ለሁሉም ሰው የሚሆን ልዩ የመንግሥት ዜና
1 የዓለም ሁኔታ የሚያሳስባቸውን በሁሉም ቦታ የሚገኙ ሰዎች ፍላጎት የሚቀሰቅስ ልዩ የመንግሥት ዜና ከሚያዝያ 24 ጀምሮ በዘመቻ መልክ በማሰራጨት ላይ እንገኛለን! መልእክቱ ወቅታዊ ብቻ ሳይሆን አጣዳፊም ነው። በሁሉም ጉባኤዎች የሚገኙ አስፋፊዎች ይህ መልእክት በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች እጅ እንዲገባ ለማድረግ ከልብ እየጣሩ ናቸው። አንተስ የተሟላ ተሳትፎ እንዲኖርህ እየጣርክ ነውን?
2 ለሁሉም ጉባኤዎች ለእያንዳንዱ አስፋፊ 50 ለእያንዳንዱ አቅኚ ደግሞ 100 የሚያህሉ የመንግሥት ዜና ተልኳል። ከዚህ ውስጥ ምን ያህል ለማሰራጨት ችለሃል? በመጀመሪያ ተስፋ ያደረከውን ያህል ማሰራጨት ካልቻልክ ስርጭቱ በግንቦት 14 ከማብቃቱ በፊት የበለጠ ለማከናወን ስለሚያስችሉ ዘዴዎች በጥንቃቄ አስበሃል? ረዳት አቅኚ ሆነህ ብታገለግልስ? በአመሻሹ ላይ ምሥክርነት ለመስጠት እንዲያስችል በሳምንቱ መካከል በተቋቋሙ ተጨማሪ የአገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ትችላለህን?
3 ሽማግሌዎች የአገልግሎት ክልሎች እንደታቀደው መሸፈን አለመሸፈናቸውን በጥንቃቄ ይመረምራሉ። አንድ ጉባኤ አስቀድሞ ከተሰጠው ክልል ውስጥ የተወሰኑ ክፍሎችን መሸፈን የማይችል ከሆነ ሽማግሌዎች ከጎረቤት ጉባኤ እርዳታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። የእኛ ልባዊ ጥረትና በጉባኤዎች መካከል የሚኖረው ጥሩ ትብብር ሥራው በሚገባ እንዲከናወን አስተዋጽኦ ያደርጋል።
4 አዳዲስ አስፋፊዎችንና ልጆችን ጨምሮ ብዙዎች በዚህ ሥራ መካፈል በመቻላቸው ተጨማሪ ደስታ እንዳመጣልህ አያጠራጥርም። ጥሩ ምላሽ ያሳዩትን ሰዎች ተመልሰው ሄደው እንዲጠይቁ በማበረታታት ይህ የደስታ መንፈስ እንዳለ እንደሚቀጥል ተስፋ አለን። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ስም የምንይዝበትን ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽ በትክክል እንድንጠቀምበት በጥብቅ ተመክረናል። ከግንቦት አጋማሽ በኋላ ባሉት ቀናት አዳዲስ ጥናቶችን ለማግኘት ግብ በማድረግ በተመላልሶ መጠየቆች ላይ ትኩረት የምናደርግበት ጥሩ ጊዜ ይሆንልናል።
5 ተመልሰን በምንሄድበት ጊዜ ምን ብለን ለመናገር እንችላለን? እንዲህ ብሎ መናገር ውጤታማ ሆኖ ታገኘው ይሆናል:- “በቅርብ ጊዜ ሰጥቼዎ የነበረውን ጽሑፍ ያስታውሱ ይሆናል፤ ጽሑፉን ለማንበብና በጉዳዩ ላይ ለማሰላሰል አጋጣሚ እንዳገኙ ተስፋ አደርጋለሁ። መልእክቱ በጠቅላላው የሰው ዘር ፊት ላይ የተጋረጡትን አንገብጋቢ ጉዳዮች ይዳስሳል።” በሁለተኛው ገጽ ላይ የሚገኙ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ዓረፍተ ነገሮችን አንብብና ከዚያ እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- “ወደፊት ለሚመጣው ነገር ራሳችንን ለማዘጋጀት ምን ማድረግ ያስፈልገናል ብለው ያስባሉ?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ሰውዬው ፍላጎት ካሳየ ከመንግሥት ዜና በገጽ 2–4 ላይ ባሉት ነጥቦች አወያየውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርለት ጋብዘው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ካልሆነ በቅርቡ የወጣውን መጽሔት አበርክትለት።
6 በሌላ ጉባኤ ክልል አገልግለህ ከነበረ በዚያ ጉባኤ ያሉ አስፋፊዎች ተመላልሶ መጠየቆችን ለማድረግ እንዲችሉ ያገኘሃቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ስም መስጠት እንዳለብህ አትዘንጋ። በተመሳሳይም አንዳንድ ተመላልሶ መጠየቆችን እንድታደርግ ከተሰጠህ ፈጥነህ ተመልሰህ ከመሄድ አትዘግይ።
7 ይህን የመንግሥት ዜና ልዩ በሆነ መንገድ የማሰራጨቱ ሥራ ከፍተኛ ደስታ ከመፍጠሩም በላይ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ያለንን ጥረት በበለጠ እንድናጠናክር አነሳስቶናል። ይህ ትልቅ ስኬት እንደሆነና በሁሉም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች የይሖዋን ታላቅ ስምና ዓላማ ይበልጥ እንዲገነዘቡ እንዳደረጋቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳ. 12:4, 5) ብዙ ሥራ ባከናወንን መጠን ደስታችንም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ይሆናል።—መዝ. 126:3