ቤታቸው ሄደን ካላነጋገርናቸው እንዴት ይሰማሉ?
1 የመንግሥቱ ወራሾች ከሆኑት ቅቡዕ ቀሪዎች ጋር በመተባበር ከ50 ሚልዮን በላይ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ጉበኛ ሆኖ የማገልገል ኃላፊነትና መብት ተሰጥቶናል። ከነዚህም ውስጥ ከሦስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑት በዋና ከተማዋ ውስጥ እንደሚኖሩ ይገመታል። በተቻለ መጠን እነዚህ ሰዎች በሙሉ ምሥራቹንም ሆነ ማስጠንቀቂያውን መስማት ይኖርባቸዋል። (ሕዝ. 3:17-19፤ ሮሜ 10:14) ባለፉት ዓመታት ብዙዎች በመንገድ ላይ፣ በገበያ፣ በመሥሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤትና በሌሎች ቦታዎች መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በመስጠት ለመስበክ ያደረጉት ጥረት የሚያስመሰግን ነው። የተደረገው ጥረት ብዙዎች ለመስማት የሚችሉበትን አጋጣሚ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። ይህን ጥረታችንን ልንገፋበት ይገባናል። ይሁን እንጂ መልዕክቱን የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ ቤታቸው ድረስ ሄደን ልናነጋግራቸው የሚገባን ሌሎች ብዙ ሰዎችም አሉ። በመጀመሪያው ገጽ ላይ ያለው ርዕስ እንደሚለው ‘ያለ ማሰለስ ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ’ በሩ ተከፍቶልናል። ሁላችሁም በዚህ ፍሬያማ የሆነ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ጊዜ እንድትመድቡ እናበረታታችኋለን።
2 ከቤት ወደ ቤት ሄዶ ስለማገልገል አፍራሽ የሆነ አመለካከት አትያዙ። (መክ. 11:4) አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚያጋጥሙን ምንም አያጠራጥርም፤ ይሁን እንጂ በመንገድ ላይስ ተቃዋሚዎች ያጋጥሙን የለም? አንዳንድ ጊዜ ሊረብሹን የሚፈልጉ ሰዎች ተሰብስበው ያሾፉብን ይሆናል፤ ሆኖም በመንገድ ላይም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ያጋጥሙናል። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንደሚገባን መማር እንችላለን።
3 እስቲ በጥሩ ጎኑ ያሉትን ጥቅሞች ደግሞ አስቡ፦ 1. ብዙ ጊዜ ከቤት ስለማይወጡ ሌላ ቦታ ልናገኛቸው የማንችላቸውን ሰዎች አግኝተን ልንሰብክላቸው እንችላለን። 2. በደንብ ያዳመጠንን ሰው አድራሻ ለማወቅ አንቸገርም። 3. ብዙውን ጊዜያችንንም በመመሥከር እናሳልፈዋለን። በመንገድ ላይ በምንሠራበት ጊዜ ግን አብዛኛው ጊዜ የሚባክነው በመጓዝና ሰው እስኪመጣ በመጠበቅ ነው። 4. በመጽሐፍ ቅዱስና በጽሑፎች በደንብ ለመጠቀም እንችላለን፤ ሰው በሚበዛበት መንገድ ላይ ግን እንዲህ ለማድረግ አያመችም። 5. ሕጋዊ እውቅና በማግኘታችን በተከፈተልን በዚህ ሰፊ የሥራ በር እንድንገባ ለቀረበልን ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠታችን እርካታ እናገኛለን። (ማቴ. 5:14-16) 6. ያለ ምንም አድልዎ በእያንዳንዱ ቤት ያሉ ሰዎች መልዕክቱን የመስማት ወይም በጽሑፍ የማንበብ አጋጣሚ ያገኛሉ። 7. ክርስቶስና የመጀመሪያ ተከታዮቹ ከቤት ወደ ቤት ይሄዱ እንደነበረ ሁሉ እኛም እንዲሁ በማድረግ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናሳውቃለን። (1 ቆሮ. 11:1) 8. ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚሰብኩ ወንድሞችን ካቀፈው ዓለም አቀፍ ማኅበር ጋር ያለንን አንድነት እናሳያለን፤ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በዚህ የታወቁ ናቸው። (1 ጴጥ. 5:9 አዓት)9. አዘውትረን ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የአገልግሎት ክልላችንን መሸፈናችን ለሁሉም ሰው፣ በሩቁ ለሚመለከቱን ተቃዋሚዎቻችን እንኳን ሳይቀር፣ ጥሩ ምሥክርነት ይሆናል። (1 ቆሮ. 4:9) 10. ሐዋርያው ጳውሎስ በሥራ 20:20, 21 እና 26 ላይ እንዳለው የምሥክርነቱን ሥራ ሙሉ በሙሉ እንዳከናወንንና ከሰው ሁሉ ደም ነፃ እንደሆንን አፋችንን ሞልተን ለመናገር ያስችለናል።
4 የክልል የበላይ ተመልካቾች በጉብኝታቸው ጊዜ፣ በተለይ ጥሩ የአገልግሎት ክልል አመዳደብ ባለባቸው ጉባኤዎች ውስጥ፣ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎችን በማነጋገራቸው እንደተደሰቱ ሪፖርት አድርገዋል። ከቤት ወደ ቤት በጥሩ ሁኔታ የሚያገለግሉ አስፋፊዎች ይበልጥ ውጤታማ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ካሉት አቅኚዎች ውስጥ ብዙዎቹ ከመንገድ ወደ መንገድ ብቻ የሚሠሩ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ያሏቸው ጥናቶች አንድ ወይም ሁለት ብቻ ነው። በዚያው ጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ አቅኚ ግን እንዴት አሥራ ሁለት ጥናቶች ሊኖሩት እንደቻለ ተጠይቆ ሲመልስ “ብዙ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት አገለግላለሁ። ጥናቶቼን ያገኘኋቸው በዚህ መንገድ ነው!” በማለት በግልጽ ተናግሯል። አዎን፣ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ሰዎች እንዲሰሙ ያደርጋል። እኛም የማገልገል ስሜታችን እንዳይዳከም ወይም አገልግሎታችን አሰልቺ እንዳይሆንብን ይረዳናል። እድገት የምናደርግ እንድንሆን ይረዳናል።
5 ረብሻ የሚፈጥሩ ተቃዋሚዎች ቢያጋጥሙንስ ምን ለማድረግ እንችላለን? ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ከመጨነቅ ይልቅ አምላክ ጥበብና ሰላም ይሰጠን ዘንድ እንድንጸልይ ያበረታታናል። 2 ጢሞቴዎስ 2:24 ደግሞ ከክርክር እንድንርቅ ይነግረናል። በለዘበ አንደበት (ምሳሌ 25:15) ‘ደህና ዋል’ ብለነው ልንሄድ እንችላለን። (ከምሳሌ 26:20 ጋር አወዳድር።) በምሳሌ 22:3 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት እዚህ ላይ ይሠራል። ስለ ሃይማኖት ሲነሣ የሚናደዱ ሰዎች ያሉበትን አካባቢ ትተን ልንሄድ ወይም በዚያ አካባቢ መሥራታችንን ልናቆም እንችላለን። በአንድ ግቢ ውስጥ ብዙ ቤቶች ካሉ በቀን አንድ ቤት አንኳክተን አጭር ምሥክርነት ከሰጠን ወይም መጽሔት ካበረከትን ሊበቃን ይችላል። ምናልባትም ሌሎች አስፋፊዎች ደግሞ በሌላ ቀን መጥተው በዚያው ግቢ ውስጥ ያለ አንድ ሌላ ቤት አንኳኩተው እንደኛው እንዲያደርጉ ዝግጅት ልናደርግ እንችላለን። በዚህ ሁሉ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹና የአገልግሎት ክልል አገልጋዩ እንዲሁም የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች ጥሩ የአገልግሎት ክልል ቅንጅት እንዲኖር በማድረግ ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
6 ሰዎች ሁሉ ሊሰሙ እንዲሁም በግ መሰል ሰዎች ሊገኙ ይችሉ ዘንድ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የአገልግሎት ክልላችንን በደንብ አጣርተን መሸፈንን ጨምሮ በሁሉም ዓይነት የአገልግሎት መንገዶች ብንጠቀም የምናገኘው በረከት ይጨምራል፤ ደስታችንም ታላቅ ይሆናል።—1 ጢሞ. 4:16