የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wp17 ቁጥር 4 ገጽ 4-7
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወትና ስለ ሞት ምን ይላል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወትና ስለ ሞት ምን ይላል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
  • ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት ተስፋፋ
  • ‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’
  • በትንሣኤ ላይ ያለህ እምነት ምን ያህል ጠንካራ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ነፍስ የሚጠብቃት የተሻለ ተስፋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ሙታን የት ናቸው?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ከሞት በኋላ ሕይወት—ሰዎች ምን ብለው ያምናሉ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
wp17 ቁጥር 4 ገጽ 4-7
መቃብር ውስጥ ያለ አስከሬን

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሕይወትንና ሞትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወትና ስለ ሞት ምን ይላል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን እንዲህ ሲል እንዳዘዘው ይናገራል፦ “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ እስክትረካ ድረስ መብላት ትችላለህ። ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ ግን አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) ይህ ጥቅስ በግልጽ እንደሚያሳየው አዳም የአምላክን ትእዛዝ ቢያከብር ኖሮ አይሞትም ነበር፤ ከዚህ ይልቅ በኤደን ገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ይችል ነበር።

አዳምና ሔዋን አርጅተው

የሚያሳዝነው ግን አዳም የአምላክን ትእዛዝ ችላ በማለት ሚስቱ ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ እንዲበላ ያቀረበችለትን ግብዣ ተቀበለ። (ዘፍጥረት 3:1-6) አዳም አለመታዘዙ ያስከተለው መዘዝ ለእኛም ተርፏል። ይህን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) እዚህ ጥቅስ ላይ “አንድ ሰው” የተባለው አዳም ነው። ለመሆኑ አዳም የሠራው ኃጢአት ምን ነበር? ሞት ያስከተለበትስ ለምንድን ነው?

አዳም ያደረገው ነገር ማለትም የአምላክን ሕግ ሆን ብሎ መጣሱ ወይም አለመታዘዙ ኃጢአት ነው። (1 ዮሐንስ 3:4) አምላክ ለአዳም እንደገለጸለት ኃጢአት የሞት ቅጣት ያስከትላል። አዳምም ሆነ ዘሮቹ አምላክን እስከታዘዙ ድረስ ለኃጢአትና ለሞት አይዳረጉም ነበር። አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው እንዲሞቱ ሳይሆን ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ‘ሞት ለሰው ሁሉ እንደተዳረሰ’ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከሞትን በኋላ ከእኛ ተለይታ በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ነገር አለች? ብዙዎች ለዚህ ጥያቄ አዎ የሚል መልስ ይሰጣሉ፤ የማትሞት ነፍስ በውስጣችን አለች ብለው ያምናሉ። ይህ ግን አምላክ አዳምን ዋሽቶታል ብሎ እንደመናገር የሚቆጠር ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ከሞተ በኋላ በውስጡ ያለች አንዲት ረቂቅ ነገር በሌላ ዓለም በሕይወት መኖሯን የምትቀጥል ከሆነ አምላክ እንደተናገረው ሞት ለኃጢአት ቅጣት አይሆንም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ሊዋሽ [አይችልም]” ይላል። (ዕብራውያን 6:18) እንዲያውም ሔዋንን “አትሞቱም” በማለት የዋሸው ሰይጣን ነበር።—ዘፍጥረት 3:4

ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በውሸት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ‘ስንሞት ምን እንሆናለን?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የዘፍጥረት መጽሐፍ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ሠራው፤ በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውየውም ሕያው ሰው ሆነ።” “ሕያው ሰው” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ነፈሽa የሚል ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “የሚተነፍስ ፍጥረት” ማለት ነው።—ዘፍጥረት 2:7 የግርጌ ማስታወሻ

ከዚህ መመልከት እንደምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ ሰው የማትሞት ነፍስ እንዳለችው አይናገርም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ግለሰብ “ሕያው ሰው” ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ስናገላብጥ ብንውል “የማትሞት ነፍስ” የሚል አገላለጽ አናገኝም።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሰው የማትሞት ነፍስ እንዳለችው የማይናገር ከሆነ አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ነፍስ አትሞትም ብለው የሚያስተምሩት ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የጥንቶቹ ግብፃውያን የነበራቸውን እምነት እንመርምር።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ትምህርት ተስፋፋ

በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረው ሄሮዶተስ የተባለው ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ “ነፍስ አትሞትም ብለው ማስተማር የጀመሩት” ግብፃውያን እንደነበሩ ተናግሯል። የጥንቶቹ ባቢሎናውያንም ነፍስ አትሞትም ብለው ያምኑ ነበር። ታላቁ እስክንድር በ332 ዓ.ዓ. መካከለኛውን ምሥራቅ በተቆጣጠረበት ወቅት ግሪካውያን ፈላስፎች ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርገው ነበር፤ በመሆኑም ይህ ትምህርት በመላው የግሪክ ግዛት በፍጥነት ተስፋፋ።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የማትሞት ነፍስ” የሚል አገላለጽ አይገኝም

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ኤሴናውያን እና ፈሪሳውያን የሚባሉ ሁለት የአይሁድ እምነት ኑፋቄዎች ‘ሰው ሲሞት ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ በሕይወት መኖሯን ትቀጥላለች’ ብለው ያስተምሩ ነበር። ዘ ጂዊሽ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “አይሁዳውያን ነፍስ አትሞትም ብለው ማመን የጀመሩት የግሪካውያን አስተሳሰብ በተለይ ደግሞ የፕላቶ ፍልስፍና ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው ነው።” በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስም ይህ ትምህርት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሳይሆን ‘የአፈ ታሪክና የተረቶች ስብስብ’ ብሎ በጠራው “የግሪክ ልጆች እምነት” ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ገልጿል።

የግሪካውያን አስተሳሰብ እየተስፋፋ ሲሄድ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎችም ይህን የአረማውያን ትምህርት ተቀበሉ። ታሪክ ጸሐፊው ዮና ሌንደሪንግ እንደገለጹት ከሆነ “ነፍሳችን በአንድ ወቅት በተሻለ ቦታ ትኖር እንደነበረ፣ አሁን ግን ኃጢአተኛ በሆነ ዓለም ውስጥ እንደምትኖር የሚገልጸው የፕላቶ ግምታዊ ሐሳብ ክርስቲያኖች የእሱን ፍልስፍና በቀላሉ እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል።” በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያን ነፍስ አትሞትም የሚለውን የአረማውያን ትምህርት የተቀበለች ሲሆን ውሎ አድሮ ይህ እምነት ከዋነኞቹ የክርስትና ትምህርቶች አንዱ ሆነ።

‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፦ “በመንፈስ መሪነት የተነገረው ቃል በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች ከመናፍስት ለሚመነጩ አሳሳች ቃሎችና ለአጋንንት ትምህርቶች ጆሯቸውን በመስጠት ከእምነት መውጣታቸው እንደማይቀር በግልጽ ይናገራል።” (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑ በግልጽ ታይቷል። ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ‘ከአጋንንት ትምህርቶች’ አንዱ ነው። ይህ ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የሌለው ሲሆን ከጥንቶቹ አረማዊ ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች የመነጨ ነው።

ደስ የሚለው ነገር ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 8:32) የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችን አብዛኞቹ የዓለም ሃይማኖቶች ከሚያስፋፏቸው አምላክን የሚያዋርዱ ትምህርቶችና ልማዶች ነፃ እንድንወጣ አስችሎናል። ከዚህም በላይ በአምላክ ቃል ውስጥ ያለው እውነት ከሞት ጋር በተያያዘ ሰዎች ከሚከተሏቸው ልማዶችና አጉል እምነቶች ነፃ ያወጣናል።—“ሙታን የት ናቸው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በምድር ላይ 70 ወይም 80 ዓመት ብቻ ከኖሩ በኋላ ወደ ሌላ ዓለም ተሸጋግረው ለዘላለም እንዲኖሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የእሱ ታዛዥ ልጆች ሆነው እዚሁ ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ በማሰብ ነው። ይህ ታላቅ ዓላማ አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር መግለጫ ሲሆን ዓላማው መፈጸሙ አይቀርም። (ሚልክያስ 3:6) መዝሙራዊው “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት በመንፈስ መሪነት የተናገረው ሐሳብ የሚያጽናና ነው።—መዝሙር 37:29

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕይወትና ሞት ምን እንደሚል ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ከፈለግክ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ተመልከት። መጽሐፉን www.jw.org/am ላይም ማግኘት ይቻላል።

a ነፈሽ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል የ1954 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እና አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ሕያው ነፍስ” በማለት የተረጎሙት ሲሆን የ1980 ትርጉም ደግሞ “ሕይወት ያለው ፍጡር” ብሎ ተርጉሞታል።

ሰዎች ለዘላለም መኖር ይችላሉ?

ከጥቂት ዓመታት በፊት ተመራማሪዎች በውኃ ውስጥ ያገኟቸው አንዳንድ ዕፀዋት በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የኖሩ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፤ ምናልባትም እነዚህ ዕፀዋት በምድር ላይ ካለው ማንኛውም ሕያው ፍጥረት የበለጠ ዕድሜ ያላቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ዕፀዋት ፖሲዶኒያ ኦሺያኒካ ተብሎ የሚጠራው የባሕር ቄጠማ ዝርያዎች ናቸው፤ ይህ ተክል በስፔንና በቆጵሮስ መካከል ያለውን ሰፊ የሜድትራንያን ባሕር ወለል ሸፍኖ ይገኛል።

ዕፀዋት ይህን ያህል ዕድሜ መኖር ከቻሉ የሰዎች ዕድሜ ያጠረው ለምንድን ነው? ስለ እርጅና የሚያጠኑ አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት የሰዎችን ዕድሜ ማስረዘም እንደሚቻል ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ በዚህ መስክ የተደረሰባቸውን “ብዙ አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶች” ይዘረዝራል። ሳይንሳዊ ግኝቶች በሰው ዕድሜ ርዝማኔ ላይ የሚያመጡት ለውጥ ይኑር አይኑር ወደፊት የሚታይ ነገር ነው።

ይሁንና የዘላለም ሕይወት ተስፋ በዘመናዊ ሳይንስ ላይ የተመካ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ ሲናገር “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው” ይላል። (መዝሙር 36:9) ኢየሱስም ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) በእርግጥም ይሖዋ አምላክንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅና ለማስደሰት የምናደርገው ጥረት ዘላለማዊ በረከቶች ያስገኝልናል።

የባሕር ቄጠማ

ተመራማሪዎች የዚህ የባሕር ቄጠማ ዝርያ የሆኑ አንዳንድ ዕፀዋት በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደኖሩ ያምናሉ

ሙታን የት ናቸው?

ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው

መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን በመቃብር ውስጥ እንደሆኑና ወደፊት ትንሣኤ እንደሚያገኙ ይናገራል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ‘ሙታን ምንም ስለማያውቁ’ ሥቃይ እየደረሰባቸው እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው። (መክብብ 9:5) ኢየሱስ ሞትን ከከባድ እንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐንስ 11:11-14) በመሆኑም በሞት ያንቀላፉትን የምንፈራበት ወይም ለእነሱ ስንል እንደ ተዝካርና ሙት ዓመት ያሉ ድግሶችን የምናዘጋጅበት ምንም ምክንያት የለም። ሙታን ሊረዱንም ሆነ ሊጎዱን አይችሉም፤ ምክንያቱም “በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።” (መክብብ 9:10) ይሁን እንጂ አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት ሞትን እንዳልነበረ ያደርገዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:26, 55፤ ራእይ 21:4

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ሊጣልበት የሚገባው መጽሐፍ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ቀጥሎ የቀረበውን ማስረጃ ተመልከት፦

  • ከላባ የተሠራ ብዕርና የቀለም ብልቃጥ

    ተወዳዳሪ የሌለው ደራሲ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ከ1513 ዓ.ዓ. እስከ 98 ዓ.ም. ድረስ ባሉት 16 መቶ ዓመታት ውስጥ 40 በሚያህሉ ሰዎች የተጻፉ 66 መጻሕፍትን የያዘ መጽሐፍ ነው። ያም ሆኖ በውስጡ የያዘው ሐሳብ እርስ በርሱ አይጋጭም፤ ከዚህም ሌላ መልእክቱ ከዳር እስከ ዳር ተያያዥነት ያለው ነው። ይህም የመጽሐፉ ደራሲ ወይም ባለቤት ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ እንደሆነ ያረጋግጣል። መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት፣ ሰዎች ቢሆኑም መልእክቱ የመጣው ከአምላክ ነው።

  • ዓምድ

    ትክክለኛ ታሪካዊ ዘገባ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ክንውኖች ትክክለኛ ከሆኑ ታሪካዊ መረጃዎች ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ። ኤ ሎየር ኤግዛምንስ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦ “ስለ ፍቅር የተጻፉ ልብ ወለድ መጽሐፎች፣ አፈ ታሪኮችና የሐሰት ማስረጃዎች በውል በማይታወቅ ስፍራና በአንድ ያልተወሰነ ጊዜ ላይ የተፈጸሙ ነገሮችን የሚገልጹ ቢሆንም . . . በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች ግን ሁኔታዎቹ የተፈጸሙበትን ጊዜና ቦታ በትክክል ይገልጹልናል።”

  • አተም

    ትክክለኛ ሳይንሳዊ መረጃ፦ እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ አይደለም፤ ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመን ያልተደረሰባቸውን ትክክለኛ ሳይንሳዊ መረጃዎች ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ምዕራፍ 13 እና 14 ላይ ስለ ጀርሞችና ተላላፊ ስለሆኑ በሽታዎች ገና ምንም ባልታወቀበት ዘመን የግል ንጽሕናንና የጤና አጠባበቅን እንዲሁም በሽተኞች እንዲገለሉ ማድረግን በተመለከተ ዝርዝር ሕጎች ተሰጥተዋል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ክብ መሆኗንና በሕዋ ላይ ተንጠልጥላ እንደምትገኝ የሚናገር ሲሆን ሳይንስ እነዚህን እውነታዎች የደረሰባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጻፉ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ነው።—ኢዮብ 26:7፤ ኢሳይያስ 40:22

እስካሁን የተመለከትናቸው ምሳሌዎች “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ትክክለኛ መሆኑን ከሚያረጋግጡት በርካታ ማስረጃዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ