በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች በጥሩ ሁኔታ መጠቀም
1 መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ዛሬ ሰዎች ከሚያነቧቸው መጽሔቶች ሁሉ የላቀ ጥቅም ያላቸው መጽሔቶች ናቸው። ለምን? ምክንያቱም የያዟቸው መንፈሳዊ እውነቶች በሰዎች ሕይወት ላይ ዘላለማዊ የሆነ መልካም ውጤት ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም ብዙዎች ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ንቁዎች አይደሉም፤ ወይም ደግሞ ይህን መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን እንዴት ሊያረኩት እንደሚችሉ አያውቁም። ሰዎች መንፈሳዊ ዓይናቸው እንዲከፈት በመርዳት ጳውሎስን ልንመስለው እንችላለን። — ማቴዎስ 5:3፤ ሥራ 26:18
2 ይሆናል የሚል አመለካከት ያላችሁና በሚገባ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፦ በክልላችሁ ውስጥ እውነትን የሚቀበሉ በግ መሰል ሰዎች አይጠፉም። አንዳንዶቹ የሚያስፈልጋቸው መጽሔቶቹን እንዲያነቡ በደግነት ማበረታታት ብቻ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ስታበረክቱ ይሆናል የሚል አመለካከት ያላችሁና ተግባቢዎች ሁኑ። ሌሎች ጽሑፎችን በምታበረክቱበት ጊዜም ቢሆን መጽሔቶቹን በርከት አድርጋችሁ በመያዝ ማንኛውንም አጋጣሚ ለማበርከት ተጠቀሙበት።
3 መጽሔቶችን በማበርከት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ራሳችን የመጽሔቶቹን ጠቃሚነት በትክክል መገንዘብ አለብን። በምናበረክታቸው መጽሔቶች ውስጥ ያሉትን ትምህርቶች በደንብ ማወቅ ይኖርብናል፤ ይህም መጽሔቶቹን ለማበርከት ያለንን ትምክህትና ጉጉት ከፍ ያደርገዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሔቶቹን ስታነቡ ይህን ሐሳብ በአእምሮአችሁ ያዙ። በአገልግሎታችሁ የምትጠቀሙባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ለመምረጥ ንቁዎች ሁኑ። እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ:- ‘ይህ ትምህርት በተለይ ለእነማን ይስማማል? ይህ የሚስማማው ለቤት እመቤት ነው፣ ለወጣት ነው፣ ወይስ ለነጋዴ ነው? ይህ ነጥብ ለተማሪ፣ ላገባ ሰው፣ ስለ አካባቢው ሁኔታ ለሚጨነቅ ሰው ይስማማልን? ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን መጽሔቶቹ ከያዟቸው ወቅታዊ ርዕሰ ትምህርቶች በግል ያገኘነውን እውቀትና ጥቅም መሠረት አድርገን መጽሔቶቹን እንዲያነቡ ለማበረታታት መቻል ይኖርብናል።
4 የቆዩ እትሞችን በሚገባ ተጠቀሙባቸው፦ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ከታተሙበት ቀን በአንድ ወይም በሁለት ወር ውስጥ ሁሉም መበርከት ባይችሉም እንኳን ያላቸውን ጠቃሚነት እንደማያጡ አስታውሱ። የያዟቸውን ሐሳቦች ጊዜ አይሽራቸውም፤ በጥሩ ሁኔታ አስቀምጠናቸው ከሆነ የቆዩትን ቅጂዎችም ቢሆን ከማበርከት ወደኋላ ማለት የለብንም። የቆዩ መጽሔቶች እንዲከማቹ ማድረግና በፍጹም አለመጠቀም ለእነዚህ ጠቃሚ መሣሪያዎች አድናቆት እንደጎደለን ያሳያል። እያንዳንዱ መጽሔት መንፈሳዊ ፍላጎቶችን የሚቀሰቅሱና የሚያረኩ እውነቶችን ይዟል። የቆዩትን እትሞች ከማስቀመጥና ከመርሳት ይልቅ እነዚህን መጽሔቶች ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ለማበርከት ልዩ ጥረት ማድረግ አይሻልምን?
5 የንቁ! መጽሔት በመጀመሪያ ጊዜ መንፈሳዊ ዝንባሌ ያልነበራቸው ብዙ ሰዎች ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁዎች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። የይሖዋን ሕዝብ በመንፈሳዊ ለመመገብ በወጣው ፕሮግራም ውስጥ መጠበቂያ ግንብ ዋነኛ መሣሪያ ነው። እነዚህ መጽሔቶች በግሩም ሁኔታ እርስ በርስ ይደጋገፋሉ፤ የምሥራቹም እንዲሰበክ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
6 ማንኛውንም አጋጣሚ መጽሔቶችን ለማበርከት ከተጠቀምንበት እነዚህ መጽሔቶች በግ መሰል የሆኑትን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊያረኩ እንደሚችሉ ሙሉ በሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይችላል። ይሆናል የሚል አመለካከት ለመያዝ፣ በሚገባ ለመዘጋጀትና በአገልግሎቱ አዘውታሪዎች ለመሆን እንፈልጋለን። የምሥራቹ አስፋፊዎች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ መጽሔቶች አዘውትረን በጥሩ ሁኔታ እንጠቀምባቸው።