ሌሎች እውነትን እንዲያውቁ እርዳቸው
1 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ስለ እውነት ሊመሠክር ነበር። እውነት ለሌሎች እንዲሰብክ ሲል ደቀ መዛሙርቱ አስተማሪዎች እንዲሆኑ አሠለጠናቸው። ሌሎችን በማስተማሩ ረገድ የተሳካላቸው እንደሚሆኑ ትምክህት ስለነበረው ‘መምህራን’ ሲል ጠርቷቸዋል። (ማቴ. 13:52 የ1980 ትርጉም) በማንኛውም ጊዜ በቀላሉ ሊያወጣው የሚችለው የሀብት ክምችት ካለው ሰው ጋር አመሳሰላቸው። ዛሬ ያሉት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ለማፋጠን በጽሑፎች ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ብዙ ጉባኤዎች በቅናሽ ዋጋ ሊበረከቱ የሚችሉ የቆዩ መጻሕፍት አሏቸው። እንደነዚህ ዓይነት መጻሕፍት ከሌሏችሁ ከኛ ልታገኟቸው ትችላላችሁ። ግባችን በዚህ ዘመቻ እነዚህን መጻሕፍት በሙሉ አበርክተን ለመጨረስ ነው። በጽሑፎቹ በመጠቀምም ሰዎች ስለ ታላቁ አስተማሪ፣ የሰው ልጆች ከዓለም መከራ የሚገላገሉ ስለመሆናቸው እንዲሁም ስለ አምላክ ዘላለማዊ ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት እንችላለን። በነዚህ ጠቃሚ መሣሪያዎች ለመጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2 “ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ” የተባለውን መጽሐፍ ለማበርከት የሚያስችልህን ውይይት ለመክፈት እንዲህ ልትል ትችላለህ፦
◼ “ጤና ይስጥልኝ። ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮ ለመገንባት የሚፈልጉ ሰዎችን እያነጋገርን ነን። በአሁኑ ጊዜ ልጆቻችን በዓለም ላይ አፍራሽ ተጽዕኖዎች ስለሚያጋጥሟቸው እነሱን በመልካም ሥነ ምግባር አንጾ ማሳደጉ አንድ ራሱን የቻለ ችግር ነው። እውነት አይደለም? የአምላክ ቃል ወላጆችን እንዲህ በማለት ያበረታታል፦ (ምሳሌ 22:6፤ 24:3)” ከዚያም ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ልጆችን ለማሠልጠንና ቤትን በጥበብ ለመገንባት በጣም እንደሚረዳ ግለጽለት። እውነተኛነትን፣ ታዛዥነትን፣ አመስጋኝነትን፣ ትሕትናን፣ ይቅር ባይነትንና ሌሎች በርካታ ጥሩ ጥሩ ጠባዮችን አስተምሯል። ከልጆችዎ ጋር ሊያነቡትና ሊወያዩበት የሚችሉት አንድ ጥሩ መጽሐፍ ላሳይዎት እወዳለሁ። ከእህትዎና ከወንድምዎ ልጆች ጋርም ሊወያዩበት ይችላሉ።” ከዚያ ታላቁ አስተማሪ የተባለውን መጽሐፍ አበርክትለት።
3 ሌላው አቀራረብ እንዲህ ሊሆን ይችላል፦
◼ “ያነጋገርናቸው ብዙ ሰዎች በዓለም ላይ እውነተኛ ፍቅር በመጥፋቱ ምክንያት ተጨንቀው አግኝተናቸዋል። ሁኔታው እርስዎን ያሳስብዎታልን? . . . ይህ የሆነበት ብዙ ምክንያት አለ። ይህ ዓይነት ሁኔታ እንደሚመጣ ደግሞ ተተንብዮ ነበር። ታዲያ ልጆቻችን ይህ ሁኔታ ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን? በመዝሙር 119:9-11 ላይ ያለውን ጥሩ አነጋገር ልብ ይበሉ። ኢየሱስም ሊጠብቁን የሚችሉ እንዲህ ያሉ ትምህርቶችን አስተምሯል። ለልጆች የተጻፈውን የዚህን መጽሐፍ ማውጫ እስቲ ይመልከቱት። . . . ”
4 “ሰው በዓለም ላይ ካለው መከራ የሚገላገልበት ጊዜ ደርሷል!” የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ለማበርከት፦
◼ “ሰው ብዙ ቢጥርም እንኳን አስተማማኝ የሆነ የወደፊት ጊዜና ዓለም አቀፍ የሆነ ደስታ ይመጣል የሚለው ተስፋ የደበዘዘው ለምን ይሆን? ብለው አስበው ያውቃሉ? . . . የአምላክ ቃል በመዝሙር 146:3, 4 ላይ ይህ የሆነበትን ምክንያት ይገልጽልናል።” ከዚያ በዚህ መጽሐፍ ተጠቅመህ አምላክ የሚሰጠው ተስፋ ምን እንደሆነ ልትገልጽለት ትችላለህ። በገጽ 8 ላይ የጊዜያችንን ሁኔታ፣ በገጽ 36 ላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊው ባለ ሥልጣን የትንቢቶቹን ትርጉም ሲረዳ የሚያሳዩትን ስዕሎች ገልጠህ ልታሳየው ትፈልግ ይሆናል።
5 “ዘላለማዊ ዓላማ” የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ለማበርከትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መግቢያ ልትጠቀም ትችላለህ። መጽሐፉን ገጽ 4 ላይ ገልጠህ አንቀጽ 2ን ልታነብለት ትችላለህ። እርግጥ ነው፣ ይህ መጽሐፍም ሆነ “ሳልቬሽን” የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ የሚበረከተው እንግሊዝኛ ማንበብ ለሚችሉ ሰዎች ነው። ለእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች አረንጓዴ ሽፋን ያለውን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በቅናሽ ዋጋ ልናበረክትላቸው እንችላለን። እነዚህ ጽሑፎች የወጡት ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ቢሆንም በየቤቱ ለምናገኛቸው ሰዎች አዲስ ከመሆናቸውም በላይ ዋጋቸውም ቀላል መሆኑን አስታውስ። እነዚህ መጽሐፎች ካርቶኖች ውስጥ ታሽጎባቸው ከሚቀመጡ ይልቅ ሰዎች ቢያገኟቸው ጥሩ ስለሆነ መጽሐፎቹን በቅንዓት አበርክት።
6 ይሖዋ እውነትን አሳውቆናል። በጽሑፍም ይሁን በቃል ይህን እውነት ለምናገኛቸው ሰዎች ለማካፈል ያለንን አጋጣሚ ሁሉ ልንጠቀምበት ይገባል። በዚህ መንገድ ለሌሎች ሰዎች ዘላለማዊ ጥቅም የሚያመጣ ትምህርት የምናስተምር የሕዝብ መምህራን መሆናችንን እናሳያለን።—ማቴ. 28:19, 20