የጥያቄ ሣጥን
◼ በተደጋጋሚ እቤታቸው ሄደን ላላገኘናቸው ሰዎች ደብዳቤ በምንጽፍበት ጊዜ በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?
አንዳንድ ሰዎች ቤት በምንሄድበት ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ እነርሱን እቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ እናገኘዋለን። አንዳንድ አስፋፊዎች እነዚህን ሰዎች ለማግኘት ደብዳቤ መጻፍ የተሻለ ዘዴ ሆኖ አግኝተውታል። ደብዳቤ መጻፍ ውጤት ቢኖረውም ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለማስቀረት አንዳንድ ማሳሰቢያዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ይሆናል:-
በማኅበሩ አድራሻ አትጠቀም። በማኅበሩ አድራሻ መጠቀም ደብዳቤው ከቢሯችን የተላከ ያስመስላል። ይህም አላስፈላጊ ችግር ከመፍጠሩም በላይ ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ወጪ ያስከትላል።
የቤቱ ባለቤት ትክክለኛ አድራሻ መጻፉንና በቂ ቴምብር መለጠፉን አረጋግጥ።
አድራሻውን “እዚህ ቤት ለሚኖሩ ኗሪዎች” ብለህ ከመጻፍ ይልቅ የሰውዬውን ትክክለኛ ስም ተጠቀም።
እቤት ማንም ሰው ከሌለ ደብዳቤዎችን በበሩ ሥር አሽሉከህ አትክተት።
አጭር መልእክት የያዙ ደብዳቤዎች ይመረጣሉ። ረዥም መልእክት ከመጻፍ ይልቅ ትራክት ወይም መጽሔት ከደብዳቤው ጋር አባሪ አድርጎ መላክ ይመረጣል።
በጽሕፈት መኪና የተጻፉ ደብዳቤዎች ለማንበብ የቀለሉ ሲሆን ጥሩ ግምት ያሰጣሉ።
ቀደም ብለህ ሰውዬውን በግል እስካላነጋገርከው ድረስ ደብዳቤዎች ተመላልሶ መጠየቅ ተብለው አይቆጠሩም።
ቀደም ሲል ፍላጎት ላሳየ ሰው ደብዳቤ የምትጽፍ ከሆነ ከሰውዬው ጋር ለመገናኘት እንድትችል አድራሻህን ወይም ስልክ ቁጥርህን መግለጽ ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠኛ ፕሮግራም እንዳለን ግለጽ።
አካባቢው በሚገኘው ጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ግብዣ አቅርብለት። ስብሰባው የሚደረግበትን ቦታ አድራሻና ስብሰባው የሚጀመርበትን ሰዓት ግለጽ።
ክልልህን ሸፍነህ ካስረከብክ በኋላ እቤታቸው ላላገኘሃቸው ሰዎች ደብዳቤ መጻፍህን መቀጠል አይኖርብህም። አሁን ክልሉን ተረክቦ በመሥራት ላይ ያለው አስፋፊ ተከታትሎ የመርዳት ኃላፊነት አለበት።