ብሮሹር ላበረከታችሁላቸው ሁሉ ተመላልሶ መጠየቅ አድርጉላቸው
1 ‘እንደገና ስለ እርሱ በማሰባቸው’ ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ሰዎችን አመስግኗቸዋል። (ፊልጵ. 4:10) የእነርሱን ምሳሌ ለመስክ አገልግሎት ሞዴል አድርገን ከተጠቀምንበት፣ ስለ መሰከርንላቸው ሰዎች ‘እንደገና ከማሰባችንም’ በተጨማሪ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ እንገፋፋለን።
2 “የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች” የሚለውን ብሮሹር አበርክታችሁ ከነበረ እንደዚህ ማለት ትችላላችሁ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ስላደረግነው ውይይት ሳሰላስል ነበር፤ ወደ አእምሮዬ የመጡትን ሁለት ጥቅሶች ላካፍልዎት እፈልጋለሁ። አምላክ የምድርን አገዛዝ በራሱ ቁጥጥር ሥር እንደሚያደርግ ተነጋግረን እንደነበረ ያስታውሱ ይሆናል። ይህ እንደሚፈጸም ይሖዋ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል ገብቷል። [ዳንኤል 2:44ን አንብብ።] ይህ በእርግጥ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ የገባውን ቃል በመፈጸም ረገድ ስላለው ችሎታ ምን እንዳለ ልብ ይበሉ። [ኢሳይያስ 55:11ን አንብብ።] ይህ በአምላክ መንግሥት ላይ እምነታችንን እንድንጥል ሊያበረታታን አይገባምን? ነገር ግን አምላክ የገባውን ቃል የሚፈጽመው መቼ ይሆን?” ይህንን ጥያቄ በሚቀጥለው ጊዜ ስትመጣ እንደምትመልስለት ንገረው።
3 “የምትወዱት ሰው ሲሞት” የሚለውን ብሮሹር ለወሰደ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርጉለት ይህንን አቀራረብ ልትጠቀሙ ትችላላችሁ:-
◼ “አንድን ሰው በሞት ማጣትን በተመለከተ ያደረግነውን ውይይት ግምት ውስጥ በማስገባት ተመልሼ ለመምጣት ልዩ ጥረት እድርጌአለሁ።” የሚከተለውን በምትናገርበት ጊዜ ገጽ 30 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየው:- “ሰዎች ከሞት ሲነሱና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር እንደገና ሲገናኙ የሚያሳየውን ይህንን አስደሳች ሥዕል ያስታውሱታል? ይህ ሁኔታ የሚከናወነው ሰማይ ነው ወይስ ምድር ብዬ ጠይቄዎት ነበር። ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ በዚህ ብሮሹር ገጽ 26 ላይ አግኝተውት ይሆናል።” ከሦስተኛው አንቀጽ እስከ አምስተኛው አንቀጽ ውስጥ ባሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ተወያዩ፤ በተጨማሪም ዮሐንስ 5:21, 28, 29ን አንብብ። ጊዜ በፈቀደልህ መጠን በገጹ ላይ የቀሩትን ሁሉንም ጥቅሶች አንብብ።
4 “በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር!” በተባለው ብሮሹር አማካኝነት ጥናት ማስጀመር ትችላላችሁ?
◼ ስለ ሞት በሚያብራራው ርዕሰ ጉዳይ (ሥዕል 8–17) ውይይት መጀመር ትችላለህ ወይም እንደሚከተለው ብለህ በመጠየቅ በሽፋኑ ሥዕል መጠቀም ትችላለህ:- “በዚህ ሥዕል ላይ በሚታየው ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ቢጠየቁ ግብዣውን ይቀበሉት ነበር?” (በተጨማሪም [ወይም በዚህ ምትክ] በሥዕል 47 እና 49 መጠቀም ትችላለህ።) ከዚያም ዮሐንስ 17:3ን ጥቀስና ስለ ፈጣሪያችን ይበልጥ ማወቅ እንዳለብን ጠበቅ አድርገህ ግለጽ። የመጀመሪያውን ሥዕል አውጣና አንደኛውንና ሁለተኛውን ሐሳብ አንብብለት። ሁኔታዎች የሚፈቅዱልህ ከሆነ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አንብብና እስከ ሥዕል 4 እና 5 ድረስ ቀጥል። በሚቀጥለው ጊዜ ለምታደርገው ተመላልሶ መጠየቅ ሁኔታዎችን አመቻች። ጥናቱ የሚቀጥል መስሎ ከታየህ ከሦስተኛው ተመላልሶ መጠየቅ በኋላ አዲስ ጥናት ሪፖርት ማድረግ ትችላለህ!
5 “ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም” በተባለው ብሮሹር አማካኝነት በሚከተለው መንገድ እንደገና ውይይት መጀመር ትችላላችሁ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳይቼዎት ነበር። የይሖዋን ስም ማወቅና በስሙ መጠቀም የአምልኮታችን ዋነኛ ክፍል ነው።” ገጽ 31 አውጥተህ በመጨረሻዎቹ አራት አንቀጾች ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ከልስና ዮሐንስ 17:3ን እና ሚክያስ 4:5ን አንብብ። ሰዎች የአምላክ ስም በትክክለኛው መንገድ የሚቀደሰው እንዴት እንደሆነና ገነት በሆነችው ምድር ላይ የሚኖሩትን በረከቶች እንዴት ማግኘት እንደምንችል የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደምናደርግላቸው ንገረው።
6 ስለዚህ ያነጋገራችኋቸውን ሰዎች እንደገና አስቧቸው። ሳታቋርጡ ተመልሳችሁ በመሄድ አነጋግሯቸው፤ በተጨማሪም የምታካፍሏቸውን ጠቃሚ ነገር ተዘጋጅታችሁ ሂዱ። አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን በማስገኘት ‘ፍሬ የምታፈሩ’ መሆን ትችላላችሁ።— ማቴ. 13:23