ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሳችሁ አነጋግሩ
1 ተመላልሶ መጠየቆች በማድረግ ረገድ ቁም ነገረኞች መሆናችን ለይሖዋና እኛን መሰል ለሆኑ ሰዎች ያለን ፍቅር መግለጫ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግና እንድናስተምር በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ለሰጠን መመሪያ ታዛዥ እንደሆንን ያሳያል። ተመላልሶ መጠየቅ ሕይወት አድን በሆነው ሥራችን ውስጥ ወሳኝ ድርሻ አለው። (እባክህ ምሳሌ 24:11, 12ን አንብብ።) ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ የተደራጀን ከሆንን መጀመሪያ ስናነጋግር የዘራነውን ዘር ዲያብሎስ ለቅሞ ሊወስደው አይችልም። (ማቴ. 13:19) ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች በሚገባ በማስታወሻህ ላይ ትመዘግባለህን? ሁልጊዜ ለተመላልሶ መጠየቅ ጊዜ ትመድባለህን? ያደረግሃቸውን ተመላልሶ መጠየቆች በጥንቃቄ መዝግበህ ሪፖርት ታደርጋለህን? እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ በቀላሉ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የሚያስችሉ ሐሳቦች ቀጥሎ ቀርበዋል። ምሳሌዎቹ የቀረቡት የምታነጋግረውን ሰው ሰላምታ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ደህንነቱን እንደምትጠይቀው ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
2 በአምላክ ላይ የነበረውን እምነት ያጣ ሰው አነጋግረህ ከነበረና መጠነኛ ፍላጎት አሳይቶ ከነበረ ከመጽሐፉ በገጽ 12 እና 13 ላይ ያለውን ሥዕል አውጥተህ እንደሚከተለው በማለት ልትጀምር ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ውብ የሆኑ አካባቢዎችን የሚያሳየውን ይህን የሚያምር ሥዕል ተመልክተን ነበር። ‘ይህን ዓይነቱን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ያለብዎ ይመስልዎታል?’ [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ልናሟላቸው ከሚገቡ ዋና ዋና መሠረታዊ ብቃቶች መካከል አንዱን በግልጽ አስቀምጧል። [ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።] በአምላክ ለማመን እውቀት ያስፈልጋል። ማወቅ የሚያስፈልገንን ነገር ለመማር የሚያስችለን በጣም ጥሩ የሆነው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ማጥናት ነው።” ምዕራፍ 1ን አውጣና ከአንቀጽ 1 እስከ 3 ውስጥ ያሉትን የሚያበረታቱ አንዳንድ ሐሳቦች አሳየው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ አሳየውና ተመልሰህ መጥተህ የበለጠ ውይይት ማድረግ እንድትችሉ ሐሳብ አቅርብለት።
3 አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ተመልሰህ የምትሄድ ከሆነ እንደሚከተለው ማለት ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው መጥቼ በነበረበት ጊዜ ስለ [ተነጋግራችሁበት የነበረውን ጉዳይ ጥቀስ] ተነጋግረን ነበር። አምላክ በዓለም ላይ ብዙ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ጥያቄ ተነስቶ ነበር። ምን መደምደሚያ ላይ ደረሱ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ ለእነዚህ አስጨናቂ ሁኔታዎች ተጠያቂ አለመሆኑን ማወቁ የሚያበረታታ ነው።” ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 99 እና 100 አውጣና በእነዚህ ገጾች ላይ ባሉት አንቀጾች ውስጥ ከሚገኙት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች በጥቂቶቹ ላይ ተወያዩ። በሌላ ጊዜ ተመልሰህ በመምጣት አምላክ በቅርብ ጊዜ መከራን እንደሚያስወግድ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ ልታወያየው እንደምትፈልግ ግለጽለት።
4 በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች የሚያሳስቡትን አንድ ወላጅ ለማነጋገር ተመልሰህ የምትሄድ ከሆነ እንደሚከተለው ማለት ትችላለህ:-
◼ “ወላጅ እንደመሆንዎ መጠን ለልጆችዎ የተሻለ ነገር እንደሚመኙላቸው አውቃለሁ። ልጆችዎን መጥፎ ከሆነው ነገር ሁሉ መጠበቅ ስለማይችሉ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት መወጣት እንደሚችሉ ሊያስተምሯቸው ይገባል። ይህንን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ይመስልዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አንድ ወላጅ ለልጆቹ ሊያደርግ ከሚችላቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች አንዱ ሥልጠና መስጠት ነው።” ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 245-6 አውጣና የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮችን አስፈላጊነትና ምክሩን መከተሉ በረከት ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ በማጉላት መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ተግባራዊ ምክር ላይ እንዲያተኩሩ አድርግ። በዚህ መጽሐፍ በመጠቀም የቤተሰብን ኑሮ አስደሳች ለማድረግ የሚረዱ ተጨማሪ ሐሳቦች ማግኘት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለማሳየት ሌላ ጊዜ ተመልሰህ እንደምትመጣ ግለጽለት።
5 አጠር ያለ አቀራረብ ተጠቅመህ ላነጋገርካቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “አምላክ እንድናረጅና እንድንሞት ዓላማ አልነበረውም። ዓላማው ገነት በሆነች ምድር ውስጥ ለዘላለም እንድንኖር ነበር።” ገጽ 162 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየው። በገጽ 74-5 የሚገኙትን ከ16-18 ያሉትን አንቀጾች አንብብ። ሌላ ጊዜ ተመልሰህ ለመምጣት ቀጠሮ ያዝ።
6 ይህ መጽሐፍ ይሖዋ በመጨረሻ ቀናት ውስጥ የመሰብሰቡን ሥራ ‘ለማፋጠን’ ያዘጋጀው አንዱ ዝግጅት ነው። (ኢሳ. 60:22) ውጤታማ በሆነ መንገድ ከተጠቀምንበት ሰዎችን የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ልንረዳበት እንችላለን።