የመንግሥት ዜና ተበርክቶላቸው ፍላጎት ያሳዩትን ተከታትላችሁ እርዱ
1 ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ “ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?” የሚል ርዕስ ያለውን የመንግሥት ዜና ቁ. 35ን የማሰራጨት መብት አግኝተናል። በሁሉም ቦታ ያሉ አስፋፊዎች ይህን የመንግሥት ዜና እትም መልእክቱ ለሚገባቸው ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ አቅማቸው በፈቀደ መጠን እየጣሩ ነው። (ማቴ. 10:11) ምንም እንኳ ዘመቻው የሚያበቃው እሁድ ኅዳር 16 ቢሆንም ገና መሸፈን ያለበት ክልል ካለ ለጉባኤው የተላከው የመንግሥት ዜና ቁ. 35 እስኪያልቅ ድረስ ማሰራጨታችሁን እንድትቀጥሉ የጉባኤያችሁ ሽማግሌዎች ይጠይቋችሁ ይሆናል።
2 ይህ የመንግሥት ዜና እትም የብዙ ሰዎችን ፍላጎት ቀስቅሷል። እነዚህ ሰዎች የሰው ዘር ባጠቃላይ የተፈጥሮ ፍቅር ማጣቱን ከመገንዘባቸው የተነሳ ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን ብለው ያስባሉ። (2 ጢሞ. 3:3) በዘመቻው አማካኝነት ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ተከታትለን ለመርዳት እንፈልጋለን።
3 የመንግሥት ዜና ውጤት እያስገኘ ነው፦ በ1995 በተደረገው የመንግሥት ዜና ስርጭት ዘመቻ ወቅት አንድ ቅጂ የደረሳት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው እንደሚያምኑ በይበልጥ ለመረዳት ስለፈለገች በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘች። ስብሰባው ላይ በተገኘችበት ዕለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ያለማንገራገር የተስማማች ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ አዘውትራ በስብሰባዎች ላይ ትገኝ ነበር። ብዙም ሳትቆይ በፊት አባል ለነበረችበት ቤተ ክርስቲያን ደብዳቤ ጽፋ ከአባልነት እንዲሰርዟት ጠየቀች!
4 እስካሁን ድረስ በክልላችን ውስጥ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥት ዜና ቁ. 35 የያዘውን መልእክት አንብበዋል። ሆኖም ለመልእክቱ የሰጡት ምላሽ ምንድን ነው? አብዛኞቹ ያነበቡት ነገር አድናቆት ያሳደረባቸው በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ ተመልሶ ካላነጋገራቸው በስተቀር እርምጃ አይወስዱም። ተመልሰህ ለመሄድ አቅደሃል? ለሰዎች ያለን ፍቅራዊ አሳቢነት ይህን ለማድረግ ሊያነሳሳን ይገባል። የመንግሥት ዜና ፍላጎት ያሳደረባቸውን ሰዎች ሁሉ ተመልሶ ማነጋገር ያስፈልጋል።
5 ተመልሰህ በምትሄድበት ጊዜ ምን ለማለት ትችላለህ? የመንግሥት ዜና ስለያዘው መልእክት ወቅታዊነት ጥቂት ሐሳቦች ከሰነዘርህ በኋላ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ አንድ ጥያቄ ጠይቅ። የቤቱ ባለቤት ሐሳቡን በሚገልጽበት ጊዜ በአእምሮው የያዘው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ እንድትችል በጥሞና አዳምጥ። ከዚህ በኋላ በመንግሥት ዜና ውስጥ በተጠቀሰው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር ላይ የሚገኝ ተመሳሳይ ሐሳብ ጥቀስ። ጥሩ ምላሽ ካገኘህ ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ሞክር።
6 “የመንግሥት ዜና” ቁ. 35 ፍላጎት ያሳደረባቸውን ሰዎች ተመልሳችሁ በምታነጋግሩበት ጊዜ ልትጠቀሙባቸው የምትችሉ አንዳንድ አቀራረቦች ቀጥሎ ቀርበዋል:-
◼ “በቅርቡ አንድ ትራክት ትቼልዎት እንደነበር ያስታውሱ ይሆናል። ትራክቱ በዛሬው ጊዜ የሰውን ዘር በመከፋፈል ላይ ስላለ አሳሳቢ ጉዳይ ይናገራል። ዛሬ ሰዎች ለሌሎች ፍቅር የላቸውም።” የመንግሥት ዜና ገጽ 2 ላይ “የጎረቤት ፍቅር ቀዝቅዟል” በሚለው ርዕስ ስር በቀረበው ማስረጃ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ከዚህ በመቀጠል “የአምላክ ዓላማ የሰው ዘር በዚህ መንገድ እንዲኖር ይመስልዎታል?” ብለህ ጠይቅ። መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር ላይ ትምህርት 5ን አውጥተህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ጥረት አድርግ።
◼ “መጀመሪያ በተገናኘንበት ጊዜ ‘ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?’ የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ሰጥቼዎት ነበር። ይህን የመሰለ ዓለም ሊመጣ የሚችል ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር ትምህርት 6ን ገልጠህ አንቀጽ 6ን አንብብ። ቀጥሎም በሚክያስ 4:3, 4 ላይ የሚገኘውን አምላክ የሰጠውን ተስፋ አንብብ። የቤቱ ባለቤት ፍላጎት ካሳየ ብሮሹሩን እንዲወስድና ጥናት እንዲጀምር ሐሳብ አቅርብለት።
◼ “ባለፈው የመጣሁ ጊዜ ‘ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?’ የሚል ርዕስ ያለው ትራክት ትቼልዎት ነበር። ትራክቱ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በነፃ እንዲመራልዎት ግብዣ ያቀርባል። ተመልሼ የመጣሁት መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የምንጠቀምበትን ጽሑፍ ላሳይዎት ነው። [እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አሳየው።] ይህ መጽሐፍ ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱበት ጊዜ መቼ እንደሚመጣ በግልጽ ያብራራል። ለሌሎች ጥያቄዎችም መልስ ይሰጣል፤ እነዚህ ጥያቄዎች እርስዎን ሲያሳስቡዎ የቆዩ ሊሆኑ ይችላሉ:- የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው? አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ? በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ?” ከዚህ በኋላ “ጥናቱ እንዴት እንደሚካሄድ ላሳይዎ?” ብለህ ጠይቀው። የቤቱ ባለቤት ማጥናት እንደማይፈልግ ከገለጸ መጽሐፉን በግሉ ማንበብ ይፈልግ እንደሆነ ጠይቀው። ፈቃደኛ ከሆነ የተለመደውን የአስተዋፅኦ ዋጋ እንዲከፍል በማድረግ አንድ ቅጂ ትተህለት ሂድ። ተመልሰህ ለመሄድ ዕቅድ አውጣ።
7 የመንግሥት ዜና ቁ. 35ን በማሰራጨት የአገልግሎት ክልሉን አጣርተን ከሸፈንን በኋላ በቀሪው የወሩ ቀናት እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ማበርከት እንችላለን። ይህን መጽሐፍ ለማበርከት የሚያስችሉ በርካታ አቀራረቦች በመጋቢት፣ በሰኔና በኅዳር 1996 እንዲሁም በሰኔ 1997 የመንግሥት አገልግሎታችን እትሞች የመጨረሻ ገጾች ላይ ቀርበዋል።
8 ይህ ልዩ የሆነ የመንግሥት ዜና ስርጭት በስብከቱ ሥራ የምናደርገውን ጥረት እንድንጨምር ሁላችንንም ሊገፋፋን ይገባል። የሰው ዘር እርስ በርሱ ተፋቅሮ እንዲኖር የአምላክ ዓላማ መሆኑን በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች ማወቅ እንዲችሉ በመርዳት ይህ ዘመቻ በይሖዋ እገዛ ግቡን እንደሚመታ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። የመንግሥት ዜና ተበርክቶላቸው ፍላጎት ያሳዩትን ሁሉ ተከታትለን በምንረዳበት ጊዜ ትጋት የተሞላበት ጥረታችንን ይሖዋ መባረኩን እንዲቀጥል ምኞታችን ነው።