ስብሰባዎችን በሰዓቱ ጀምራችሁ በሰዓቱ ጨርሱ
1 የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባን ጨምሮ ሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች በሰዓቱ ተጀምረው በሰዓቱ ማብቃት አለባቸው። ለምን? ሰዓት ማክበር የሥርዓታማነት ምልክት ከመሆኑም በላይ በስብሰባዎች ላይ ለሚገኙትም ሆነ ክፍሎቹን ለሚያቀርቡት አሳቢነት የሚገለጽበት መንገድ በመሆኑ ነው። (መክ. 3:17ሀ፤ 1 ቆሮ. 14:33) ስብሰባዎችን በሰዓቱ ጀምሮ በሰዓቱ ለማብቃት ቀጥሎ የቀረቡትን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ አሳቢነታችንን ማሳየት እንችላለን።
2 ከሌሎች ጋር ለመጫወት፣ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ለማከናወንና በመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት ለመካፈል ምንጊዜም ቀደም ብለን ወደ ስብሰባ ለመምጣት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በጥቅሉ ሲታይ መዝሙርና ጸሎት አምስት ደቂቃ ይፈጃል። ጉባኤውን ወክለው ጸሎት የሚያቀርቡ ወንድሞች የስብሰባውን ዓላማ ማስታወስ የሚኖርባቸው ሲሆን ይህንንም በመክፈቻውም ሆነ በመደምደሚያው ጸሎት ላይ መጥቀስ ይገባቸዋል። በዚህ ጊዜ የሚያቀርቡት ጸሎት ረጅም መሆን አያስፈልገውም።
3 የሕዝብ ስብሰባ:- ለሕዝብ ንግግር የሚመደበው ጊዜ 45 ደቂቃ ነው። ከተመደበው ጊዜ ማሳለፍ ቀጥሎ የሚቀርበውን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ሰዓት ይሻማል። መዝሙሮቹንና የሚቀርቡትን ጸሎቶች ጨምሮ ሁለቱ ስብሰባዎች በሁለት ሰዓት ውስጥ መጠናቀቅ አለባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ስብሰባው 9:00 ላይ በመክፈቻው መዝሙር ከተጀመረ የሕዝብ ተናጋሪው 9:50 ላይ ንግግሩን ማብቃት አለበት። ከዚያም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በ9:55 ተጀምሮ 10:55 ላይ ሲያበቃ ስብሰባው በመዝሙርና በጸሎት ይደመደማል። የሕዝብ ተናጋሪዎች የንግግሩ አስተዋጽኦ ላይ የተመደበውን ጊዜ በጥብቅ መከተል ያለባቸው ሲሆን እንደ ሰላምታ ያሉ ከንግግሩ ጋር ዝምድና የሌላቸውን ጉዳዮች ማካተት የለባቸውም። ተናጋሪው የመሰብሰቢያ አዳራሹ የሚገኝበትን ቦታ የማያውቅ ከሆነ አቅጣጫውንና እዚያ ለመድረስ በግምት ምን ያህል ሰዓት እንደሚፈጅበት የጋበዙትን ወንድሞች መጠየቅ አለበት።
4 “የመጠበቂያ ግንብ” ጥናት:- ሁሉም አንቀጾች ተነብበውና የክለሣ ጥያቄዎቹ ውይይት ተደርጎባቸው ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት የተመደበው አንድ ሰዓት ነው። የጥናቱ መሪ የሚናገራቸው ከርዕሱ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ያላቸው አጠር ያሉ የመግቢያ ሐሳቦች የአድማጮችን ጉጉት የሚቀሰቅሱና ወደ ትምህርቱ የሚመሩ መሆን አለባቸው። በጥናቱ ወቅት ብዙ ሐሳቦችና ማብራሪያዎች መስጠት የለበትም። የሚመራው ወንድም በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች ላይ ብዙ ሰዓት አጥፍቶ በኋላ ላይ የቀሩትን ቁጥሮች ለመጨረስ እንዳይጣደፍ ሰዓቱን ለትምህርቱ ማብቃቃት ይኖርበታል።
5 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት:- ይህ የ45 ደቂቃ ስብሰባ ነው። የማስተማሪያ ንግግርና የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦችን የሚያቀርቡት ወንድሞች የተመደበላቸው ሰዓት ሲያበቃ እንዲያቆሙ ባይደረጉም በተመደበላቸው ጊዜ ውስጥ መጨረስ አለባቸው። ሰዓት የሚያሳልፉ ከሆነ በግላቸው ምክር ሊሰጣቸው ይገባል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች የሚሰጠው ምክርና ሐሳብ ከተመደበለት ጊዜ ማለፍ አይኖርበትም። ሁሉም ተማሪዎች ለመድረኩ በሚቀርብ ቦታ ቢቀመጡና የተመደበላቸው ሰዓት ሲያበቃ ወዲያውኑ ክፍላቸውን ቢደመድሙ ጊዜ መቆጠብ ይቻላል።—የዚህን ዓመት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ተመልከት።
6 የአገልግሎት ስብሰባ:- ይህም የ45 ደቂቃ ስብሰባ ነው። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትን እንዲሁም መዝሙሮቹንና የሚቀርቡትን ጸሎቶች ጨምሮ አጠቃላዩ ስብሰባ ከአንድ ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ በላይ መፍጀት የለበትም። ስለዚህ የመክፈቻው መዝሙር 12:00 ላይ ከጀመረ ትምህርት ቤቱ በ12:50 ማብቃት ይኖርበታል። 1:40 ላይ አድማጮች ለመደምደሚያው መዝሙርና ጸሎት እንዲነሱ ይጋበዛሉ። በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ያላቸው ወንድሞች የተመደበውን ሰዓት ማክበር አለባቸው። በጥያቄና መልስ የሚቀርቡ ክፍሎች መግቢያቸው አጭር መሆን አለበት። ሰፋ ያለ የመግቢያ ሐሳብ መናገር አያስፈልግም። ሠርቶ ማሳያዎች ጥሩ ልምምድ የተደረገባቸው ሊሆኑ ይገባል፤ የሚያቀርቡት ወንድሞችና እህቶችም ለክፍሉ የተመደበውን ሰዓት ላለማባከን ዝግጁ ሆነው በቦታው ሊቀመጡ ይገባል። አንድን ክፍል የሚያቀርበው ወንድም ሰዓት ቢያሳልፍም ቀጣዩ ተናጋሪ አጠቃላይ ስብሰባውን በሰዓቱ ለመደምደም እንዲቻል ክፍሉን ሊያሳጥረው ይገባል።
7 የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት:- የመክፈቻና የመደምደሚያውን ጸሎት ጨምሮ የአንድ ሰዓት ስብሰባ ነው። ሁሉም አንቀጾች መነበብ አለባቸው። የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ ስብሰባውን በሰዓቱ ለማብቃት ትምህርቱን በሰዓት ሊከፋፍለው ይችላል፤ እንዲህ ማድረጉ የትምህርቱን የመጨረሻ ቁጥሮች በጥድፊያ ከመሸፈን ወይም ከሰዓቱ በጣም ቀድሞ ከመጨረስ ያድነዋል። በእያንዳንዱ አንቀጽ ላይ ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ ማመዛዘን መቻል አለበት። አድማጮቹ ዋና ዋና ነጥቦቹን በሚገባ እንዲረዷቸው ማድረግ ይኖርበታል። የማስተማር ችሎታውን ማዳበሩ በዚህ ረገድ የሚያጋጥሙትን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ያስችለዋል።—ቲቶ 1:9
8 የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ:- ክልል መመደብንና የመደምደሚያውን ጸሎት ጨምሮ ስብሰባው ከ15 ደቂቃ መብለጥ የለበትም። ወደ አገልግሎት የሚወጡ ወንድሞችና እህቶች አገልግሎታቸውን ወዲያው መጀመር ይፈልጋሉ። ስብሰባውን የሚመራው ወንድም ብዙዎች እስኪሰባሰቡ ሳይጠብቅ በሰዓቱ መጀመር አለበት። ከዚህም በላይ ክልሎች ከተመደቡና ስብሰባው በጸሎት ከተደመደመ በኋላ ቡድኑ ጊዜ ሳያጠፋ ወደ አገልግሎት መውጣት ይኖርበታል። በተለይ በስብሰባው ላይ አቅኚዎች የሚገኙ ከሆነ እንደዚህ ማድረጉ ተገቢ ነው።
9 ስብሰባዎች በሰዓቱ ተጀምረው በሰዓቱ ሲያበቁ ሁላችንም እንጠቀማለን። በተለይ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸውና በተወሰነ ሰዓት ወደ ቤት እንዲመለሱ የሚጠበቅባቸው ወንድሞችና እህቶች እንደዚህ መደረጉን ያደንቁታል። በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ወደ ስብሰባዎች ለመምጣትና ለመመለስ መጓጓዣ በሚያዘጋጁበት ወይም ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን ሰዓት በሚናገሩበት ጊዜ ከወንድሞች ጋር ለመጫወት፣ ጽሑፎች ለመውሰድና ለመሳሰሉት ነገሮች የሚያስፈልጋቸውን ጊዜ ግምት ውስጥ ቢያስገቡ መልካም ነው። ስብሰባዎችን በሰዓቱ ጀምሮ በሰዓቱ መጨረስ “ሁሉ በአገባብና በሥርዓት” እንዲሆን ለማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ቆሮ. 14:40