አምላክ ምን እንደሚፈልግባቸው አስተምሯቸው
1 ‘የይሖዋን ቃል ሳይሰሙ’ ቀርተው በመንፈሳዊ የተራቡ ብዙ ሰዎች አሁንም አሉ። (አሞጽ 8:11) አንዳንዶች አምላክ እንዳለ የሚያምኑ ቢሆኑም ዓላማውና እሱ የሚፈልግባቸው ብቃቶች ምን እንደሆኑ አያውቁም። ስለዚህ ለእነርሱ ሕይወት አድን የሆነውን የመንግሥቱን እውነት የማስተማር ግዴታ አለብን። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመመስከር በሚገባ የታጠቅንና የተዘጋጀን በመሆን ይሖዋ የሚፈልግባቸውን ብቃቶች ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎችን ማግኘት እንችላለን።
2 በመጋቢትና በሚያዝያ የምናበረክታቸው ወቅታዊ የሆኑ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትሞች ይኖሩናል። በተጨማሪም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘውንም ብሮሹር ማበርከት እንችላለን። ብሮሹሩ የያዛቸው ማራኪ ሥዕላዊ መግለጫዎቹና ስሜት ቀስቃሽ የሆኑት ጥያቄዎቹ ሰፊ ተቀባይነት እንዲኖረው አስችለውታል። ግሩም በሆኑት ጽሑፎቻችን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንጠቀምባቸው የሚረዱን የሚከተሉት ሐሳቦች ቀርበዋል።
3 ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት:- ከቤት ወደ ቤት በምንሄድበት ጊዜ እቤታቸው የማይገኙ ብዙ ሰዎች ስላሉ በተገኙበት ቦታ ሁሉ ሰዎችን ፈልጎ ማነጋገር ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። በመስከረም 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ሆኖ የወጣው ጽሑፍ ምስራቹን በሁሉም ቦታ ማለትም በመንገድ ላይ፣ በሕዝብ መጓጓዣዎች፣ በመናፈሻዎችና በንግድ ቦታዎች እንድንሰብክ ማበረታቻ ሰጥቶን ነበር። በተጨማሪም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመስበክ አጋጣሚዎችን የመፍጠርን አስፈላጊነት አስገንዝቦናል። በሁሉም ቦታ ምስራቹን በመስበክህ ምን ውጤት አግኝተሃል? መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! እንዲሁም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘው ብሮሹር የሰዎችን ሕይወት የሚነኩና የማሰብ ችሎታቸውን የሚቀሰቅሱ እውቀቶችን ስለያዙ ለየትኛውም የምስክርነት ዘርፍ ተስማሚ ናቸው።
4 ውይይት መጀመር:- የጥቅምት 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን የመጨረሻ ገጽ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በመጠቀም የራስህን መግቢያ እንዴት ማዘጋጀት እንደምትችል ዝርዝር ሐሳቦችን አቅርቦ ነበር። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተሰኘው ብሮሹርም ተጠቅመህ የራስህን መግቢያ ለማዘጋጀትም እነዚሁ ሐሳቦች ይረዱሃል። ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ወይም አንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ብቻ ልንናገር እንችላለን። የምታነጋግረው ሰው ማዳመጡን እንዲቀጥል ሊወስኑ ስለሚችሉ የመክፈቻ ቃላትን በጥንቃቄ መምረጥ በጣም አስፈላጊ ነው። አንዳንዶች የሚከተለውን ዓይነት የመክፈቻ ቃላት በመጠቀማቸው ተሳክቶላቸዋል:- “አንድ የሚያበረታታ ጽሑፍ አንብቤ ነበር። ይህንን ሐሳብ ላካፍልዎት እፈልጋለሁ።” ወይም ሰውየውን በውይይት ውስጥ ለማስገባት የሚረዳ አንድ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል።
5 ለአካባቢያችሁ ተስማሚ ከሆነ በዚህ ወር በምትጠቀሙበት መግቢያ ላይ እንደሚከተለው ያለ ጥያቄ ማቅረብ ትችላላችሁ:-
◼ “በአሁኑ ጊዜ ብዙ ቆሻሻ፣ በየቦታው የወዳደቁ ወረቀቶችና የአካባቢ መበከል መኖሩን የሚያሳዩ ነገሮችን እንመለከታለን። ምድርን ለማጽዳትና ለመኖሪያነት ተስማሚ የሆነ ቦታ ለማድረግ ምን ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለትና ምድር ዓለም አቀፍ ውብ የአትክልት ቦታ የሚሆነው እንዴትና መቼ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳለህ ግለጽ። ግልጽ የሆነ ሐሳብ፣ አጠር ያለ ጥቅስና በእጅህ ካለው መጽሔት ውስጥ ጥሩ ሥዕላዊ መግለጫ አሳይና እንዲያነበው ለሰውየው አበርክትለት። ውይይቱን ከመደምደምህ በፊት ውይይታችሁን በሌላ ጊዜ ለመቀጠል እንድትችሉ ቀጠሮ ለመያዝ ሞክር።
◼ “በአሁኑ ጊዜ ተጋርጠውብን እንዳሉት ዓይነት ችግሮች በሞሉበት አካባቢ እንድንኖር የአምላክ ዓላማ ይመስልዎታል?” ሰውየው መልስ ከሰጠ በኋላ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:- “ኢየሱስ ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት ይምጣ ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸውን ጸሎት በሚገባ ሳያውቁ አይቀሩም። ታዲያ የአምላክ መንግሥት በእርግጥ ምንድን ነው? ብለው አስበው ያውቃሉ?” አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር ትምህርት 6ን አውጣና በትምህርቱ መጀመሪያ ላይ የሰፈሩትን ጥያቄዎች አንብብ። ከዚያም አንቀጽ 1ን አንብብና የመጀመሪያው ጥያቄ መልስ የት እንደሚገኝ ጠቁመው። ለቀሩትም ጥያቄዎች አጠር ያለ መልስ እንደተሰጣቸው አብራራ። ብሮሹሩን አበርክትና መንግሥቱን አስመልክቶ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ እንደገና ልትገናኙ እንደምትችሉ ሐሳብ አቅርብ።
◼ “በዓለም የሚገኙ ሃይማኖቶች የሰው ልጆች ለገጠሟቸው ችግሮች መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ጭራሽ ችግር ፈጣሪ መሆናቸውን ብዙ አስተዋይ ሰዎች መገንዘብ ጀምረዋል። ስለዚህ ጉዳይ እርስዎ ምን ይሰማዎታል?” የሰውየውን አመለካከት ካዳመጥክ በኋላ ፍላጎቱን ሊያነሳሳ የሚችል ስለ ሐሰት ሃይማኖት ውድቀት ወይም ጥረቷ ከንቱ መሆኑን የሚገልጽ አንድ ሐሳብ በእጅህ ካለው መጽሔት አሳየው። መጽሔቱን ማንበብ ይፈልግ እንደሆነ ጠይቅ። ስማችሁን ከተለዋወጣችሁ በኋላ እውነተኛው ሃይማኖት የሰው ዘሮችን ችግር እንዴት እንደሚፈታ ለመወያየት በድጋሚ እንድትገናኙ ቀጠሮ መያዝ እንደምትፈልግ ግለጽ።
◼ “በዛሬው ጊዜ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ብዙ ችግሮች ያሉ ቢሆንም ደስታ የሰፈነበት ቤተሰብ ለማግኘት የሚያስችለው ምሥጢር ምንድን ነው? ብለው ጠይቀው ያውቃሉ?” መልስ እስኪሰጥ ጠብቅና አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደስታ የሰፈነበት ቤተሰብ የሚያስገኘውን እውነተኛ ቁልፍ ግልጽ አድርጎ እንዳስቀመጠ አብራራ። ምናልባትም ኢሳይያስ 48:17ን ልታነብ ትችላለህ። ከዚያም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር ትምህርት 8 አውጣና ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የቀረበውን አስተማማኝ መመሪያ የሚገልጹ ጥቂት ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንብብ። በትምህርቱ መጀመሪያ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አንብብ። ሰውየው መልሶቻቸውን ማንበብ ይፈልግ እንደሆነ ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስ ደስታ ለሰፈነበት ቤተሰብ የያዛቸውን ተጨማሪ ተግባራዊ መመሪያዎች ለማብራራት ሌላ ጊዜ ተመልሰህ እንደምትመጣ ግለጽ።
6 በመጋቢት 1997 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ሆኖ የወጣው ጽሑፍ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ደፋሮች እንድንሆን ማበረታቻ ሰጥቶናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይት ስናደርግ ባይሳካልን እንኳ ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር እንድንጠቀም ሐሳብ አቅርቧል። የሰው ዘር ከሁሉም በላይ የሚያስፈልገው ነገር አምላክ ምን እንደሚፈልግበት ማወቅና በሥራ ላይ ማዋል ነው። (ቆላ. 1:9, 10) ይሖዋ ለሕይወት ያወጣቸውን የምናውቃቸውን ብቃቶች ሰዎችን ለማስተማር ከጀመርን በሚያዝያና በግንቦት ሌሎችን በጣም እንረዳቸዋለን።— 1 ቆሮ. 9:23