መልካም ፍሬ የሚያስገኙ ተመላልሶ መጠየቆች
ውጤታማ የማስተማር ችሎታ ይጠይቃሉ
1 ተመላልሶ መጠየቆች የመስክ አገልግሎታችን አስፈላጊና አስደሳች ክፍል ናቸው። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሶ በማነጋገር በኩል ትጉዎች መሆን ያለብን ለምንድን ነው? የይሖዋ ስም የሚታወቀውና የሚከበረው፣ እንዲሁም አምላክን የሚፈሩ ሰዎች ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ለማግኘት የሚችሉት በዚህ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ አማካኝነት ስለሆነ ነው። (2 ቆሮ. 2:17 እስከ 3:3) ተመላልሶ መጠየቅ የይሖዋን ስም መቀደስና የሌሎችን ሕይወት የሚመለከት መሆኑን መገንዘባችን ተመልሰን ከመሄዳችን በፊት ጥሩ ዝግጅት እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል።
2 ጥሩ አስተማሪ አስቀድሞ በተጣለው መሠረት ላይ እንዲገነባ ተማሪውን ይረዳዋል። አንድ አስተማሪ ተማሪው ከጊዜ ወደ ጊዜ ባገኘው እውቀት ላይ እየገነባ እንደሚሄድ ሁሉ እኛም መጀመሪያ ያነጋገርነውን ሰው ተመልሰን ስንጠይቅ ብዙውን ጊዜ በተነጋገርንበት ርዕስ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ መስጠት ይኖርብናል። ይህም ሐሳቡ የተያያዘ እንዲሆንና የሰውዬው አስተሳሰብ እየሰፋ እንዲሄድ ያስችላል።
3 “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?” የተባለውን ብሮሹር ላበረከትክለት ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ የሚከተለውን መግቢያ ውጤታማ ሆኖ ታገኘው ይሆናል:-
◼ “ጤና ይስጥልኝ! እንደገና በመገናኘታችን ተደስቻለሁ። ባለፈው ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ‘የመጨረሻ ቀናት’ እና ለእኛ ምን ትርጉም እንዳላቸው ተወያይተን ነበር። በመጨረሻ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር እንዴት እናውቃለን ብለው ራስዎን ጠይቀው ይሆናል። (2 ጢሞ. 3:1) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ጓጉተው ነበር። [ማቴዎስ 24:3ን አንብብ።] ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ በዛሬው ጊዜ የምናያቸውን ሁኔታዎች ገልጿል። እነዚህም ሁኔታዎች ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ጭንቀትንና ዓመፅን ይጨምራሉ።” በገጽ 19 እና 20 አንቀጽ 3 እና 4 ላይ የተገለጸውን የጥምር ምልክቱን አንድ ክፍል አሳየው። ሰውዬው ጥሩ ፍላጎት ካሳየ በገጽ 20 እና 21 አንቀጽ 5–8 ላይ ያሉትን የጥምር ምልክቱን ሌሎች ክፍሎች አሳየው። ሌላ ጊዜ ተመልሰህ በመምጣት በብሮሹሩ ሽፋን ላይ የተነሱትን ጥያቄዎች ልትመልስለት እንደምትፈልግ ንገረው።
4 “የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴት ልታውቀው ትችላለህ?” በተባለው ብሮሹር አማካኝነት እንዲህ በማለት ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ትችላለህ:-
◼ “የመኖራችንን ዓላማ በተመለከተ ያደረግነውን ውይይት እንደገና ለመቀጠል ጓጉቼ ነበር። በዛሬው ጊዜ ከምንኖርበት በጣም አስጨናቂ ሁኔታ በተለየ መንገድ ደስታና ሰላም በሰፈነባቸው ሁኔታዎች ሥር እዚህ ምድር ላይ እንድንኖር አምላክ ዓላማ እንደነበረው ሁለታችንም የምንስማማ ይመስለኛል። የገባውን ቃል የሚፈጽም ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ኢሳይያስ 55:11ን አንብብና በገጽ 30 ከአንቀጽ 25–27 ላይ የተሰጡትን ሐሳቦች ተወያዩባቸው። ጠቃሚ የሆነውን የሕይወት ዓላማ ለማግኘት ከሁሉ የተሻለው መንገድ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ እንደሆነ ግለጽለት።
5 “በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር!” በተባለው ብሮሹር አማካኝነት ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ተመላልሶ ስትጠይቅ ብሮሹሩን እንደገና በማሳየት እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “በዚህ ብሮሹር ሽፋን ላይ ስለሚታየው የተዋበ ዓለም ተነጋግረን ነበር። እዚህ ውስጥ ለመኖር ለሚፈልጉ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ልነግርዎት እፈልጋለሁ።” ሥዕል 41ን አውጣና ኢሳይያስ 9:6ን አንብብ። ሥዕል 62ን አሳየውና ታዛዥ የመሆንን አስፈላጊነት በማጥበቅ ዮሐንስ 3:16ን አንብብ። የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናትና የሚሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት በማድረግ እምነት ማሳየት የሚቻልበትን መንገድ እንዲማሩ በመርዳት ላይ እንዳሉ ንገረው።
6 ከእያንዳንዱ ተመላልሶ መጠየቅ በኋላ ውጤታማነትህን ለማሻሻል በማቀድ ተመላልሶ መጠየቁ እንዴት እንደነበር አንድ በአንድ መርምር። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- የምናገረው አንድ የተወሰነ ነገር በአእምሮዬ ይዤ ነበርን? ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩሩ አድርጌ ነበርን? የገነባሁት በመጀመሪያ ውይይታችን ጊዜ በተጣለው መሠረት ላይ ነበርን? አቀራረቤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የታቀደ ነበርን? መልሶችህ አዎንታዊ ከሆኑ ጥሩ የአምላክ ቃል አስተማሪ ለመሆን እየጣርክ እንዳለህ ያረጋግጣል።