በመንግሥት ዜና ቁ. 36 አማካኝነት የተቀሰቀሰው የሰዎች ፍላጎት እንዲያድግ ማድረግ
1 የደረሰህን የመንግሥት ዜና ቁ. 36 አሰራጭተህ ጨርሰሃል? ይህ የመንግሥት ዜና “አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞልሃል?” የሚል ሁሉንም ሰው የሚያሳስብ ወቅታዊ ጥያቄ ያነሳል። 2000 ዓመት በተቃረበበት ወቅት በአዲሱ ሺህ ዓመት የተለያዩ ነገሮች ይከሰታሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። የመንግሥት ዜና ቁ. 36 ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን ከጠቀሰ በኋላ የዓለም ሁኔታ ወደፊት ጥሩ ነገር ይመጣል የሚል አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ የሚያደርግ እንዳልሆነ ይገልጻል። ብዙ ሰዎች የሚናፍቁት ሰላምና ደህንነት የሚመጣው ክርስቶስ ኢየሱስ በሚገዛበት ሺህ ዓመት ብቻ ነው። መንግሥቱ እውን እንደሆነ ያለን ሙሉ ትምክህት የመንግሥት ዜና ቁ. 36ን በተቻለ መጠን ለእያንዳንዱ ሰው እንድናሰራጭ ይገፋፋናል።
2 በመንግሥት ዜና ስርጭት የተገኘ አዎንታዊ ምላሽ:- ከዚህ ቀደም የተከናወኑት የመንግሥት ዜና ስርጭቶች ለስብከት ሥራችን ጥሩ ማነቃቂያ ሆነውልን ነበር። ካናዳ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የመንግሥት ዜና ቁ. 35ን አስመልክቶ ሲጽፍ “አስፋፊዎችና አቅኚዎች በመስኩ ላይ በማገልገል ለዚህ ልዩ ዘመቻ ልባዊ ድጋፍ የሰጡ ሲሆን ብዙ አበረታች ተሞክሮዎችም ተገኝተዋል” ብሎ ነበር። እናንተም የመንግሥት ዜና ቁ. 36ን በማሰራጨቱ ዘመቻ ተመሳሳይ ቅንዓት የተሞላበት ተሳትፎ እንዳደረጋችሁ ምንም ጥርጥር የለውም።
3 ይህንን የመንግሥት ዜና የማሰራጨቱን ዘመቻ ኅዳር 17, 2000 ለማጠናቀቅ ታቅዷል። ለጉባኤያችሁ የተመደበውን የአገልግሎት ክልል ሙሉ በሙሉ ሸፍናችኋል? ካልሸፈናችሁ ሽማግሌዎች ዘመቻውን እስከ ኅዳር መጨረሻ ድረስ እንድትቀጥሉ ይጠይቋችሁ ይሆናል።
4 በጉባኤያችሁ የመንግሥት ዜና ቁ. 36 ሥርጭትን በተመለከተ የሰዎች ምላሽ ምን ይመስላል? አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር እንዲላክላቸው እና/ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላቸው ለመጠየቅ ቅጹን ሞልተው የሚልኩ ከስንት አንድ ናቸው። ይሁን እንጂ ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ፍላጎት ያሳዩ አብዛኞቹ ሰዎች አንድ የይሖዋ ምሥክር ተመልሶ እስካላነጋገራቸው ድረስ ምንም እርምጃ ላይወስዱ ይችላሉ። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በሙሉ እንደገና መጠየቅ ይገባል። ይህ መቼ ቢደረግ የተሻለ ነው? በተቻለ መጠን ቶሎ ተመልሰን ክትትል ልናደርግላቸው ይገባል።
5 የመንግሥት ዜና ቁ. 35 ከተበረከተ በኋላ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ የተገኙትን የሚከተሉትን ተሞክሮዎች ተመልከት። በአየርላንድ የምትኖር አቅኚ ለአንዲት የምግብ ቤት ባለቤት የመንግሥት ዜና አበረከተችላት። ሴትዬዋ ትራክቱ በያዘው መልእክት በጣም ስለተደነቀች ሌላ ጊዜ እንድትመጣ እህትን ጠየቀቻት። እህት ከሁለት ቀን በኋላ ተመልሳ ሄደችና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። በዴንማርክ ደግሞ አንድ ቤት ውስጥ ማንም ሰው ስላልነበረ ወንድሞች የመንግሥት ዜና ትተው ሄዱ። በዚያው ዕለት እዚያ ቤት ነዋሪ የሆነች ሴት ቅጹን ሞልታ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮ የላከች ሲሆን ቅርንጫፍ ቢሮው ደግሞ በአቅራቢያው ለሚገኝ ጉባኤ ላከው። በዚያው ሳምንት ውስጥ ሁለት እህቶች ሄደው አነጋገሯት፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ዝግጅት ተደረገላት፤ እንዲሁም ሴትየዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘች!
6 ተመልሰህ ስትሄድ ምን ልትል ትችላለህ? የመንግሥት ዜና ካበረከትን በኋላ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀላልና አስደሳች የሆነ የአገልግሎታችን ክፍል ነው። ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበት ጊዜ ለቤቱ ባለቤት የተሰጠው ቅጂ በቅርብ ላይገኝ ስለሚችል አንድ የመንግሥት ዜና ቁ. 36 ይዞ መሄድ ጥሩ ነው። የሚከተለውን አቀራረብ ልትሞክር ትችላለህ።
7 ማንነትህን ለቤቱ ባለቤት ካስታወስክ በኋላ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ‘አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?’ የሚል ትራክት ሰጥቼዎት ነበር። የክርስቶስ ኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት በቅርቡ እንደሚጀምርና ምድርን ወደ ገነትነት እንደሚለውጣት ማንበቡ የሚያጽናና አይደለም? [በመንግሥት ዜና ቁ. 36 ላይ የሚገኙትን ሥዕላዊ መግለጫዎች አሳየው።] በመጨረሻው ገጽ ላይ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚል ብሮሹር እንዲላክልዎ መጠየቅ እንደሚችሉ ይናገራል።” ብሮሹሩን አሳየው፣ ትምህርት 5ን ገልጠህ የመጀመሪያውን ጥያቄ እንዲሁም አንቀጽ 1ን እና 2ን ከአነበብክ በኋላ የቤቱ ባለቤት ሐሳብ እንዲሰጥ ጋብዘው። አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶችን አንብብና አብራራ። የሚቻል ከሆነ በሌላኛው ጥያቄና አንቀጽ ላይ ተወያዩ፤ ከዚያም በሌላ ጊዜ ተመልሰህ ለመምጣትና ውይይቱን ለመቀጠል ጊዜ ወስኑ።
8 በኅዳር ወር ከዘመቻው ቀጥሎ የሚበረከተው “አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ” የተባለው ብሮሹር ወይም “እውቀት ” መጽሐፍ ስለሆነ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ‘አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?’ የሚል ትራክት ሰጥቼዎት ነበር። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልዎ የሚፈልጉ ከሆነ መጠየቅ እንደሚችሉ ይናገራል። ዛሬ የመጣሁት ለጥናት የምንጠቀምበትን ጽሑፍ ላሳይዎት ነው። [አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር የመጨረሻ ገጽ አሳየው ወይም ከእውቀት መጽሐፍ ገጽ 188-9ን አሳየው።] በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው ሺህ ዓመት በዚህ ሥዕል ላይ የተገለጸውን የሚመስል ሁኔታ ያመጣል። በገነት ውስጥ ሕይወት ከሚያገኙት ሰዎች መካከል ለመሆን አምላክ የሚሰጠውን ትክክለኛ እውቀት መቅሰም አስፈላጊ ነው። ፈቃድዎ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንደምናጠና በአጭሩ ላሳይዎ እችላለሁ።”
9 የመንግሥት ዜና ቁ. 36 ስርጭት ታላቅ ምሥክርነት እንድንሰጥ በማስቻል በአገልግሎቱ ያለንን ተሳትፎ ከፍ አድርጎልናል። ዘመቻው በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የብዙ ሰዎችን ፍላጎት እንደቀሰቀሰ ጥርጥር የለውም። ይህንን ፍላጎት ለማሳደግ ሁላችንም የምናደርገው የተቀናጀ ጥረት የይሖዋ እርዳታ ሲታከልበት ተጨማሪ በግ መሰል ሰዎች ለማግኘት ያስችለናል።—ማቴ. 10:11፤ ሥራ 13:48, 49, 52