ሌሎች ራሳቸውን እንዲጠቅሙ እርዷቸው
1 ይሖዋ ማወቅ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ እንደሚያስተምረን ቃል ገብቶልናል። በመዝሙር 32:8 ላይ “አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይህ ማረጋገጫ ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም አለው። ያለምንም ራስ ወዳድነት ሌሎች ሰዎች ጥበብ የሞላባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች በመከተል እንዴት ራሳቸውን መጥቀም እንደሚችሉ ልናሳያቸው እንፈልጋለን። (ኢሳ. 48:17) በመስከረም ወር ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ በማበርከት ይህንን ማድረግ እንችላለን። መልእክቱን ስናቀርብ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ማሳየት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ።
2 በአሁኑ ጊዜ በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች በሰፊው ስለተዛመቱ “ለዘላለም መኖር ” ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚከተለውን ሐሳብ ለመናገር ትመርጥ ይሆናል:-
◼ “ካነጋገርኳቸው ሰዎች መካካል አብዛኞቹ በትዳር ውስጥ ደስታ ማጣትና ፍቺ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱ በጣም አሳስቧቸዋል። እርስዎ ስለዚህ ችግር ምን ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ብዙ ሰዎች የችግሮቹ ዋነኛ መንስኤዎች ምን እንደሆኑ መገንዘብ ተስኗቸዋል። የትዳር ጓደኛሞች ልባዊ ጥረት ቢያደርጉ ትዳራቸውን ከመፍረስ ማዳን ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ደስታ ሊያገኙበት ይችላሉ። ትዳርን የተሳካ ለማድረግ ቁልፉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ነው።” ኤፌሶን 5:28, 29, 33ን አንብብ። ገጽ 243ን አውጥተህ በአንቀጽ 16 እና 17 ላይ ካወያየኸው በኋላ መጽሐፉን አበርክትለት።
3 ወላጆች ለልጆቻቸው በቂ ጊዜና ሥልጠና ሊሰጧቸው ያስፈልጋል። “ለዘላለም መኖር ” የተባለውን መጽሐፍ ስታስተዋውቅ እንደዚህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ሁላችንም ስለ ልጆቻችን የወደፊት ደህንነት እናስባለን። ልጆች የወደፊት ሕይወታቸው አስተማማኝ እንዲሆን ወላጆች አስተዋጽኦ ሊያበረክቱበት የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ምን ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የዛሬ 3,000 ዓመት ገደማ የተጻፈ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ የሚሰጠውን ይህንን ምክር ላንብብልዎት። [ምሳሌ 22:6ን አንብብ።] ልጆቻችን በትምህርት ቤት ከሚሰጣቸው ትምህርት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጠቀሙ መቻላቸው ባይካድም ከሁሉ የተሻለ ጥቅም ያለውን ሥልጠና የሚያገኙት ወላጆች እቤት ከሚሰጧቸው ማሠልጠኛ ነው። ይህ ማሠልጠኛ ጊዜ፣ ትኩረትና ፍቅር ቢጠይቅም እነዚህ ጥረቶች ሊደረጉለት የሚገባው ነው።” ገጽ 245ን አውጥተህ በአንቀጽ 20 እና 21 ላይ ከተወያያችሁ በኋላ ይህ መጽሐፍ በቤተሰብ ጥናት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዴት መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ግለጽለት።
4 ምድር እንዴት ገነት እንደምትሆን በማሳየት “ለዘላለም መኖር ” የተባለውን መጽሐፍ ለማበርከት ትፈልግ ይሆናል:-
◼ “የወደፊቱ ሕይወትዎ ምን እንደሚመስል ለማወቅ እንደሚፈልጉ እርግጠኛ ነኝ። ኢየሱስ አባታችን ሆይ በተባለው ጸሎት ላይ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ይሁን ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። ይህ ነገር ሲፈጸም ምድር ምን ትመስል ይሆን? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እዚህ ላይ ሠዓሊው ገነት የምትሆነዋን ምድር እንዲህ ባለ ሁኔታ አስቀምጧታል። [በገጽ 12 እና 13 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየው። ከዚያም በአንቀጽ 12 ላይ የተጠቀሰውን ኢሳይያስ 11:6–9ን አንብብ።] እንዲህ ባለው ዓለም ውስጥ መኖር በጣም አያስደስትምን? ይህ መጽሐፍ እርስዎና ቤተሰብዎ እንዲህ ባለው ገነት ውስጥ እንዴት መኖር እንደምትችሉ ይገልጽልዎታል።”
5 አቀራረብህን ቀደም ብለህ መዘጋጀትህ በበር ላይ ለምታገኘው የተሳካ ውጤት ቁልፍ ነው። በሩን ከማንኳኳትህ በፊት ስለ አንድ ቅዱስ ጹሑፋዊ ትምህርት የምትናገረው አንድ የተጨበጠ ነገር እንዳለህ አረጋግጥ። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፉን ለመውሰድ ፈቃደኛ ካልሆኑ አበረክታለሁ ብለህ ከያዝከው መጽሔት ወይም ትራክት ውስጥ ፍላጎታቸውን የሚቀሰቅስ አጠር ያለ ሐሳብ በአእምሮህ ያዝ። በመስከረም ወር የሚከፈትልህን ማንኛውም አጋጣሚ የመንግሥቱን የእውነት ዘር ለመዝራት ተጠቀምበት። (መክብብ 11:6) እንዲህ በማድረግ ሌሎች ዘላለማዊ ዘለቄታ ያላቸው ጥቅሞች እንዲያገኙ ትረዳቸዋለህ።