እምነት የነበረው በመሆኑ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ባዶ ቦታ አለ የሚለውን ሐሳብ አይቀበልም ነበር። በዚያን ጊዜ ከነበረው የሳይንቲስቶች እውቀት አንጻር የአርስቶትል ንድፈ ሐሳብ ትክክል ይመስል ስለነበር ወደ 2,000 ለሚጠጉ ዓመታት ሕዝቡ በጥቅሉ የእርሱን አስተሳሰብ ተቀብሎ ኖሯል። በ16ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ገደማ እንኳን ዦን ቦደ የተባለ ፈረንሳዊ ፈላስፋ ሰፊ ተቀባይነት የነበረውን አመለካከት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያለው ወይም ስለ ፊዚክስ ጥቂት የሚያውቅ ማንም ሰው ከባድና ግዙፍ የሆነችው ምድር . . . እየተግተረተረች . . . በራሷ ዛቢያ ላይ በመሽከርከር ፀሐይን ትዞራለች ብሎ አያስብም፤ ምክንያቱም ምድር ትንሽ ብትንቀሳቀስ ታላላቅ ከተሞችና ቅጥሮች፣ የገጠር ከተሞችና ተራሮች ይደረማመሱ ነበር።”

ቤተ ክርስቲያን የአርስቶትልን አስተሳሰብ ተቀበለች

በጋሊሊዮና በቤተ ክርስቲያን መካከል ለተፈጠረው ውዝግብ መንስኤ የሆነው ሌላው ምክንያት ብቅ ያለው በ13ኛው መቶ ዘመን ነበር፤ ለግጭቱ መፈጠር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥልጣን የነበረው ቶማስ አኳይነስ (1225-74) ትልቁን ሚና ተጫውቷል። አኳይነስ የፈላስፎች ቁንጮ አድርጎ ለሚመለከተው ለአርስቶትል ጥልቅ አክብሮት ነበረው። የአርስቶትልን ፍልስፍና ከቤተ ክርስቲያኗ ትምህርቶች ጋር ለማዋሃድ ለአምስት ዓመት ያህል ብርቱ ትግል አድርጓል። ዌድ ሮውለንድ የተባሉ ሰው ጋሊሊዮስ ሚስቴክ (የጋሊሊዮ ስህተት) በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ጋሊሊዮ በኖረበት ዘመን “ከአርስቶትል ፍልስፍናዎች ጋር የተቀላቀሉት የአኳይነስ መንፈሳዊ ትምህርቶች የሮማ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ቀኖናዎች ሆነው ነበር” ብለዋል። ከዚህም በላይ በዚያ ዘመን ራሱን የቻለ የሳይንስ ማኅበረሰብ እንዳልነበረ ማስተዋል ይገባል። በአጠቃላይ ትምህርት ነክ ጉዳዮችን የምትቆጣጠረው ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖትና በሳይንስ ላይ ብቸኛዋ ባለ ሥልጣን ነበረች።

በቤተ ክርስቲያንና በጋሊሊዮ መካከል ለተፈጠረው ውዝግብ ዋነኛው መንስኤ ይህ ነበር። ጋሊሊዮ የስነ ፈለክ ተመራማሪ ከመሆኑ በፊት የነገሮችን እንቅስቃሴ የሚመለከት ጽሑፍ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ላይ በጣም ይከበር የነበረው አርስቶትል የፈጠራቸውን መላ ምቶች እንደሚጠራጠር ገልጿል። ይሁን እንጂ ጋሊሊዮ በ1633 በካቶሊክ ፍርድ ሸንጎ ፊት እንዲቀርብ ምክንያት የሆነው የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት ፀሐይ ናት የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በጽናት መደገፉና ይህ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚስማማ መናገሩ ነበር።

ጋሊሊዮ የመከላከያ ሐሳብ በሚያቀርብበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን በጥብቅ እንደሚያምን አረጋግጧል። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ለተራው ሕዝብ እንደሆነና ፀሐይ እንደምትዞር ያሳያል የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ቃል በቃል መረዳት እንደማይገባ ተሟግቷል። ይሁን እንጂ ክርክሩ ፍሬ ቢስ ነበር። ጋሊሊዮ በግሪክ ፍልስፍና በመመራት ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቺ መስጠትን በመቃወሙ ተወግዟል! የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጋሊሊዮ ላይ የተበየነው ፍርድ ስህተት መሆኑን በይፋ ያመነችው በ1992 ነበር።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

ከእነዚህ ክንውኖች ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ ደረጃ ጋሊሊዮ በቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ላይ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምንም ጥርጣሬ አልነበረውም። አንድ የሃይማኖት ርዕሰ ጉዳዮች ጸሐፊ “ቤተ ክርስቲያን፣ እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በጥብቅ ልትከተል ይቅርና ከመጀመሪያውም በደንብ እንዳልያዘችው የጋሊሊዮ ታሪክ ያስገነዝባል” ሲሉ ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያን የግሪኮችን ፍልስፍና ከሃይማኖታዊ ትምህርቶቿ ጋር በመቀላቀል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከመከተል ይልቅ ለወጎች እጅዋን ሰጥታለች።

እነዚህ ሁሉ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ልማድና በዚህ ዓለም መሠረታዊ ሕግጋት ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ ያስታውሱናል።—ቆላስይስ 2:8

ዛሬም እንኳን ክርስቲያን ነን የሚሉ በርካታ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚቃረኑ ጽንሰ ሐሳቦችና ፍልስፍናዎች ያምናሉ። ለምሳሌ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ ከሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ይልቅ የዳርዊንን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አምነው ተቀብለዋል። በዚህ መንገድ አብያተ ክርስቲያናት ዳርዊንን የዘመናችን አርስቶትል ያደረጉት ከመሆኑም በላይ ዝግመተ ለውጥን ደግሞ ከሃይማኖታዊ ትምህርታቸው መካከል ፈርጀውታል።b

እውነተኛ ሳይንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል

ከላይ የተመለከትናቸው ሐሳቦች ለሳይንስ ያለንን አመለካከት ሊያዛቡብን አይገባም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ከአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ትምህርት እንድንቀስምና ከምናያቸው ነገሮች የአምላክን አስደናቂ ባሕርያት እንድናጤን ይጋብዘናል። (ኢሳይያስ 40:26፤ ሮሜ 1:20) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ ሳይሆን የአምላክን የአቋም ደረጃዎች የምንማርበት፣ የፍጥረት ሥራዎቹን በማየት ብቻ ልንማራቸው የማንችላቸውን ባሕርያቱን የምናውቅበትና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ የምንገነዘብበት መጽሐፍ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። (መዝሙር 19:7-11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) እንዲህም ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለ ፍጥረት ተጠቅሶ የምናገኘው ነገር ሁሉ ትክክል ነው። ጋሊሊዮ ራሱ “መጽሐፍ ቅዱስንና ፍጥረትን ወደ ህልውና ያመጣው አምላክ ነው። . . . እነዚህ ሁለት እውነቶች ፈጽሞ ሊጋጩ አይችሉም” ብሏል። እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት።

ከዋክብትና ፕላኔቶች ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይበልጥ መሠረታዊ የሆነው ነገር፣ በጽንፈ ዓለም የሚገኙት ቁስ አካላት በሙሉ እንደ ስበት ባሉ ሕግጋት የሚመሩ መሆናቸው ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ስለ ተፈጥሮ ሕጎች ለመጀመሪያ ጊዜ የጻፈው አጽናፈ ዓለምን በስሌት መግለጽ እንደሚቻል ያምን የነበረው ፓይታጎረስ ነው። ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ ደግሞ ጋሊሊዮ፣ ኬፕለርና ኒውተን ቁስ አካል ምክንያታዊ በሆኑ ሕግጋት እንደሚመራ አረጋገጡ።

ስለ ተፈጥሮ ሕግ የተጠቀሰው ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ደግሞ በኢዮብ መጽሐፍ ላይ ይገኛል። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1600 ገደማ አምላክ ኢዮብን “የሰማያትን ሥርዐት [ወይም ሕግ] ታውቃለህ?” ብሎ ጠይቆት ነበር። (ኢዮብ 38:33) ከክርስቶስ ልደት በፊት በሰባተኛው መቶ ዘመን የተጻፈው የኤርምያስ መጽሐፍ፣ ይሖዋ “የጨረቃንና የከዋክብትን ሥርዓት” እንዲሁም “የሰማይንና የምድርንም ሥርዐት” እንደፈጠረ ይናገራል። (ኤርምያስ 31:35 የ1954 ትርጉም፤ 33:25) ጆርጅ ሮውሊንሰን የተባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ እነዚህን ዘገባዎች ከተመለከቱ በኋላ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እንደ ዘመናችን ሳይንቲስቶች ሁሉ ስለ አጠቃላዩ የተፈጥሮ ሕግ አስረግጠው ተናግረዋል” በማለት ገልጸዋል።

ለምሳሌ ያህል በኢዮብ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ዘገባ የተጻፈው ፓይታጎረስ በጽንፈ ዓለም ያሉትን ነገሮች ስለሚቆጣጠረው ሕግ ከመጻፉ ወደ አንድ ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ ስለ ተፈጥሮ እውነታዎች ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን ይሖዋ የሁሉም ነገሮች ምንጭ መሆኑን ለማስተማርና የተፈጥሮ ሕጎችን መፍጠር እንደሚችል ለማስገንዘብም እንደሆነ አትዘንጋ።—ኢዮብ 38:4, 12፤ 42:1, 2

ሌላው ምሳሌ የሚሆነን ደግሞ በምድር ላይ የሚገኘው ውኃ የሚያደርገው ዑደት ነው። የውኃ ዑደትን በአጭሩ ለመግለጽ ያህል ውኃ ከባሕር ላይ ይተንና ደመና ይሆናል፤ ከዚያም በዝናብ ወይም በበረዶ መልክ ወደ ምድር ይዘንባል፤ ከዚያም እንደገና ወደ ባሕር ይገባል። ስለዚህ ዑደት የሚገልጹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆኑና እስከ አሁን ድረስ ያሉ ጥንታዊ ማስረጃዎች የተጻፉት ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው መቶ ዘመን ነው። ይሁን እንጂ ይህንን የሚመለከተው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የተጻፈው እነዚህ ማስረጃዎች ከመጻፋቸው በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት ቀደም ብሎ ነው። ለምሳሌ ያህል የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ከክርስቶስ ልደት በፊት በ11ኛው መቶ ዘመን “ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ” ብሎ ጽፏል።—መክብብ 1:7

እንዲሁም ተራ እረኛና ገበሬ የነበረው ነቢዩ አሞጽ በ800 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ‘የባሕሩን ውሃ ጠርቶ፣ በገጸ ምድር ላይ የሚያፈሰው’ ይሖዋ እንደሆነ ጽፏል። (አሞጽ 5:8) ሰሎሞንና አሞጽ የተወሳሰቡ ሙያዊ ቃላትን መጠቀም ሳያስፈልጋቸው በተለያየ መንገድ ስለ ውኃ ዑደት በትክክል ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ምድርን እንዲያው በባዶው ላይ እንዳንጠለጠላት’ ይናገራል። (ኢዮብ 26:7) እነዚህ ቃላት በተነገሩበት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1600 ገደማ ከነበረው እውቀት አንጻር ሲታይ፣ ጠጣር የሆነ ነገር በሕዋ ውስጥ አለምንም ድጋፍ ሊንጠለጠል መቻሉን የገለጸ ሰው ሊደነቅ ይገባዋል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ይህ ከተነገረ ከ1,200 ዓመታት በኋላ የኖረው አርስቶትል እንኳን ሕዋ አለ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ አይቀበልም ነበር!

የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ተቀባይነት አግኝተው በነበረበት መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን፣ እነዚህን የመሰሉ ትክክለኛ ዘገባዎች ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ መስፈራቸው አያስደንቅህም? አስተዋይ ለሆነ ሰው ይህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት መጻፉን የሚያረጋግጥለት አንድ ማስረጃ ነው። ስለዚህ ከአምላክ ቃል ጋር በሚጋጭ ትምህርት ወይም ጽንሰ ሐሳብ በቀላሉ ላለመታለል ጥንቃቄ ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ነው። ታሪክ በተደጋጋሚ እንዳረጋገጠው በጣም የተማሩ ሰዎች እንኳን የተናገሯቸው ፍልስፍናዎች ለተወሰነ ጊዜ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ ይሆናል፤ “የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—1 ጴጥሮስ 1:25

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከክርስቶስ ልደት በፊት በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረውና የሳሞሱ አርስጥሮኮስ ተብሎ ይጠራ የነበረው ግሪካዊ፣ የጽንፈ ዓለም እምብርት ፀሐይ ናት ይል የነበረ ቢሆንም የአርስቶትል እምነት ድጋፍ በማግኘቱ ምክንያት ተቀባይነት አጥቷል።

b ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ሰፊ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዘኛ) በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን “ብዙዎች በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑት ለምንድን ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 15ን ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የፕሮቴስታንቶች አመለካከት

የፕሮቴስታንት የተሐድሶ እንቅስቃሴ መሪዎችም የሥርዓተ ፀሐይ እምብርት ፀሐይ ናት የሚለውን አስተሳሰብ ያወግዙ ነበር። ከእነዚህም መካከል ማርቲን ሉተር (1483-1546)፣ ፊሊፕ መላንክተን (1497-1560) እና ጆን ካልቪን (1509-64) ይገኙበታል። ሉተር ስለ ኮፐርኒከስ ሲናገር “ይሄ ሞኝ ጠቅላላውን የስነ ፈለክ ሳይንስ ለመቀልበስ ተመኝቶ ነበር” ብሏል።

ለውጥ አራማጆቹ በኢያሱ ምዕራፍ 10 ላይ ፀሐይና ጨረቃ ‘ባሉበት መቆማቸውን’ የሚገልጸውን ዘገባ የመሳሰሉ ቃል በቃል የተረዷቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ አንዳንድ ታሪካዊ ክንውኖችን እንደ ማሳመኛ ነጥብ አድርገው ያቀርቡ ነበር።c ለውጥ አራማጆቹ እንዲህ ያለ ጥብቅ አቋም የነበራቸው ለምንድን ነው? ጋሊሊዮስ ሚስቴክ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ እንደገለጸው የፕሮቴስታንት የተሐድሶ እንቅስቃሴ የሊቀ ጳጳሱን ቀንበር ቢጥልም ከአርስቶትልና ከቶማስ አኳይነስ “ሥልጣን ነፃ መውጣት” አልቻለም፤ ምክንያቱም የእነዚህ ሰዎች አመለካከት “በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች ዘንድ በእኩል ደረጃ ተቀባይነት ነበረው።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

c “ፀሐይ ወጣች” እና “ጀንበር ጠለቀች” የሚሉት አነጋገሮች ከሳይንስ አንጻር ትክክል አይደሉም። ይሁን እንጂ እነዚህ አባባሎች በዕለት ተዕለት ንግግራችን ተቀባይነት ከማግኘታቸውም በላይ የምንናገረው ከምድር እየተመለከትን በመሆኑ ትክክለኛ ናቸው። በተመሳሳይ ኢያሱ የተናገረው ስለ ስነ ፈለክ የምርምር ውጤት ሳይሆን በወቅቱ እየተመለከተ ስለነበረው ነገር ነው።

[ሥዕሎች]

ሉተር

ካልቪን

[ምንጭ]

ሰርቪተስ ኤንድ ካልቪን (1877) ከሚለው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አርስቶትል

[ምንጭ]

ኤ ጀነራል ሂስትሪ ፎር ኮሌጅስ ኤንድ ሃይ ስኩልስ (1900) ከተባለ መጽሐፍ የተወሰደ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶማስ አኳይነስ

[ምንጭ]

ከኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጂየስ ኖውሌጅ (1855) የተወሰደ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አይዛክ ኒውተን

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ስለ ምድር የውኃ ዑደት ገልጿል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ